top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የቡታጅራና ከተማ እና የአልከሶ ከተማ "ታሪክ ጠገብ መስጂድ"


የእስልምና ሃይማኖት ክዋኔዎችን ለዘመናት ያስተናገዱ ጥንታዊ መስጂዶች በመስቃን ቤተ-ጉራጌ ቡታጅራና ከተማ እና በስልጤ - አልከሶ ከተማ

ኢትዮጵያ ሀገራችን ከጥንት ጀምሮ ለረጅም ዘመናት የክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች አብረው በመቻቻል፤በመከባበር እና በፍቅር የሚኖሩባት ሀገር ናት፡፡በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከመቼውም ጊዜ በላይ የህዝቦች በነጻነት አብረው እኩል እንዲኖሩ የሚያስችል ህገ-መንግስት በመረጋገጡ የሃይማኖቶችም ነጻነት እንዲሁ ሊከበር ችሏል፡፡ ክልላችን ደግሞ ብዝሃ የባህል እሴቶች፤ቋንቋዎች ትውፊቶች ባለቤት እንደመሆኑ መጠን በተረጋገጠው የእምነት እኩልነትም የተለያዩ የእምነቶቻቸውና የባህል ክዋኔያቸውን የሚያንጸባርቁበት ስፍራም አሏቸው፡፡ከእነዚህ ስፍራዎች ውስጥ ጥንታዊ የእስልምና ሃይማኖት ክዋኔዎችን በማስተናገድ ወደሚታወቁ ሁለት መስጂዶች ሁለት ሆነን ለመቃኘት አመራን - ወደ ጉራጌ ዞን ቡታጅራ ከተማ እና ወደ ስልጤ ዞን አልከሶ ከተሞች፡፡ በአጭሩ እንዲ ተመልክተነዋል መልካም ንባብ፡፡

የመጀመሪያውን ጉዟችንን ከሀዋሳ ተነስተን በዝዋይ በኩል ወደ ቡታጅራ ነበር ማልደን -ያደረግነው፡፡ጠዋት ረፈድፈድ ሲል ወደ ታላቁ የቡታጅራ መስጂድ አመራን፡፡ያለወትሮው የመስጂዱ ቅጽር ግቢ ጭር ብሏል፡፡ዙሪያውን ብንቃኝ አልፎ አልፎ ትንንሽ ታዳጊ ልጆች ናቸው የሚታዩን፡፡በመሆኑም ማን እንደሆን እና ምን እንደምንፈልግ ላጋጠሙን ታዳጊዎች በመግለጽ ወደ አንድ አዛውንት ጠቆሙን፡፡ እንዲተባበሩን ጠይቀናቸው በተንጣለለው የመስጂዱ ቅጽር ግቢ ውስጥ ከአንድ ጉብታ በሳር የለመለመ ስፍራ ላይ አረፍ ብለው ማውጋት ጀመሩ ኡስታዝ አህመድ ኢብራሂም፡፡


የቡታጅራና ከተማ እና የአልከሶ ከተማ "ታሪክ ጠገብ መስጂድ"

ጊዜው በውል ባይታወቅም አሁን ከሚገኘው የቡታጅራ ትልቁ መስጂድ በፊት የአካባቢው ነዋሪዎች እስልምና እምነትና ተዛማጅ ማህበራዊ ክዋኔዎችን የሚያዘወትሩበት መጠነኛ ቤት በዚሁ ስፍራ እንደነበር ይናገራሉ - ኡስታዝ አህመድ ኢብራሂም፡፡በዚሁ መስጂድ ውስጥ ከሰላሳ አመታት በላይ አገልግለዋል፡፡ታዲያ ይህንን መስጂድ ማን መቼ እንደቆረቆረ ይንገሩን አልናቸው፡፡ቦታውን የያዙት የሼህ ኢሳቅ አጥባሪ አባት ሼህ ሀምዛ ናቸው ፡፡ድሮም ግን አነስተኛ የቆርቆሮ ቤት እንደ መስጂድ ያገለግል ነበር፡፡ከዛ ቦሃላ ግን እን አብዱራህማን ሸሪፍ፤እነ ሻለቃ ሱልጣን ኢብራሂም እና ሌሎች ናቸው የአካባቢውን ነዋሪዎች በማስተባበር በህዝብ መዋጮ እንዲቆረቆር ያደረጉት፡፡ ይህ የዞኑ ታላቅ መስጂድ በተለየ የዘመኑ ምህንድስና ውጤት ግንባታው የተጀመረው በ19 69 የተጀመረ ሲሆን የተጠናቀቀው እና ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው በ19 73 ዓ.ም ነው፡፡ በወቅቱ ለእስልምና ሃይማኖታቸው ቀናኢ የነበሩ የጉራጌ ተወላጆች በኮሚቴ ደረጃ በመደራጀት እስከ ጠቅላይ ግዛት ከዚያም ወዲህ እስከ ክ/ሃገር ድረስ በመዘዋወር ህዝቡን ሊያስተባብሩና መዋጮ ሊያሰባስቡ ችለዋል፡፡እንግዲህ እንደእሳቸው አገላለጽ በንጉሱ ዘመን እና በደርግ የነበሩ ስያሜዎችን ነው - ጠቅላይ ግዛት እና ክፍለ ሃገር ማለታቸው፡፡ የሆኖ ሆኖ ይህ ቡታጅራ መስጂድ ከአምስት ዓመታት የግንባታ እና የአካባቢውንና የሌሎችን ፈቃደኛ የእምነቱ ተከታዮችን በማሰባሰብና ያላቸውን እንዲያዋጡ በማድረግ አነሆ እስከ ዛሬ ድረስ ከዞኑ ባለፈ የሃገር እና የክልላችን አንዱ ታላቅ ቅርስ ሆኖ ሊቆየን ችሏል፡፡ ለዘመናት በመስጂዱ ውስጥ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ተሰባስበው ፈጣሪያቸውን /አላህን/ እሚያመሰግኑበት እና ሚለማመኑበት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ግንባታው ውበት ያለው እና በአራት ወጋግራዎች ብቻ በመሰራቱ ለየት ያደርገዋል፡፡እንደሳቸው አገላለጽ የቡታጅራን መስጂድ የሚያህል እና የሚመሳሰል እንደውም አይገኝም - ቢኖር እንኳን ከአንድና ሁለት አይበልጥም ፡፡ የእምነቱተከታች ሶላት የሚሰግዱበት ማለትም የወንዶቹ ብቻ ሰላሳ ሜትር በሰላሳ ሜትር ማለትም በዘጠኝ መቶ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ነው፡፡ ለሴት የእስልምና እምነት ተከታዮች የሚሆነው ደግሞ ምድር ቤት ሆኖ በተመሳሳይ ሰላሳ ሜትር በሰላሳ ሜትር ቁመትና ስፋት የተሰራ ነው፡፡ነገር ግን አቻ የለውም መባሉ በስፋቱ ሳይሆን በፎርሙና በቅርጹ ነው እንደ ኡስታዝ አህመድ ኢብራሂም አገላለጽ፡፡

ይኸው የቡታጅራ መስጂድ እንደ ሌሎቹ ተመሳሳይ መስጂዶች እንደ አሁኑ እንዲቆም ወጋግራዎች ሳይበዛበት - በአራት ወጋግራዎች / ምሰሶዎች/ ብቻ መታነጹ ይለየዋል፡፡በውስጡ ሶላት ለመስገድ ብቻ ያለምንም መጣበብ በአንድ መደዳ ብቻ ሰባ የሚሆኑ የእምነቱ ተከታዮችን ያስተናግዳል ፡፡ ወደ ውስጥ ገብተው ሲመለከቱት ጣራው በውብ ስኴር ስኳር በሆኑ ቅርጾች በነጭ ቅብ ተዥጎድጉዶ ይመለከቱታል ፡፡ ወለሉም ሆነ ጣራው በጣም ጽዱ በመሆነቸው ቅርሱ ውበትን እንደጠበቀ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊተላለፍ እንደሚችል ምንም ስጋት አይኖርም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እኛንም የገረመን በእስልምና እምነት መሰረት ወደ መስጂድ ቅርሱና አካባቢው ተጠግቶ እንኳን ለመቃኘት መጫሚያን ማውለቁ ግድ ነው፡፡ግድግዳዎቹ ብርሃን አስገቢ በሆኑ መስታዎቶች ተሸቆጥቁጠው አልፎ አልፎ በሰማያዊ ቀለም ተውቧል፡፡መካከል ላይም ጣሪያው በክብ ቅርጽ ወደ ላይ ሰፋ ተደርጎ እንዲሁ ሰማያዊ ቀለም ተውበዋል፡፡ ዙሪያውንም በመስታወት በመታነጹ እንኳን ለእምነቱ ተከታዮች ለማንኛውም ሰው ሲመለከቱት ሀሴትን የሚሰጥ ብርሃናማ እና ጽዱ ነው፡፡ የውስጥ ምሰሶዎቹም ቢሆኑ ግርጌያቸውን ቢጫ ከመቀባታቸው በስተቀር እንዲሁ ሃጫ ነጭ በረዶ በመሰለ ቀለም ተቀብተዋል፡፡ መስጂዱ በአሰራር ፎርሙ የተለየ ሆኖ በመሰራቱ እና በርካታ የእስልምና እምነት ተከታዮችን ለእምነታቸው ክዋኔዎች አገልግሎት በመስጠቱ እንዲሁም ከአዲስ አበባ በቅርበት የሚገኝ በመሆኑ በብዙ ሰዎች ዘንድ እውቂያ እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡በውስጡም በአረብኛ የተጻፉ ቁርአንና ክታብ የመሳሰሉ የእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮዎችን የያዙ መጽሃፍቶች ይገኙበታል፡፡አሁንም ግን የተለያዩ የእስልምና ዕምነት የሚጠይቃቸውን ሃይማኖታዊ አገልግሎቶችን ሚሰጥ ሲሆን ለታዳጊ ህጻናትም ሰኞ እና አርብ ሲቀሩ በሳምንቱ ቀናት በሙሉ የቁርኣን ትምህርት ይሰጥበታል፡፡ወደ መስጂዱ አልፎ አልፎ የውጭ እና የሃገር ውስጥ ጎብኚዎች ሲመጡ ይስተዋላል፡፡እኛ ከስፍራው ስንደርስም ጭር በማለቱ ወቅቱ ወርሃዊው የሊቃው /መሰብሰቢያ/ በመሆኑ ይህ ክዋኔ ወደ ሚካሄድበት ስፍራ የአካባቢው የእምነቱ ተከታዮች ሄደው ዱአ /ጸሎት/ እያካሄዱ መሆናቸውን ነግረውን ወደ ስፍራው ታክሲ/ባጃጅ/ በመኮናተር አቀናን፡፡ ከዋናው የተሸከርካሪ መንገድ ወደ ውስጥ በግምት ስድስት ኪሎ ሜትሮችን በእግር መጓዛችን ግድ ነበር፡፡ አቀበት ቁልቁለት እና አነስተኛ ወንዝ ተሻግረን ከተንጣለለው ሜዳ ደረስን፡፡ሜዳው በሙሉ በእልምና እምነት ምእመናን ተጥለቅልቋል፡፡ ሁሉም በያለበት ተቀምጦ ፈጣሪውን ይለማመናል -ዱአ ያደርጋል፡፡መረጃ ሊሰጡን የሚችሉ አዛውንት በማፈላለግ ሀጂ ኢብራሂም እንዲሪስ የተባሉ በሊቃው /በመሰብሰቢያው/ ትልቅ ድንኳን ውስጥ በመዝለቅ መወያየት ጀመርን ፡፡ ስለ ታላቁ የቡታጅራ መስጂድ ታሪክ ስንጠይቃቸው ቀደም ሲል ከዘረዘርነው የተለየ አልነገሩንም - ከዚያ ይልቅ በጣም የሳበን የእስልምና እምነት ተከታዮች ተሰባስበው ስለሚያከናውኑት ባህላዊና እምነታዊ ማህበረ ክዋኔ መጠየቅን መረጥን፡፡ ስፍራው ለእንደዚህ አይነት አገልግሎት የተመረጠበት ወቅት በውል ባይታወቅም እንደሳቸው አባባል ከአጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ቀደም ብሎ ነው፡፡ ከጠዋት ጀምሮ ለጸሎት በስፍራው በመሰባሰብ አላህ ይለመናል፡፡ ጤና ሰላም እና ጥጋብ ወይም አዝመራ ምርት እንዲሰጥ የዚህ ስፍራ ተሰብሳቢ ለጀማው /ለስብሰባው/ ያለውን እየለገሰ እስከ አስር ሰዓት ድረስ ይቆይበታል፡፡ በዞኑ ለእንዲህ አይነቱ ሃይማኖታዊ ክዋኔ በጀማነት 18 ስፍራዎች ያሉ ሲሆን አንዱ በዙር የሚደርሰው ከዓመት ከመንፈቅ በኋላ መሆኑንም ነግረውናል፡፡እኛ ምንም እንኳን የእስልመና እምነት የሚዘወተርበትን ጥንታዊ መስጂድ ቅኝት ላይ ብንሆንም ጥንታዊና ፈጣሪን /አላህን/ መለማመኛ የሊቃውንም ስፍራ በጨረፍታ መመልከት ችለናል፡፡ሁሉም የእስልምና እምነት ተከታይ የጀማው ተሰብሳቢ በአስር ሰላት ስግደት በኋላ ወደ መጡበት አካባቢዎች ይመለሳሉ፡፡


የቡታጅራና ከተማ እና የአልከሶ ከተማ "ታሪክ ጠገብ መስጂድ"

ቀጣይ ጉዟችንን ወደ ስልጤ ዞን አነስተኛዋ አልከሶ ከተማ ሆነ - ጥንታዊውን የአልከሶ መስጂድን ለመቃኘት፡፡ ይህች አነስተኛ ጥንታዊ ከተማ ከዞኑ ዋና ከተማ ከስልጤ በስተሰሜን ስምንት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ የአልከሶ ጥንታዊ መስጂድ ከወረዳዋ አልከሶ ከተማ 3.8 ኪሎ ሜትር ወደ ውስጥ ገባ ብሎ የሚገኝ ነው፡፡ ፀሃይ እየበረታች ቢሆንም ወደ መስጂዱ የምናደርገውን ጉዞ ሚገታን ባለመሆኑና ወደ ቅርሶችና ሌሎች የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ጉዞ በማድረግ ልምዱ ያለን በመሆኑ በአካባቢው በመሰብሰብ ላይ ሚገኘውን ሰብል እየቃኘንና ወጋችንን እያወጋን ቀጥለናል፡፡በመንገዳችን ላይ የስልጤ አካባቢ ነዋሪዎች ጥንካሬን በሴቷም በወንዱ ልንመለከት ችለናል፡፡ ራቅ ካሉ አካባቢዎች ምርቶቻቸውን በጋማ ከብቶቻቸው ጀርባ ላይ ጭነው ከእንሰሶቹ እኩል በፍጥነት ሲሄዱ እንግዳ መሆናችንን ለመገመት ባለመቸገራቸው ‹‹ሰላም አለይኩም›› ሳይሉን እና እኛም ‹‹ዋአለይኩም ሰላም›› የሚል ምላሽ እየሰጠን በእንግዳ ተቀባይ ፈገግታቸው እየተማረክን ከስፍራው ደረስን፡፡ የስልጤና አካባቢዋ የጥንት ነዋሪዎች ለእምነታቸው ማህበራዊ ክዋኔ በወቅቱ መስራች የነበሩት አልከስዬ በመረጡት ቦታ በ1935 ዓ.ም በዚህ ስፍራ ጉልበታቸውን አስተባብረው ከአሁኑ ሃላባ ልዩ ወረዳ ድረስ በእግር በመጓዝ ይህንን ቅርስ እስከ አሁን ሊያቆዩል ችለዋል፡፡ በቅጽር ግቢውና በዙሪያዎቹ የተለያዩ ጥንታዊ ቤቶች ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲውሉ ተሰርተው ይገኛሉ፡፡ ስፍራውምረባዳማና ነፋሻማ በመሆኑ ጸጥታ የሰፈነበት ነው፡፡ እኛም በፀሀይ ተጉዘን በመድረሳችን አረፍ ማለትንና ውሃ ጠጥተን ወደ ውይይታችን እንድንገባ ፈቀድ ጠይቀን ጀምረናል፡፡ የመስጂዱ ኢማም /የእምነቱ ተከታዮችን የሚመሩ/ ሼህ አብራር ሃይደር ጋር በአልከስዬ መስጂድ ስር ተቀምጠናል፡፡ ካለንበት ስፍራ ብዙም ያልራቁ ታዳጊ ህጻናት ከአንድ ዛፍ ጥላ ስር ተሰባስበው ቁርዓን በመማር ላይ ናቸው፡፡መረጃ ሰጪያችንን ሼህ አብራር ሃይደርን እና እኛን ሌሎችም በመስጂዱ ግቢ የሚገኙ ተቀላቅለውናል፡፡ መስጂዱ በዚህ ስፍራ ላይ እንዲሰራ ምክንያት የነበረው በወቅቱ መስራች የሆኑት እና በስማቸው የተሰየመላቸው አልከስዬ በእስልምና ሀይማኖት መሰረት አላህን እየለማመኑ ለአካባቢው ነዋሪዎች እና ለሌሎች በርካታ ሃይማኖታዊ በጎ ተግባራትን በማከናወናቸው ነው - ይላሉ ሼህ አብራር ፡፡

ህዝቡም በስፍራው እየተገኘ አልከስዬ አላህን እንዲለማመኑላቸው እና ከደረሰባቸው ችግር መላቀቅ እንዲችሉ በመፍቀዳቸው ማዘውተር ጀመሩ፡፡ ከዚያ በኋላ ነበር አላህ አዞኛል እና ራቅ ባለው በሃላባ ልዩ ወረዳ ጎልጆ ወደ ተባለ ስፍራ ሄዳችሁ ጠንካራ የጥድ ምሰሶ አምጡ በማለት አልከስዬ ለአካባቢው የእስልምና እምነት ተከታዮች ሃይማኖታዊ መሰል ትዛዝ ያስተላለፉት፡፡

ነዋሪውም ይንን ሰምቶ በእግር ወደ ተባለው ስፍራ አቀና፡፡ይሁንና ግን በመከራ ሁሉም ተባብሮ በገመድ በመጎተት ይዞት የመጣው ወፍራም የጥድ ምሰሶ አልከስዬ አላህ አሳይቶኛል ያሉት ሳይሆን ቀረ፡፡ይህም ረጅምና ጠንካራ ለምሰሶ እንዲሆን ታስቦ በአካባቢው ነዋሪዎች በገመድ ተጎትቶ የመጣው እንጨት እስከ አሁን ድረስ የኋልዮሽ ያንን ዘመን እንድናስታውስ እያደረገ በግቢው ውስጥ ለዘመናት ተነጥፎ ይገኛል፡፡

ረጅሙ ለምሰሶ የታሰበው እንጨት በዛ ሁሉ ጉልበት መጥቶ ያለምንም አገልግሎት ይህን ያህል ጊዜ በግቢው ውስጥ ተጋድሞ መተኛቱ በውስጡ ቁጭት አንዳለበት አድርገን እንድናስብ ጋባዥ ነው፡፡


የቡታጅራና ከተማ እና የአልከሶ ከተማ "ታሪክ ጠገብ መስጂድ"

አልከስዬ ዋናው ምሰሶ እሱ እንዳልሆነ ለአካባቢው ነዋሪዎች እንደገና ሌላ እንዲያመጡ እዚያው ሆነው የተመለከቱ መሆናቸውን ሼህ አብራር ነግረውናል፡፡ በመሆኑም እዚያው ተመልሰው ወደ ሀላባ ልዩ ወረዳ በመጓዝ የአሁኑን ስፋቱ ብቻ ሶስት ሜትር የሆነ ጠንካራ የጥድ ምሰሶ በገመድ በመጎተት አመጡ፡፡ ለመስጂዱ ግድግዳ የሚሆኑት ደግሞ እያንዳንዳቸው በስምንት ሰዎች ጉልበት ከፊት አራት ከኋላ ደግሞ እንዲሁ አራት በመሆን በሸክም ሊመጣ ችሏል፡፡ለዋናው ምሰሶ መቆሚያ ወደ ውስጥ ጥልቀቱ ሁለት ሜትር ተቆፍሮ በጥበብ እንዲቆም የተደረገ ነው፡፡ ዙሪያውን እስከ 28 የሚደርሱ ምሰሶዎች ሲኖሩ በውስጥ በኩል ደግሞ ከዋናው ምሰሶ ጋር ተያይዘው ወደ ግድግዳ የተሸገሩ ድጋፍ ሰጪዎች 16 ምሰሶዎች ይገኛሉ፡፡ የመስጂዱ ጥንታዊ የአሰራር ዘዴንም ለቃኘ የስልጤን ህዝብ የጥንታዊ የቤት አሰራር ጥበብን ያስተውላል፡፡ እንዲሁ በተመሳሳይ በጥበብ ታግዘው የተደጋገፉ ምሰሶዎችንም ለሚመለከት ድንቅ ጥንታዊ የአካባቢው ነዋሪዎችን ጥበበ-ክህሎትን በአግራሞት እንዲደመም ጋባዥ ናቸው፡፡በቅርቡ ደግሞ ይህንን የአልከሶ መስጂድ ቅርስነትን እንዳለ ለመጠበቅ ተጨማሪ ስምንት የብረት ምሰሶዎች ድጋፍ እንዲሆኑ ተደርገው ተሰርተዋል፡፡

ይህ ጥንታዊ መስጂድ ቅርስ በ19 35 ዓ.ም ተጀምሮ በ19 41 ዓ.ም እንደተጠናቀቀ ሼህ አብራር አውሰተውናል፡፡እንደውም የመስጂዱ ጥንስስ እንጨቶቹን የማምጣት ተግባራት ከ19 33 ዓ.ም ቀደም ብሎ የተጀመረ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡ታላቅ ዓመታዊ የእስልምና በዓል ከረመዳን በዓል 15 ቀናት ቀደም ብሎ ሲከበር ከመላው ሀገሪቱ የእምነቱ ተከታች ተሰባስበው በመምጣት በደማቅ ሁኔታ

ያከብሩታል፡፡ ምንም እንኳን ይህ በዓል በዚህ ቀን ለዘመናት በደማቅ ሁኔታ የሚከበር ቢሆንም ጥንታዊ መስጂዱ ገን በቀን አምስት ጊዜ ሶላት የሚሰገድበት እና በየወሩም ሃይማኖታዊ ፈጣሪን /አላህን /ተሰባስቦ የመለመን ስርዓትም ይከወንበታል፡፡ እስከ አሁንም መስጂዱን አምስት የሚሆኑ የእምነት አባቶች በማስተዳደር አልፈዋል በማለት ሼህ አብራር በትውስታ ይናገራሉ፡፡ ዘወትር በመስጂዱ ቀሪ ዘመንን ፈጣሪ /አላህ/ የፍቅር፤የመቻቻል እና የጤና እንዲሆን በመመኘት ለሃገራችን ህዝቦች በእምነቱ መሰረት ዱአ /ጸሎት/ ጭምር የሚደረግበት ነው፡፡ በመስጂዱ የቁራን ትምህርትም ከዚሁ እምነታዊ ስርዓት ጎን ይሰጣል፡፡ በውስጡ የእስልምና ዕምነት አስተምህሮትን የያዙ ከዋናው ቁርዓን ጀምሮ ሌሎችም ጥንታዊ የጽሁፍ ቅርሶችም ይገኛሉ፡፡የግድግዳ ላይ ጽሁፎችን ጨምሮ ዘመናዊ አውቶማቲክ በአረብኛ እና በእንግሊዝኛ ተጽፎ የመስጂዱን የሙቀት መጠን፤የሶላት መስገጃ ጊዜያቶችን፤ሰአትን ወዘተ. መረጃዎችን የያዘ የግድግዳ ዛይ ጌጥ መሳይ መገልገያ ቁሶችን ሲመለከ የስልጤ አካባቢ ነዋሪዎችን ለእምነታቸው የሰጡትን ትኩረት

ያዩበታል፡፡ ግድግዳዎቹ የተለያዩ የእምነቱ ጥቅሶችን የያዙ የአረብኛ ቋንቋ የቅርስ ጌጦች ይታዩበታል፡፡ ውስጡ በምንጣፍ ያሽቆጠቆጠም ነው፡፡ የተለያየ መጠን ያላቸው የጥንታዊ እስልምና እምነት ንብረቶች ማስቀመጫ መደርደሪያዎችም ይገኛሉ፡፡ ጥንታዊ የእስልምና እምነት ማህበራዊ ክዋኔዎችን ለዘመናት ያስተናገዱ እና እንዳሉ ለቀጣዩ ትውልድ እስከዛሬ ድረስ የቆዩ የጉራጌ ዞን የቡታጅራውን መስጂድ እና የስልጤ ዞን የአልከሶ መስጂድ ቅኝታችንን ስንቋጭ ቀጣዩ ትውልድም እንዲንከባከባቸው እና እንዲጠብቃቸው ከአደራ ጭምር በማሳሰብ ይሆናል- ቸር እንሰንብት፡፡

ምንጭ - ደ/ብ/ብ/ህ/ ክልል መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ


163 views1 comment
bottom of page