የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ
"ሥራ ፍቅርና ተስፋ" (በኪራም ታደሰ)
Updated: Jun 9, 2019

ባለቅኔው ጆን ባሮውስ መስኮቱ ላይ ቆም ብሎ ሲቃኝ አንድ ጎረቤቱ በቤቱ ጥግ ሲያልፍ ተመለከተ፡፡ ሰውዬም በደስታና በርካታ መንፈስ ሳይሆን በትካዜና በጭንቀት አቀርቅሮ ነበር የሚንገላወደው፡፡ ለዚህ ሁኔታው ያበቃው ምን እነደሆነ ጆን ባሮውስ ተረዳለት፡፡ ሰውዬው የሚወደውና የሚመስጠው ጊዜውን ትርጉምና አቅጣጫ የሚሰጥለት ምንም ዓይነት ሥራ አልነበረውም፡፡ ሥራ ያጣ ሰው ለሥቃይ የተዳረገ ነው ሲል ባሮውስ ማሰላሰል ያዘ፡፡ የደመቀ የወፎች ኅብረ ዝማሬን እያዳመጠና ለስላሳ የነፋስ ሽውታ እየተመገበ ባሮውስ በጉዳዩ ላይ ሲያስብበት ቆየ፡፡
የሥራን ክቡርነትና ህይወት አዳሽነት ከእርሱ ወዲያ የተገነዘበ አልነበረም፡፡ በአንድ ወቅት እርሱም ራሱ በሥራ አጥነት ለሥቃይ ከተዳረጉት ምስኪኖች መኻል አንዱ አልነበር? ያኔ ህይወት ጣዕሟን ነፍጋዋለች ፤ ባዶና ግትር ሆናበታለች፡፡ ያኔ መብላትም ሆነ መተኛት ፣ መጫወትም ሆነ መግባባት ተስኖት ነበር፡፡
ሥራ ነፍስ ዘራለት — እርሻ ላይ የመማሰን ፣ የማረስና የመጎልጎል ፣ የመዝራትና የመትከል ፣ የማረምና የመኮትኮት … ተግባራት ፣ ለም አፈር ጨብጦ በጣቶቹ መኻል የመናኘት ሥራ እርሱነቱን ከሚኖርባት ዓለም ጋር እንዳዋሐደለት በሚገባ ያውቀዋል፡፡
ደስታ ፣ እንደ ህልም ቦግ እልም የማትልና ዘወትር ከአጠገብ የምትገኝ መሆኗን ለሰዎች ለማስረዳት ምንኛ ተጣጣረ! ግን ፣ በዙሪያው የነበሩት ሁሉ ተስፋ በሚያስቆርጥ መንገድ እየዋተቱ ህይወታቸውን ሲከትሩት መመልከቱ አላስችል ብሎት የደስታ ምንጩ ሥራ ፣ መንፈስን የሚመስጥ ሥራ መሆኑን ለማስገንዘብ ቆርጦ ተነሣ፡፡
ከማንኛውም ነገር ሁሉ በላቀ ሁኔታ ደስታን የሚለግስ አንድ ነገር አለ ፤ ምን ይሆን?… በጣም ቀላልና በእጅ የሚገኝ ነው፡፡ ይህን ምስጢር ለጨረታ ላቀርበው ብችል ምን ያህል ሰው በጎረፈ! ዋጋውም ምንኛ በናረ! ብልሆች ብቻ ናቸው ምንነቱን የሚገምቱት፡፡ አንዳንዶቹ ጤንነት ፣ ወይም ገንዘብ ፣ ወይም ባልንጀራ ፣ ወይም ይህን ወይ ያን ሃብት ይሉ ይሆናል፡፡ ግን ፣ እነዚህ ሁሉ ተሟልተው ደስታ አትኖርም፡፡ ዝናና ሥልጣንም ደስታን አያስገኙም፡፡ ጤንነት ፣ ገንዘብ ፣ ባላንጀራ ፣ የሞቀ ቤት … ሁሉም አስፈላጊ ቢሆኑም ደስታ አያጎናጽፉምና ከእነዚህ ሁሉ የሚልቅ አንድ ነገር አለ፡፡ ያ ነገር — ምን ይሆን? ህመምተኛው ጤና ፣ ድሃው ሃብት ፣ ምሁሩ ዕውቀት ፣ እልቅና የሚሻው ሥልጣን ፣ የደከመው ደግሞ ዕረፍትን ይል ይሆናል በማለት ባሮውስ ማስተማሩን ጀመረ፡፡
ዓይነተኛውን የደስታ ምንጭ ምንነት አሁን ስነግራችሁ ቅር ትሰኙ ይሆናል ይላል ባሮውስ፡፡ የተለመደ ፣ በቅርብ ያለ ፣ ብዙ ሰዎች በእጃቸው ያስገቡት ፣ ግን አስደሳችነቱን ያልተገነዘቡት ጉዳይ ነው፡፡ ወይ ከአቅማቸው በላይ ሆኖባቸዋል፣ ወይ የሚጥማቸው ሆኖ አላገኙትም፡፡ ጅረት የሚሻው ዋነኛው ነገር ምንድን ነው? ሳያቋርጥ መንኳለሉን ይሆናል፡፡ ከተከተረ ጣጣ ይወስዳል፡፡ ሰውም እንዲሁ የማያቋርጥ እንቅስቃሴን ይሻል — የአካል ፣ የመንፈስ ፣ የጭንቅላት፡፡ ስለዚህ የደስታ ምንጩ ሥራ ፣ የሚጥም ሥራ ነው፡፡ ሰዎች ሁሉ ከሥራ ቢታገዱ ዓለማችን ምንኛ የሥቃይ ቋት በሆነች!
ሥራ የደስታ ምንጭ መሆኑን ፣ በእርሱም በመጠመዳቸው ህልውናቸውን ከመገዝገዝ መቆጠባቸውን የሚገነዘቡ በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ ደስታ የምትቀርበው አጥብቀው የሚሿትን ፣ ስለርሷ የሚያብጠለጥሉትን አይደለም — አመች ሁኔታን በመፍጠር እንጂ፡፡ መከተልን እንጂ መምራትን አታውቅም፡፡ ፊት ካለችም እርሷን ለመቅደም መሞከሩ አይበጅም፡፡
በሙሉ ልብ ተመስጦ ፣ ያለ የሌለ ኃይሉን በሚጥመው ሥራ ላይ የሚያውል ሰው ምንኛ የታደለ ነው! እያለ ባሮውስ የፍልስፍና አቅጣጫውን ጠቆመ፡፡
በምንወደው ሥራ ተጠምደን ደስታና እርካታን ማግኘት ከቻልን ሁላቸንም ስለፍቅር በገባን ጥልቀት እናሰባለን፡፡ እንደ ማንኛውም ማኅበራዊ ግንኙነት ሁሉ ለልብ ወዳጅነትም ዋናው መመሪያ ለመወደድ ከፈለክ ሰው ወዳድ ሁን የሚለው ነው፡፡ ፍቅርን ልትላበስ ከፈለክ ይላል ዴል ካርኒጊም በበኩሉ ብቸኛው መንገድ እንዲያፈቅሩህ መወትወትህን ትተህ ፍቅርህን ለግስ ፣ ፍቅርን ስትሰጥ ብቻ ነው ፍቅርን የምታገኘው፡፡
ደግነትና መተሳሰብ አስፈላጊ ባሕርያት መሆናቸው የተዘነጋበት ዘመን ከቶ አይገኝም፡፡ ስለራሱ ብቻ የሚያስብ ሰው ፣ ራሱን በራሱ የጠቀለለ ኢምንት ቋጠሮ ነው ያለው ሃሪ ፎስዲክም ይህንኑ እውነታ ከልብ በማጤን ነው፡፡
ብዙ ጊዜ ፍቅር ሰጥቶ መቀበል ነው ሲባል እንሰማለን፡፡ ለራስህ እንዲደረግልህ የምትሻውን ለሌላውም አድርግ የሚለው አባባል ፣ የሰዎችን ግንኙነት ከሚያዳብሩ ጥንታዊና ጊዜ የማይሽራቸው ድንጋጌዎች መኻል አንዱ ሲሆን ፣ በግብረ-ገብ መመሪያነቱ ዛሬም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ ኢመርሰን ጓደኛ ለማፍራት ጓደኛ ሁን በማለት ይህንኑ ሃቅ አስተጋብቷል፡፡
እንግዲህ ይህን ስናደርግ ማናችንም ስለ ነገ የተስፋ ወኔአችንን ከሌሎች ጋር ብንካፈል ምንኛ መልካም ነው፡፡ እርግጥ ነው እንደ ሲድኒ ዳርክ አባባል፤ ቀደም ያሉት አባቶቻችን የመኖርንና የመሞትን ምንነት አስተምረውናል፡፡ እኛም ወራሾቻቸው መሆናችንን አንዘንጋ፡፡ ወደ ጦር ግንባር የሚሄድ ወታደር ጦር ሜዳ መሞት እንዳለ ልቦናው ቢያውቅም እንኳን በድል ብስራት ዜና ከጓዶቹ ጋር እንደሚመለስ ያስባል፡፡ ተስፋ የትም አለ፡፡
ለህይወት አስፈላጊዎቹ ቁም ነገሮች ሥራ ፣ ፍቅርና ተስፋ ናቸው –ጆሴፍ ኤድሰን፡፡
(በኪራም ታደሰ)
(ግብአት ከሊሊያን ኤይችለር ውርስ በመንግሥቱ ወ/ማርያም)