የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ
"ወንድ ወደ ችሎት ሴት ወደ ማጀት" (በእሙ-ኢሳን)
Updated: Jun 9, 2019

ይባል ነበር ድሮ…ድሮ “ወንድ ወደ ችሎት ሴት ወደ ማጀት”። ዛሬ… ዛሬ ግን ለቀኑ ቀን ይስጠውና ሴቶች ወደ ማጀት ሳይሆን ወደ ችሎት እየወጡ ነው። በዚህ መልካም ተግባር ጠቅላያችንን ሳላመሰግን አላልፍም። እስከ ዛሬ ድረስ በእኔ እድሜ የወንድ እንጂ የሴት መሪ አልተከሰተም። ወይም ሴት ሲመራ እንጂ ሲመራ አላየሁም። ከመመራት ወደ መምራት ላሸጋገረን የአለማቱ ጌታ ምስጋና ይግባውና ዛሬ እኛ ሴቶቹ ከማጀት ወጥተናል።
ብታምኑ ባታምኑም ከአንድ ስኬታማ ወንድ ጀርባ ጠንካራ ሴት አለች። “ከሴት ብልሃት አይጠፋም ይባል የለ” ውድ ወገኖች ይህንን ብልሃት የምታገኘው እኮ የእለት ተእለት ተግባሯን ስታከናውን በህይወቷ የሚገጥማትን ችግር ሁሉ በድል ለመወጣት በምታደርገው የትግል ቆራጥነትን ለነገሮቿ መፍቻ ቁልፍ ትፈልግለታለች። በተጨማሪም ለእያንዳንዱ ችግር መፍትሄ ታበጅለታለች።
ሴት ልጅ ጥንካሬን የምትማረው ገና በልጅነቷ ነው። ወላጆቿ ቤት ወላጆቿን በስራ በማገዝ የአቅሟን እያበረከተች ታድጋለች። ከዛም እድሜዋ ለጋብቻ ሲደርስ እና ትዳር ስትመሰርት ሃላፊነቷ ይጨምራል። ሴት ልጅ ለእራሷ የምትኖረው በጣም ትንሹን ጊዜ ብቻ ነው። ሃላፊነትን ወላጆችዋን በማገልገል ትጀምራለች። ከዚያም ትዳር ይዛ ልጆችን ስታፈራ ለልጆቿና ለለባሏ ሃላፊነቷን በመወጣት ረገድ ተወዳዳሪ የላትም። ለባሏ ስኬት ቀን ከለሊት ትለፋለች። ለልጆቿም እንደዚሁ።
ድሮ… ድሮ “ሴት” የስድብ ወይም “የፈሪ” መገለጫ ነበር። የሚገርመኝ “ሴት” ብለው የሚሳደቡት ናቸው። ከሴት ተወልደው፣ ሴት አግብተው እና ሴት ወልደው “ሴት” ብለው ሲሳደቡ ማንነታቸውን እረስተዋል እንዴ ? ያስብላል !
እናንተ… በወንዶች አመለካከት ጫና ደርሶባችሁ አሚን ብላችሁ የተቀበላችሁ ሴቶች እንዲሁም እናንት… ወንዶች “ሴትነት” የፆታ መገለጫ እንጂ የበታችነት ወይም የማሳነስ መገለጫ አይደለም። በታሪክ ሴቶች ሃላፊነት በመሸከም የሚስተካካላቸው የለም። የእለት ሰራቸውን እየሰሩ ጥንካሬንና ስኬት ያለ ምንም እንከን ይወጡታል። የሚፈልጉትም ለመወሰን ወደ ዃላ አይሉም። እናም ዘሬ… ዛሬ እመቀመጫው ላይ ያሉት ሴቶቻችን ሃላፊነታቸውን በበቂ ሁኔታ አይወጡም የሚል ግምት የለኝም። ስጋቴ ግን ወንበሩን እንዲዘውሩት ሙሉ ፍቃድ አግኝተዋልን ? የሚለው ነው። ወይስ ሳሎን እንዳለ አበባ ለጌጥ ብቻ ነው የተቀመጡት። በዘመነ ደርግ “ያለ ሴቶች ተሳትፎ አብዮት ግቡን አይመታም” እየተባለ በአደባባይ እየተነገረ የመቁረጡ የመፍለጡ ተግባር ግን በወንዶቹ ብቻ ነበር የሚተገበረው። የአብይ ኢህዴግ ዘመንም እንደ ዘመነ ደገርግ እንዳይሆን ስጋቱ አለኝ። ከስጋትም አልፎ እህታችን የመከላከያ ሚኒስትሯ የሹመት ፊርማቸው ሳይደርቅ በወንድ ተተክተዋል።
ለሴቶች ያለ ምንም ተጽእኖ ስልጣን ተሰጥቷቸው ያለ… ማንም ተጽእኖ እራሳቸው እና እራሳቸው ብቻ የሚመሩት ከሆነ “ከሴት ያወቀ የለምና” ውጤታማ እንደሚሆኑ አልጠራጠርም። ስለዚህ ሜዳውን ብቻ ሳይሆን ሜዳውን ከነፈረሱ ሰጥተን ውጤቱን እንጠብቅ እላለሁ።
እስከዛሬ ባለው ታሪክ የምንስማማው ብሎም ዛሬ… ዛሬ በ21 ክፍለ ዘመን በሃገራችን እና በመላው አለም እየተከሰተና እያየነው ያለው ግጭት በወንድነት ስሜት ተሞልተው ወይም ወንዶች እያንዳንዱን ነገር በሃይል ለማስከበር የሚያደርጉት ሩጫ ሰላምን ከማሳጣቱ ባሻገር የበርካታ ወጣቶች ህይወትን ቀጥፏል። ስለዚህ ምናልባት ስልጣኑና ሃገርን የመምራቱ ስራ ለሴቶች ቢሰጥ ከሃይል ይልቅ ፍቅርን ከችኮላ ይልቅ ትእግስትን እንዲሁም መቻልን የተካኑ ሴቶቻችን ከሁሉም ነገሮች ውድ የሆነውን ሰላምን ያመጡልናል ብዬ አምናለሁ።
ወንድነት የፆታ መገለጫ እንጂ የጀግንነት መለያ ወይም ምልክት አይደለም። ስለዚህ እባክዎን ጠቅላያችን ለሴቶች የሚሰጧቸውን ወንበር ከነማዘዣው ይስጧቸውና ውጤቱን በጋራ እንጠብቅ።
የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ሆይ “ሴት እናት ናት”። “እናት ደግሞ በሃገር ትመሰላለች”። ታዲያ ይችህ ሃገራቸን ይህንን ከእዚያ ሳትለይ ሁሉንም አቅፋ ይዛለች። ታዲያ ለዘር ክፍፍሉ መድሃኒት ከእናት-ከሴት የተሻለ የለምና ሃለፊነቱ ወይም ሃገር የመምራቱ ስራ ለሴቶቹ ይሰጥ ባይ ነኝ።
እሙ ኢሳን
ሪያድ ሳዑዲ አረቢያ