top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ጥላቻ ቀድሞ የሚገለው ማንን ነው? የምንጠላውን ወይስ እኛን? (በሚስጥረ አደራው)

Updated: Jun 9, 2019ጥላቻ ቀድሞ የሚገለው ማንን ነው? የምንጠላውን ወይስ እኛን?

ከዚህ ቀደም ታላቋ አሜሪካ በዘር ጉዳይ መታመሷ የዓለም መገናኛዎች ቀኑን ሙሉ እያወሩ የሰነበቱበት እርዕስ ነበር። ምንም እንኳን በዘር ላይ የተመሰረተ ጥላቻ የነበረ ቢሆንም። በወቅቱ ግን ይህንን ጥላቻ ከአሸለበበት የቀሰቀሰው አጋጣሚ ስለተከሰተ ነበር፤ የእይንዳንዱን ሰው የተደበቀ ስሜት ሊያወጣው የቻለው። በየዜና ጣቢያው ሲወሩ ከነበሩት ዜናዎች፤ ፉከራዎችና ምኞቶች ሁሉ ሃሳቤን የሰረቀው ነገር ግን ሌላ ነበር።

እንደሚታወቀው የአሜሪካኖች ዋናው ችግራቸው በጥቁሮችና በነጮች መካከል ያለው የዘር ልዩነት ነው። ይህም በተለይ የነጮችን የበላይነት በሚያራምዱ ጥቂት በማይባሉ ሰዎች የሚቆሰቆስ እሳት ነው። የሚገርመው ግን ይህ የዘር ልዩነት እሳት የሚነሳው፤ በእያንዳንዱ ግለሰብ ልብ ውስጥ በተቀጣጠለች ትንሽዬ ፍም ነው። እኔም ሰሞኑን ጥያቄ የሆነብኝ ይህ “ፍም” እንዴት ልባችን ውስጥ ገባ? የሚለው ነው። ነገሮች በአገር እና በማህበረሰብ ደረጃ ከመታየታቸው በፊት በግለሰብ ደረጃ መቃኘት አለባቸው ብዬ አምናለው። ምክንያቱም አገር ማለት “እኔ” እና “እኔ” ሲደመር ማለት ስለሆነ፤ የችግሮች ሁሉ እሳት መነሻው ግለሰብ ነው ብለን መደምደም እንችላለን።

ጥላቻ ከፍቅር ይበልጥ ጉልበትን የሚጠይቅ ስሜት ነው። ፍቅርን በቁልቁለት፤ ጥላቻን በዳገት መመሰል ይቻላል። ፍቅር የሰው ልጅ ተፈጥሮ ስለሆነ፤ ምንም ጉልበት የማይጠይቅ በቀላሉ የምንጓዘው መንገድ ነው። ጥላቻ ግን በጉልበት የተሞላ፤ በፍርሃት የሚገፋ ከባድ ተራራ ነው። ምንም እንኳን ጥላቻ እጅግ የቆሸሸ ነገር ቢሆንም፤ የሰውን ልጅ ልብ ግን ፈጽሞ ሊያመነችክ እንደማይችል የሚያሳይ ታሪክ ላውጋችሁ። አመታትን ያስቆጠረ ጥላቻ፤ በፈጣሪ ሃይል ብቻም ሳይሆን በተራ ሰው ትንሽ ፍቅር የሚረታ ነገር መሆኑን ይህ ታሪክ በእርግጠኝነት ያሳያል።

ጆኒ ሊ ኬሪ ይባላል፤ በወጣትነቱ ነበር የነጮችን የበላይነት ያራምድ የነበረውን የጥላቻ ቡድን ኬኬኬን (KKK) የተቀላቀለው። በአንደበቱ እንደተናገረው ውስጡ በጥላቻ የተሞላ እረፍት የለሽ ሰው ነበር። ሲበዛ ጥቁሮችን ይጠላል፤ ጥቁሮችን ብቻም ሳይሆን ነጭ ያለሆነ ማንኛውንም ሰው ይጸየፋል። ጆኒ ኬኬኬን ከተቀላቀለ በኋላ እንደሱ በጥላቻ ከተሞሉ ሰዎች ጋር በመሆን ሌሎችን በመመልመል፤ ከተራ አባልነት ወደ መሪነት አደገ። በየሚዲያዎች እየቀረበም የቆመለትን የጥላቻ አላማ ሲሰብክ እና ሲያራምድ ቆየ።

በ1979 እ.ኤ.አ ጆኒ ለአንድ የሬድዮ ጣቢያ ክርክር እንዲያደርግ ተጋበዘ። ክርክሩ የተደረገው እሱ የነጮችን የጥላቻ ቡድን ደግፎ፤ ዌድ ዋትስ የተባለ ጥቁር አሜሪካዊ ደግሞ የጥቁሮችን መብት ብቻም ሳይሆን የመላ ሰውን እኩልነት ወክሎ ነበር። በነገራችን ላይ ዌድ ዋትስ የማሪቲን ሉተር ኪንግ የቅርብ ጓደኛ ከመሆኑም በላይ ለጥቁሮች ነጻነት በተደረገው ትግል ከፍተኛ አስተዋጽዎ አበርክቷል። በእለቱ የሆነውንና በጆኒ አንደበት የተነገረውን እነሆ

“የጠበቅኩት፤ የአፍሪካ ልብስ የለበሰ፤ ጸጉሩ የተንጨባረረ ጥቁርን ነበር፤ “ነጮች ይውደሙ” የሚል ትቢተኛ ጥቁር። ነገር ግን ዌድ ዋትስ ሲገባ፤ ሱፍ ለብሶ በእጁ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ይዟል። እጁን ዘርግቶ ሲጨብጠኝ፤ የኬኬኬን ህግ የጣስኩኝ መሰለኝ። በኬኬኬ ህግ መሰረት አንድ ነጭ ጥቁርን ከነካ ይበከላል። የጨበጥኩበትን እጅ ስመለከት ዌድ ዋትስ ‘”አይዞህ ጥቁርነቴ አይለቅም” ሲል አሾፈብኝ። ቀጥሎም “ምንም ብታደርግ እኔ አንተን እንድጠላህ አታደርገኝም” አለኝ። ከዛን ቀን ጀምሮ ብዙ ጥቃቶችን አድርገንበታል። ለምሳሌ ከጥቂት አመታት በኋላ ቤተክርስቲያኑን አቃጠልንበት። ቤተክርስቲያኑን ከማቃጠላችን በፊት ዋትስን በብዙ ፈትነነው ነበር። ምላሽ ግን አላገኘንም። ቤቱን በቆሻሻ እንሞላዋለን፤ ነጩን ልብሳችንን (የኬኬኬ አባላት የሚለብሱትን) ለብሰን ቤቱ ሄደን አስፈራርተነዋል፤ በስልክ በአካል ብዙ ብለነዋል እሱ ግን በቀልድ ከመመለስ በቀር ምንም አይለንም ነበር። ከዛ ሁሉ በኋላ ቤተክርስቲያኑን አቃጠልነበት። ሌላው ቢቀር ቤተክርስቲያኑን አቃጥለንበት በስልክ ደውዬ ድምጼን በመቀየር “ከዚህ በኋላ ብትፈራና ብትጠነቀቅ ይሻልሃል” ፤ ስለው ያወቀኝ በቀላሉ ነበር “ሀይ ጆኒ፤ ጊዜ ወስደህ ስለደወልክልኝ አመሰግናለው፤ እኔም ፈጣሪም እንወድሃለን” ነበር ያለኝ። ግራ ገባኝ፤ ሰው እንዴት ይህን ያህል ዘመን ጥላቻን በፍቅር ይመልሳል? በመጨረሻ አንድ አጋጣሚ ተከሰተ፤ በወቅቱ ጥቁሮች ነጮች ምግብ ቤት እንዲመገቡ ቢፈቀድም፤ እንደኔ አይነት ነጮች ግን እናስፈራራቸው ነበር፤ ታዲያ አንድ ቀን ዌድ ዋትስ የሆነ ምግብ ቤት ሲገባ አየንና እኔና ጓደኞቼ ተከትለነው ገባን። ዋትስ ዶሮ አዝዞ ሊበላ ተቀምጦ ነበር፤ እኔም ወደሱ ሄድኩና “ስማ ይህ ምግብ ቤት የነጮች ብቻ ነው ፤ ከዚህ ውጣ እምቢ ካልክ ግን አንድ ነገር ቃል ልግባልህ ፤ የቀረበልህን ዶሮ ምን እንደምታደርገው አይሃለው፤ እኔም አንተን ልክ እንደዛው ነው የማደርግህ፤ (ከበላኸው እበላሃለው ማለቱ ነው) ይሄኔ ዌድ ዋትስ ዶሮውን አነሳና ሳመው (ከሳምኩት ትስመኛለህ ማለቱ ነው)፤ ምግብ ቤቱ ውስጥ የነበሩት ሰዎች ነጮችን ጨምሮ በሳቅ ሞቱ፤ ከዛን ቀን ጀምሮ ይህ አንድ ግለሰብ እኛን ሁሉ እንዳሸነፈን ተረዳው፤ እሱን ማሳደዱን ተውነው፤ አሸነፈን” ሲል ለተለያዩ ሚድያዎች ቃሉን በተደጋጋሚ ሰጥቷል።

የጆኒ በጥላቻ የተሞላ ህይወት ከአመታት በኋላ ተለውጦ ነበር። የእሱን የለውጥ ሂደት ማንሳቱ አሁን አይቻለንም፤እረጅም ስለሆነ። ነገር ግን ጆኒ ዌድ ዋትስን “ የኬኬኬን ቡድን ያሸነፈ ብቸኛው ጥቁር፤ ምክንያቱም አይምሮውን እና ልቡን ስለተጠቀመ” ሲል ይገልጸዋል። የጆኒ ሊ ህይወት በራሱ አስገራሚ ነው። ከዛ የጥላቻ ህይወት ወጥቶ በአለም አገራት እየዞረ ፍቅርን ሰብኳል። ብዙ በጥላቻ መንችከው የነበሩ ልቦችን ከራሱ ህይወት በመነሳት አጥቧል። ጥላቻ የሚገድለው ጠይውን እንጂ ተጠይውን አለመሆኑን መስክሯል። የሚገርመው ከብዙ ጊዜ በኋላ ሲያሰቃየው እና ሲያንገላታው የነበረውን ዌድ ዋትስን አግኝቶ ይቅርታ በመጠየቅ፤ አመታትን የዘለቀ ጓደኝነት መመስረት ችሎ ነበር። ዌድ ዋትስ ሲሞትም በጆኒ እቅፍ ውስጥ ነበር፤ የመጨረሻ ቃሉም “የማርቲን ሉተርኪንግ ህልም እንዳይሞት አደራ” የሚል እንደነበር ጆኒ ተናግሯል። አደራውን ለመፈጸምም እሱም ህይወቱ እስከምታልፍ ጊዜ ድረስ ፍቅርን ሲሰብክ ኖሯል።

ጥላቻ በሽታ ነው፤ ምንም ጥያቄ የሌለው በሽታ። ይህ የዘር ጥላቻ ግን በማህበረሰብ ደረጃ የሚስፋፋው፤ ግለሰቦች የራሳችንን በሽታ መታከም ስላቃተን ነው። ያለንበት ግዜ ያስፈራል፤ የኔ ዘር የበላይ፤የሚለው አስተሳሰብ፤ ከፍርሃት የሚመጣ ካልታከመ የሚገድል አስከፊ በሽታ ነው። ግን ምንም ያህል ቆሻሻ ነገር ቢሆንም ፤ የሰውን ልብ ሊያመነችክ አይችልም፤ የይቅርታ ጠብታ በቀላሉ ስለሚያጥበው። አንዳንዴ እኮ ካስተዋልነው በአገር ስም፤ በሃይማኖት ስም፤ በዘር ስም ጥላቻን ስንደግፍ የቆምነው ለሃይማኖታችን፤ ለዘራችን እንዲሁም ለአገራችን ሳይሆን፤ ግላዊ ምክንያቶቻችን ለጠነሰሱት ከንቱ የጥላቻ አጀንዳ ነው። በእርግጠኝነት እዚህ አለም ላይ ጥላቻ የፈታው ችግር የለም፤ ታዲያ ለምን? ጥላቻ አሁንም ድረስ ስር ሰዶ ቤተ እምነታችንን፤ ዘራችንን እንዲሁም አገራችንን የሚያመሰው፤ እያንዳንዳችን በሽታችንን መታከመ ስላቃተን ነው። ቢሆንም ግን ተስፋ አለ፤ እንደ ዌድ ዋትስ አይነት ሰዎች አንድ ሆነው ሺዎችን ባያሸንፉ ኖሮ ምን ይውጠን ነበር?

እንደው የአለሙ ሰላምም ይቅር፤ የአገሩም አንድነት ይቆይ፤ ሰው ለገዛ ሰላሙ ካሰበ ጥላቻን ማስወገድ ግድ ይለዋል፤ አሲድ በአንድ እቃ ውስጥ ብዙ ሲቆይ መዝምዞ የሚጨርሰው የተቀመጠበትን እቃ ነው፤ ጥላቻም እንደዚሁ፤ የተቀመጠበትን ልብ ገዝግዞ ይጨርሳል እንጂ፤ የምንጠላው ሰውማ ምን ይሆናል? የሚጠላ ልብ ፈጽሞ ደስታን ሊያስተናግድ አይቻለውም፤ ምናልባት ለገዛ እራሳችን ሰላም ስንል ፍቅርን ብንለምድ ይበጀናል እንጂ፤ አገርማ የሰው ድምር ብቻ እኮ ናት። ጥላቻ ሰው መግደሉ አይቀርም፤ ቀድሞ የሚሞተው ግን የጠላው እንጂ የተጠላው አይደለም።


17 views0 comments
bottom of page