• የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

"ቃል ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ" (በእሙ - ኢሳን)

Updated: Jun 9, 2019ቃል ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ ሲባል የቃልን ከባድነት ለመግለጽ ብቻ ሳይሆን ሰው የተናገረውን ወይም ቃል የገባውን ነገር መፈጸም እንዳለበት ለመግለጽ ጭምር ነው። በዱር ያሉ ፍጥረታት በሙሉ ለወለዱት ልጅ የሚያደርጉት እንክብካቤ እና እነርሱን ለማሳደግ የሚያደርጉት ትግልን ብንመለከት ያውም በእንሰሳኛው ባህሪ ያቺ… እናት ልጆችዋ በአውሬ እንዳይበሉባት የምታደርገው ፍልሚያ የሚያስደንቅ ነው። ወደ ሰዎች ባህሪ ስንመጣ ደግሞ ከእንሰሳዎች በእጅጉ የላቀ እና የገዘፈ ነው። ታዲያ ቃል ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ ሲባል ከወለዱት ልጅ ይልቅ ቃሉ ሰለሚልቅ ነው።

ከወራቶች በፊት በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አንድ የሃገር መሪ ንግግር ሲያደርግ አጽንኦት ሰጥቼ አዳመጥኩኝ። የሚገርመው ጠቅላይችን ንግግር ያደርጋሉ ከተባለ ቴሌቪዥን ስር የምገኘው የመጀመሪያው ሰው ሆኜ ተገኘሁ። ከዚህ ቀደም እንደዚህ ትኩረት ሰጥቼ እከታተል የነበረው ሐይማኖታዊ ትምህርት ሲሆን ብቻ ነበር።

ታዲያ እንዴት ትኩረቴን ሳበው ? ወይስ እንደሚባለው ሁሉም ሰው የእራሱን ምኞት የሚነግረው ሰው ሲኖር እና ፍላጎቱን የሚያሟላለት ሲያገኝ ደስ ስለሚለው ይሆን? ብቻ አላውቅም ሲናገሩ አዳምጣቸዋለሁ። በተለያዩ አጋጣሚዎች በተገቡትን ቃሎች አዲስቷን ኢትዮጵያን በአዕምሮዬ ሳልኳት። ነገ ከተሰደድኩበት ሃገሬ ስገባ ዘረኝነት ጠፍቶ ሁሉም የሰው ልጅ በሃገሩ ታፍሮና ተከብሮ በፈለገበት ቦታ በነጻነት ሲኖር ታየኝ። አንተ የዚህ ዘር ነህ! ከዚህ ቦታ ምን አመጣህ ሳይባል የወደደው እና የመረጠው ቦታ ላይ ሲኖርና ሰፋሪ ሳይባል የሚኖርበት መልካም ጊዜ ይመጣ ይሆናል በሚል እሳቤ።

ነገር ግን ዛሬ… ዛሬ የማየውና የምሰማው እንደ ተገባው ቃል አይደለም። ታዲያ ወደ ተግባር ያልተተገበረ ቃል ከቃል የዘለለ አይሆንም። ተግባር የሌለው ቃል ለድሃው ምን ያደርግለታል? ከዚህ በፊት የነበሩት የተከበሩ መሪ ቃላቸው ወደ ተግባር ሳይቀየር አልፈዋል። እርሳቸው ቢያልፉም ግን የሰሩት ገና ለሁለት ትውልድ ይተላለፋል። ጥቃቅኑን ትተን የገዘፈውን እንኳን ብናነሳ የዘር ፖለቲካ ጉዳይና የአባይን ግድብ ሁኔታ ማንሳት ይቻላል። ካለሁበት የስደት አለም ሁላችንም በመረባረብ ቦንድ ገዝተናል ሸጠናልም። ዛሬ ግን ያ…ሁሉ ቃል ወደ ተግባር ሳይቀየር በቃልነቱ ወደ አስረኛው አመት ይዘልቃል እየተባለ ነው። አሁንም ቃል ነው የተገባው መብራቷን አላየንም እንዲሁም የለመለመ አጎራባች አካባቢ እና የአሳ እርባታውም የለም። ብቻ ሁሉም “ላም አለኝ በሰማይ አይነት ነው”። ሌላኛው ሳንሻው ያሳቀፉን የዘር ፖለቲካ ጉዳይ ሲሆን ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት አመለካከቱ አንድ የሆነ ወይም በአንድ ስሌት ከአንድ ማሽን የተፈለፈለው እስኪመስል ድረስ የዘር ፖለቲካን ብቻ የሚያቀነቅን እና በሃሳብ ከመወያየት ይልቅ ስድብ የሚቀናው ትውልድ ሃገራችን አቅፋለች ።

ዛሬ ላይ እርሶን 100 ሚሊዮን የኢትዮጵያ የሚጠብቅዎት ቃሉን በቃል እንዲያስረክቡ አይደለም። ክብርነትዎ ተግባር ያስፈልገናል። በርግጥ አንቸኩልም። አንዘገይምም! ግን እንጠብቃለን ቸኩለን ከምናበላሸው ይልቅ ዘግይተን በውን የምናገኘው ይበልጣልና።

አሁን… አሁን የማየውና የምሰማው አላምርሽ እያለኝ ነው። ክቡርነትዎ ከገቡት ቃል አንዱ የጎዳና ተዳዳሪዎች ከጎዳና ህይወት ይላቀቃሉ የሚል ነበር ! የጎዳና ተዳዳሪዎች ከጎዳና ህይወት ይላቀቃሉ በተባለበት ወቅት ደስታዬን በቃላት መግለጽ ተስኖኝ ነበር። ሃገር ቤት በምገባበት ወቅት ስሜቴን ከሚነኩት ብዙ ነገሮች ዋነኛውና ትልቁ የጎዳዳና ተዳዳሪዎች ጉዳይ ነው። ሁሌ… እመኝ ነበር ባደረኩላቸው በማለት! ታዲያ ምኞቴ በመንግስታችን የተሳካ መስሎኝ ነበር። ይሁንና እነዚሁ ችላ ተብለው የነበሩት ወገኖቻችን ከመጠለያው ከመግባታቸው ገሚሶቹ ጎሎብናል ብለው ወደ ጎዳናው ህይወት መመለሳቸው ተሰማ ተነገረ። ሲውል ሲያድር በርካታ ወገኖቻችን ደግሞ ከሞቀ ጎጃቸው በህገወጥ ስም እና በአረንጓዴ ልማት ስም ለጎዳና መዳረጋቸውን ሳይ በእጅጉ አዘንኩመኝ። “አልሸሹም ዞር አሉ” ሆነብኝ! ባዶ ቃል! ወይስ የስራ ልምድ ልውውጥ ለማድረግ የጎዳናውን ወደ ቤት የቤቱን ደግሞ ወደ ጎዳና በማድረግ የሚተገበር ቃል። ወደጄ ሆይ ለሁሉም ነገር ህግ አለው። ምናልባት ህገወጥ ሰፋሪነት ሊኖር ይችላል። ያለፕላን ግንባታ ተመስርቶ ይሆናል። የእኔ ጥያቄ ግን ህግ አይከበር ለማለት አይደለም። ህገወጥነታቸው በህግ እንዲረዱት ከተደረገ በዃላ ወደ ጎዳናው ህይወወት ከመዳረጋቸው በፊት ሊደረግላቸው የሚችል ነገር መኖር ነበረበት በህጋዊ መንገድ ቤት እንዲገነቡ ወይም መንግስት በተመጣጣኝ ክፍያ የኪራይ ቤት ሊያዘጋጅላቸው ይገባ ነበር። በመንግሰት አካላት ግን ተፈጽሞ የተገኘው ቤታቸውን በሃይል በማፍረስ ወደ ጎዳናው ህይወት በመንግስት ህገ ወጥ ተግባር እንዲወጡ ሆኖ ነበር የተገኘው። ከህግ ይልቅ እኮ ሰው መሆን ሰውነት ይቀድማል። መንግስት ተብየው ከየት ያመጣው የእራሱ ይዞታ ሆኖ ነው ወይም የትኘው የተለየ መብት ኖሮት ነው ህዝብ እዳሻው የሚያደርገው? እንደ ህጉ ከሆነ መንግስት ህዝብ የሰየመው ህዝብን በእኩል እንዲያገለግል ያስቀመጠው ነው እንጂ መንግሰት የበላይ አካል አይደለም። በምድርኛው አስተሳሰብ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ከፈጣሪ በታች የበላዩ ህዝቦች ይሆነናል ብለው ያስቀመጡት ህግ እንጂ መንግስት አይደለም። የመንግስት ተግባር ህዝቦች በጋራ በአጸደቁት ህግ መሰረት ሁሉንም በእኩል ማስተዳደር ብቻ ነው። ህግን ተላልፈው የተገኙ የመንግስት አካል የሆኑና ያልሆኑ እንደ ህጉ ከሆነ በእኩል ነው የሚዳኙት። ስለዚህ መንግስት እንዳሻ ሊሆን አይገባውም። በህገ ወጥ ስም ቤት የፈረሰባቸው እንደ ዜጋ ወይም እንደ ማንኛውም ለአቅመ አዳም-ሄዋን የደረሱ ጎጆ መስርተው ልጅ አፍርተው መኖር ይሻሉ። በመስት የተበላሸ አፈጻጸም ምክንያት ደግሞ መሆን ከሚፈልጉት መታቀብ የለባቸው። የመኖሪያ ቤት በተመለከተ የተቀመጠ ደህና ህግ ኖሮ ቢሆን ህዝቡ ህግ ወጥ ቤት የሚገነባበቱ አካሄድ የመነመነ ይሆን ነበር። ህዝብን ከማፈናቀል ህጉን አስተካክሎ ህዝቡ እንደዜጋ በመብቱ የሚጠቀምበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት። በአንጻራዊው ለመንገስት አካላት የተፈቀደ እስኪመስል ድረስ በደሃው መበት ተጠቃሚዎቹ የመንግስት አካላት እና ቤተሰቦቻቸው ናቸው።

የመኖሪያ ቤት ግንባታን በተመለከተ የተሻሉ መፍትሄዎች በማበጀት እንዲሁም ሂደቶቹን መንግሰት ማፋጠን መቻል አለበት። ጎዳና ላይ ከወጡትና ከተፈናቀሉት አብዛኛዎቹ ሴትና ህጻናት ናቸው። በየትኛውም ችግር ደግሞ የመጀመሪያ ገፈት ቀማሾች እኒሁ ሴቶች ናቸው። ምነው…? ወዳጄ የሹመቱ እለት እኮ ከሁሉም በፊት ሴትነቱ ከፍ…ከፍ ተደርጎ እንደነበር የቅርብ ግዜ ትውስታች ነው። ለሴቶች ተሰጥቶ የነበረው ክብርም ደግሞ ምነው? ዛሬ ላይ ቃል ብቻ ሆነ። ስለዚህ እየተስተዋለ ከቃል የዘለለ ተግባር እንዲሆን ይሁን።

በ2011 ዓም የሚያዝያ 23 የሙስሊሙ ማህበረሰብን ወደ ፍጹም አንድነት የወሰደው ክስተት ደግሞ ቃሉ ተግባር የሆነበት እለት ነበር። ለዚሁም በመጀመሪያ ፈጣሪያችን የተመሰገነ ይሁን! በመቀጠል ለማስማማት ቆርጠው ተነስተው የነበሩት ጠቅላይ ሚስትራችን እንደዚሁ የተመሰገኑ ይሁኑ! በመሰለስ የተስማሙት አካላት እና ህዝበ ሙስሊሙ የተመሰገኑ ይሁኑ!

ሁሌም… ቢሆን ቃሉ ይተግበር!

“ተቀባብቶ ከቀረበው ቃል ይልቅ ተሰርቶ የሚታየው እውነት ይበልጣልና”።

እሙ ኢሳን

ሪያድ ሳዑዲ አረቢያ


42 views0 comments

Copyright © 2018 Meskan Media Network - All Rights Reserved. E-mail : meskanmedia@gmail.com

  • YouTube - White Circle
  • White Spotify Icon
  • White Apple Music Icon
  • White Amazon Icon
  • White Facebook Icon
  • Twitter Clean