የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ
ደራሲ ማን ነው? (አያልነህ ሙላቱ )
Updated: Jun 9, 2019

አንተ ባለቅኔ! አንተ ልብ-ወለድ ወላጅ
ሥነጽሑፍን ከሕዝብ ገንጥሎ ተራማጅ::
ከመካከል ቁመህ ደረትህን አትንፋ
ወይ እሳቱን አንድድ ወይ እሳቱን አጥፋ…
ወይ ነፋሱን አግድ ወይ ነፋሱን ግፋ
ወይ ደመናን ጥረግ ወይ ደመናን አስፋ
ወይ ትንፋሽህን ዋጥ ወይም ትንፋሽ ትፋ::
ወይ ዐይንህን ግለጥ ወይ ዐይንህን ዝጋ
ወይ ጀሮህን ድፈን ወይ ጀሮህን አትጋ::
ወይ ታጠቅ ተፈሪ ወይም ታጠቅ ቁምጣ
ወይም ፀሐይ አግባ ወይም ፀሐይ አውጣ::
አልሚ-አጥፊ ተብለህ አብጅ ዘመድ ጓድ
ሁለት የወደደ አያገኝም አንድ::
ነፋስ አንከባሎም ወደ አንዱ አይጎልትህ
መጥፎና መልካሙን ሳይመርጥ ጭንቅላትህ::
ሥነጽሑፍ የሕዝብ ናት የሰፊው ሕዝብ ምርጫ
የላትም ጉራንጉር የግል መሸጎጫ
የልፍኝ ቤት መግቢያ… የጓሮ በር መውጫ::
እና! የምንለው የደራሲው ብዕሩ
ወይም ከሕዝብ ሆኖ ቀይ ይሁን መስመሩ::
ከሕዝቡ ደም ነክሮ ይጻፍ የሕዝብ ዋይታ
ወይም ከውሃው ጠቅሶ በውሃው ግጥም ይምታ::
ከሁለቱ መርጦ ባንደኛው ካልጣፈ
ለደሙም ለውሃውም ጠላት ነው የጦፈ::
ግን ከመኸል ቁሞ መንገዱን ከዘጋ
ኸንጥ ይግባ ተገፍቶ ምን አለው ከእኛ
አያልነህ ሙላቱ ‹‹ወይ አንቺ አገር›› (2004)