የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ
የሼህ ሁሴን ጅብሪል ትንቢታዊ ግጥሞች (ክፍል - 08)

45 ቴዎድሮስ ለጋሥ ሰው ነው ቸርነት አያጣም
ዘሩም ደኅና ሰው ነው ቢገጥም አይወጋም
ማንም ያሞኘዋል ያሳዝናል በጣም
ለሰውም ደኅና ነው እስላምን አይጎዳም
እራቅ ይላል እንጅ የእስላም ዘር አያጣም::
ዮሐንስ ንፉግ ነው ሰው ቢበላ አይወድም
የሰው ያየ ጊዜ ያደርጋል ጉድምድም
ሆዱም ለብቻው ነው ሰው አያስቀርብም
ለጦር ግን ጀግና ነው ቢሄድ አይታክትም::
46. የጠንቋይ ውዴታ ፍቅር ይቅርብህ
ለአንተ ሲህር አያጣም ይኸው ነገርኩህ
ቢያጣ አርን አያጣም እንዳይጥልብህ
ስታልፍ እንድትረግጠው ሰው እንዲስድብህ
አሩ ይሸታል ብለው ሰው እንዳይቀርብህ::
47. አሥር ዓመት ብችል ሊያርዱኝ ተሰለፉ
ለካስ ለዚህ ነውይ እምቢ ያለኝ እንቅልፉ
ለአላህ ትቼው ነበር በዱኒያ እንዲያልፉ
እንግዲህ ዘላለም መሬትን ይቀፉ
በቶሎ ገላግለኝ ሰው እንዳያለፉ::
48. በእነ ቀለመወርቅ ነሱር ባላገኝ
በመምሬ ጉርሙ ነሱር ባላገኝ
በእነ አለቃ ሣህሉ ነሱር ባላገኝ
በእነ አለቃ ውብነህ ነሱር ባላገኝ
እኒህ ተዋርደው ነው ንጉሥ የፈራኝ::
49. በእለቃ ቀለመወርቅ ነሱር ባላገኝ
በእነ ይመር አደም ነሱርን ባላገኝ
በእነ አለቃ እዮብ ነሱር ባላገኝ
(በአውገረድ አለማሽ ነስሩን ባላገኝ)
ችለን ሰደድናቸው እንቅልፍ ቢነሱኝ::
50. ነግሬአቸው ነበር ፊት ሳልታመም
አሁንም አየሁት አላህ ሲፈርም
አፈሩን በጥብጦ በጥቁር ቀለም
ቃልቻ ይኸን ፈሥር እንዳትታመም
በቀር ትጓዛለህ አምተህ ሳትሰልም::
51. አላማጣን አልፈህ ማይጨው ትዘምታለህ
ነጭ አሥመራ መጥቶ አድዋ ትገጥማለህ
አድዋን እንዳያልፍ በጣም ትዋጋለህ
ጦርህ ግን ያልቃሉ ድል ግን ታደርጋለህ
በመከርኩህ ምክር ነጃ ትወጣለህ::
52. የሸዋረጋ እናት ሐለቴን ያውቃሉ
ሁሴን መጣ ሲባል ጋንዎን ያጥባሉ
ቄጠማ ጎዝጉዘው አዱርስ ያቀርባሉ
ደስ ደስ እያለዎት በጣም ይስቃሉ
መጋረጃ ጋርደው ቁጭ ብለው ያድራሉ::