top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

"ደብቀኝ"


"ደብቀኝ"

“መቼም ዘንድሮ በጥቅስ የማንግባባበት ደረጃ ላይ ደርሰናል!” ያለው ወዳጄ ማን ነበር?ዛሬ ዛሬ: አምላክ በምህረቱ በእድሜያችን ላይ የሚጨምርልን እያንዳንዱ ቀን ይዞብን የሚመጣው ጆሮ ጭው የሚያደርግ፡ ግራ የሚያጋባ፡ የሚያስደነግጥ አልፎም ተስፋ የሚያስቆርጥ እየሆነ ከመጣ ሰነባበተ:: አንዱን ስንለው አንዱ ፡ በአንዱ ጉድ ግራ ተጋብተን ሳናበቃ ሌላ ጉድ ዱብ ይልና አእምሯችንን ሲያስጨንቅ ፡ በየማህበራዊ ድህረ ገጹ በቃላት ሲያደባድበን: በጥቅስ ሲያጨቃጭቀን ይከርማል:: አንዳንዴ የነገሩን መሰረታዊነትና ጥቅም ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ከግንዛቤ ውስጥ የሚያስገባውም ያለ አይመስለኝም :: ከያቅጣጫው የሚሰነዘረው ሃሳብ ጽንፍ እጅግ ከመራራቁ የተነሳ ጭብጡን ለማግኘት መሞከር አእምሮን ከፉኛ መፈተን ፡ ራስ ላይ እብደትን መጋብዝ ነው:: ብቻ በእያንዳንዷ የጸኃይ ብስራት ጆሮ ከስጠነው ጆሯቸንን ጭው ለማድረግ ፣ ልባቸንን ለማዛል ፣ ነፍስና ስጋችንን ለማስጨነቅ ታጥቆ የሚወጣ አዲስ ርእሰ ጉዳይ አልጠፋ ብሏል::

ድሮ ድሮ ከወገኖች ጋር ሻይ ቡና እያሉ በተለያዩ መንፈሳዊ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየት በጣም አስደሳችና የሚያንጽ ነበር:: ዛሬ ግን ሰብሰብ ብለው የሚወያዩ ወገኖች መሃል እግር ጥሎዎት ከተገኙ መነሻና ግቡ በቅጡ የማይለይ ፡ ምላሰና አእምሮን የሚያደከም; በመጨረሻም የሚያስተዛዘብ ውይይት አይሉት አተካሮ መሃል ራስዎን ያገኙታል:: “የጉድ አገር ገንፎ እያደር ይፋጃል” እንዲሉ!ሁሉም የራሱን ጽንፍ ለማጽናት የመጽሃፉን ጥቅሶች ከየገጹ እየፈለቀቀና እንደምንም እያስገባ አተካሮው ይከራል:: ሁሉም ለራሱ ልክ ነው:: አቤት ጸጉር ስንጠቃው፡ አቤት ከግራ ከቀኝ የሚለጋው የጥቅስ ኳስ ፡ ጎሉ የቱ ጋር እንደሆን አይታወቅም: ብቻ ያገኙትን እየያዙ ወዳገኙት መለጋት:: “ አሃ! ለካ እንደዛ ነው?!” ብሎ ከነበረበት አቋም ሸርተት ብሎ የሃሳብ ልዩነቱን በትንሹም ቢሆን ለማጥበብ እጅ የሚሰጥ የለም:: ጊዜ ካልገደበው ማብቂያ ያለው አይመስልም:: መነሻው ሃሳብ ምን ነበር? እኔንጃ ፡ መድረሻውስ?እኔንጃ ፡ ግቡስ?እኔንጃ::

የሚያስጨንቅ ዘመን ይመጣ ዘንድ ግድ እንደሆነ ባውቅም: በዚህ መልኩ ይሆናል የሚል ግምት አልነበረኝም:: የትምህርቱ ንፋስ እንደ ብርቱ አውሎ ንፋስ እያስገመገመ ድንገት በመልክ በመልኩ መጥቶ መሃከላችን ተገኝቷል:: አቤት ሰንቱን አጥር ናደው፣ ስንቱን ቤት አፈረሰው ይሆን? ቤት ይቁጠረው:: የአመለካከት ልዩነቶች በነፍስ ወከፍ እየሰፉ መሄዳችው “ ወቸ ጉድ እንደው አንድ የሚያግባባን ነገር ይጥፋ?” ያሰኛል:: ነገሩ እኮ አንድ የሚያደርግ ነገር ጠፍቶ ሳይሆን የሁሉ ትኩረት ልዩነቱ ላይ ስለሆነ ይመስለኛል:: አንዱ ከሌላው በተሻለ መልኩ የሚያስብ መሆኑን ለማሳየት የኔ እበልጥ የኔ እበልጥ ትንቅንቅም ይመስላል:: ብቻ “ አሁን ይሄ ሃሳብ የት ያደርሳል ? ፋይዳው ምንድነው? ጥቅም እንኳን ቢኖረው ጥቅሙ ከባከነው ጊዜ አንጻር ብሎም ከዘላለም ህይወት አንጻርና ከሃይማኖት አላማና ግብ አንጻር ሚዛን ላይ ሲቀመጥ ምን ይፈይዳል?ያሰኛል:: እንዲህ ያለው አተካሮ በሰዎች ላይ የሚፈጥረው በጎ ያልሆነ ተጽእኖና የሚዘጋውን የወንጌል በር ነገሬ የሚለውም ያለ አይመስልም::

እንደውም ሳስበው ጠላታችን ሰይጣን ስብሰባ ተቀምጦ ለእያንዳንዱ ቀን የሚሆኑ ላያግባቡ ይችላሉ ያላቸውን ጥቃቅንና ፋይዳ ቢስ ርእሰ ጉዳዮቸ መድቦ እያገዘፈ ያቀብለናል:: እኛም በደስታ ተቀብለን አዋከበን አዋክበን ተሰዳድበን ተዘላለፈን ሳናበቃ የሚቀጥለውን ርእሰ ጉዳይ እንካችሁ ይለናል:: አይናችን ታውሮ አተካራችንን ስናደራ ጠላት ያለከልካይ የሃይማኖት ተቋም ጉልበትና አቅም ያዳከማል:: አብዝተን የፈጣሪን ፊት በመፈለጊያችን በዚህ በዘመን ፍጻሜ ከሊቅ እስከደቂቅ እገሌ ምን አለ? እገሌ ለገሌ ምን ምላሽ ሰጠ? ብለን በማህበራዊ ድህረ ገጾች ላይ አይናችንን ሰክተን ቀናት ተፈራረቁ:: ጌታ እንደሚመጣ ለሁሉ ምስጋናውን እንደሚገባው እንደሚከፍል እየረሳን እኛው ፈራጅ፣ እኛው ዳኛ፣እኛው አጽዳቂ ፣ እኛው ኮናኝ ሆንን:: ሁሉ ነገር እንደው እንደፈቀደው ይሁን ፣ አንነጋገርበት ተከድኖ ይብሰል ባልልም ፡ ግን በዛ! አንዳንዱ ጉዳይ የሚሰጠው ቦታና ጊዜ ያህል ለሰው ህይወት ፋይዳ ይኖረው እንደው ራሴን ስጠይቅ ምላሹ ግራ ያጋባኛል::

ታዲያ ሰሞኑን “ ጌታ ሆይ ይህን አስጨናቂ ዘመን እንደው እንዴት ይሆን ምናልፈው?” ብዬ ስጨነቅ አንድ እናት ወደልቤ እየመጡ ሰነበቱ:: ጌታ በእኝህ እናት የአንድ ወቅት ትዝታ ልቤን ደገፈው:: እናማ መላ አልባ ለነበሩት ግራ መጋባቶቼ መላ አገኘሁላቸው:: እኝህ እናት ወ/ሮ አበበች ይባላሉ:: ትክክለኛውን እድሜያቸውን መናገር ባልችልም በትዳር ከ ሃምሳ አመት በላይ ኖረዋል: እየኖሩም ነው:: ስምንት ልጆች አሏቸው፣ ባልሳሳት ከአስራ አምስት የማያንሱ የልጅ ልጆችን አይተዋል:: ከላይ የጠቀስኩት ታሪክ የሆነው የዛሬ አምስት አመት ግድም ነው:: ከ 40 ዓመት በላይ የኖሩበት፣ ብዙ ደስታ ብዙ ሃዘን ያዩበት መሃል አዲስ አበባ ላይ የሚገኘው የቤታችው ግማሽ በመንገድ ምክንያት ሊፈርስባቸው እንደሆነ እና ከቀረውም ቤት በስተግራ ያለውን የቤቱን ግድግዳ ደራሽ የወንዝ ጎርፍ እንደወሰደባችው ሰማሁ:: ምን አይነት ዱብ እዳ ነው አስብሎኝ ነበር:: ነገሩን በስማሁ በማግስቱ እንዴት ሆናችሁ? ተረፋችሁ ወይ? ለማለት ረፈድፈድ ሲል ወደቤታቸው ጎራ አልኩ:: የአጥሩ በር ገርበብ ብሎ ስለነበር ገፋ አድርጌ ወደግቢው ዘለቅኩ:: ግቢው: ቤቱ ትርምስምስ ብሏል :: ግማሹ የቤት እቃ ግቢው ውስጥ ተኮልኩሏል:: እኚህ እናት ነጠላቸውን ትከሻቸው ላይ ደግልለው የቤቱ መግቢያ ደፍ ላይ ቁጭ ብለዋል:: እንደወትሯቸው ሁሉ ከእጃቸው የማይታጣወን መጽሐፍ ቅዱስ ገልጠው የማንበቢያ መነጽራቸውን አይናቸው ላይ ሰክተው አቀርቅረዋል::

“ ደህና ዋላችሁ“ አልኩ መጀመሪያ በቅጡም አልለዩኝም ነበር:: ይሁን እንጂ በፈገግታ ለሰላታዬ ምላሽ ሰጡኝ:: ጠጋ ስል አወቁኝና ተሳሳምን:: ነይ እዚህ ጋ ቁጭ በይ ብለው ከጎናቸው እንድቀመጥ ጋበዙኝ:: “ትናንት ማታ የጣለው ዝናብ እንዳለ ቤት ውስጥ ገብቶ አድሮ ይድረቅ ብለን ነው እቃውን ደጅ ያወጣጣነው:: ልጆቹ የቀረውን ቤት ውስጥ እያስተካከሉ ነው:: “ አሉኝ:: “ወይ ጣጣ ደግሞ ሌላ ችግር? ምን ጉድ ነው የመጣባቸው?“ አልኩ በውስጤ እሳቸው ግን መልሰው ወደ መጽሐፍ ቅዱሳቸው አቀረቀሩ “አይይ ደከማችኋ ! አልኩ ጨዋታ ላመጣ ብዬ “ ግድ የለም ይሁን : ዝናብ ስጠን እያልን ለምድሪቱ ስንጸልይ ነበር: ምድሪቱ ረስርሳለች ፡ውሃ አይደል ይደርቃል:: እኔም በጠዋት ቸርች የእህቶች ጸሎት ቆይቼ ገና መምጣቴ ነው: ጌታ ይመስገን:: አሉ:: ሁሌም ከንግግራቸው መጨረሻ “ጌታ ይመስገን” አይቀርም:: አሁንም በልቤ “ ሆ! እና ዝናቡ የዘነበ እንደው ደጅ አይዘንብም እንዴ? ምን ቤት ውስጥ አመጣው::” እያልኩ ሳስብ እሳቸው ጨዋታቸውን ቀጠሉ:: “ለዚህ ለመንገድ ብለው ከፊት ያለውን መንገድ ስለቆፈሩት ላይ ሰፈር የዘነበው ውሃው ሁሉ ተሽቆልቁሎ ሰተት በሎ ቤት ውስጥ ይገባል:: አሉኝ ”ምን እዚህ አገር እኮ ለሰው ደህንነት አያስቡም” ብዬ ቅራኔዬን አስማሁ:: እትዬም ቀበል አርገው “ግድ የለም አሁን ይሄ መንገድ አስፓልት ሲሆን ሁሉም ይስተካከላል:: ታክሲውም አውቶቢሱም በራችን ላይ ይሆናል:: ጌታ ነው ያመጣው ይሁን “ጌታ ይመስገን; ሁሉ እስኪስተካከል ለትንሽ ጊዜ ዋጋ መክፈል የግድ ነው” አሉኝ:: እንደመናደድ አደረገኝ:: አሃ! አውቀው ለመቃረን መሰለባቸዋ! ቤቱ አሁን የት ድረስ ነው ይፈርሳል የተባለው?አልኩ:: የቱ ቤት ? አሉኝ በእርጋታ እርፍ! ይሔ የርሶ ቤት ፡ የወለዱ የከበዱበት ፡ስንት ልጅ: ስንት የልጅ ልጅ ያዩበት: የኳሉ የዳሩበት ልላቸው አማረኝ:: አሃ ! ያናድዳላ:: እሳችው ግን የድምጻቸው ሁኔታ ሳይቀየር ጥያቄዬ ዘግይቶም ቢሆን ገብቷችው “ወደዚያ አካባቢ ነው ፣በሩ ላይ ቁጥሩን ጽፈውታል ” አሉኝ :: ብዙም የደነቃቸው አይመስሉም:: “በጣም ያሳዝናል “ አልኩ ወሬ ሳደምቅ ”ይሁን ጌታ አዋቂ ነው ምን ይሔ ቢፈርስ ድንኳን ነው:: ይዘነው አንሻገር ፡ምንም ባልነበረን ሰአት ጌታ የሰራልን ቤት ነው:: አሁንም ከዚህ መለስ ይበቃችኋል ካለ ይበቃናል:: ብዙ ሰዎች ሳሎናቸው ድረስ ወይም ሙሉውን የፈረሰባቸው አሉ ሲሉ ሰምቻለሁ:: እሱም ቢሆን ጌታ መልካም ነው ፡ መኖሪያችን እሱ የዘላለም አምላክ ነው::” አሉኝ እውነት ተናድጄ እንደነበር ትዝ ይለኛል:: ሰው እንዴት በሁሉ አቅጣጫ ቀና ቀናውን ብቻ ያስባል?ጌታ ኢየሱስ እንኳን በአንድ አጋጣሚ አዝኖ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል ብዬ በሐሳቤ ጥቅሴን ለጋሁ:: ላስተዛዝን ሰለመጣሁ ነው መሰል ማስተዛዝነው ባጣ ተናደድኩ:: እሳቸው ግን ከኔ አርእስት ውጪ የሆነ ጨዋታቸውን ቀጠሉ “አሁን ቅድም አንቺ ከመምጣትሽ በፊት እዚች ጋር ቁጭ ብዬ የጌታዬን ቃል እያነበብኩ ስገረም ስደነቅ ነበር አሉና ፈቃዴንም ሳይጠይቁ ከሰንበት ትምህርት ቤት ጀምሮ የማውቀውን አንድ ክፍል ከመዝሙረ ዳዊት ላይ ያነቡልኝ ጀመር:: ምእራፉን ሙሉ በአንድ ጊዜ ወርደውት ሲጨርሱ ቀና ሲሉ ከመንጽራቸው ጀርባ ያለው የፊታቸው ክፍል በእንባ ርሷል:; “አይገርምም !? ” አሉኝ ሲቃ ባነቀው ድምጽ ጎሽ!አልኩ በልቤ አሁን የመጣሁበት ጉዳይ ግብ ሊመታ ነው ላስተዛዝን ነው ለካ ሆድ ብሷቸው ነው! እያልኩ ሳሰላስል ኸረ እሳቸው ምን በወጣቸው፡ ያነበቡትን ቃል መስመር በመስመር እያብራሩልኝ በእንባ መታጠባቸውን ቀጠሉ:: ማብራሪያቸው ቀጥታ ነው :: ምንም ፍልስፍና የለውም:: ፊታቸው በእንባ ይታጠብ እንጂ በደስታ ያበራል:: ቃላቶቹ ግን ከአንደበታቸው እየወጡ ወደኔ ጆሮ ሲደርሱ እንደ ማር እየጣፈጡኝ ልቤ ውስጥ እየገቡ ሲቀረቀሩ ይታወቀኝ ነበር:: መነጽራቸውን አውልቀው በደስታ የሚፈሰውን እንባቸውን በነጠላቸው ጫፍ አደራረቁ:: ማልቀሳቸው እንዳስጨነቀኝ ገብቷቸው ነው መሰል ፈገግ እያሉ “ ሁል ጊዜ የጌታዬን ምህረቱን ፡ፍቅሩን፡ መልካምነቱን ሳስብ ነብስም አይቀርልኝም: እሱ እኮ እግዚአብሔር ነው ፡ትልቅ ነው ፡ግን ቸር ነው: መልካም ነው:: . . . ብዙ ብዙ አሉኝ:: እነዚህ ቃላት ከልጅነቴ ጀምሮ ስሰማችው ያደግኳቸው ቃላት ናቸው:: ጆሮዬ ለምዷቸው ነው መሰል ስሰማቸው የሳቸውን ያህል ትርጉም ሰጥተውኝ ማወቃቸውን እጠራጠራለሁ :: እሳቸው ግን የዝናብ ጎርፍ ሲያጥበው ያደረው ቤታቸው ደፍ ላይ ቁጭ ብለው፡ በስተግራቸው የወንዝ ደራሽ ወንዝ ገምሶ የወሰደባቸውን የቤታቸው ፍራሽ ፡ከጥቂት ቀናት በኋላ ሊፈርስና መንገድ ሊሆን የታቀደለት አጥርና ግቢያቸው ከፊታቸው ተንጣሎ እሳቸው ግን እዚያ ያሉ እስከማይመስሉ ድረስ ሌላ አለም ላይ ናቸው::

አባይን ያየ ምንጭ አያመሰግንም, ፓውዛ ያለው በኩራዝ አይደነቅም: የታረደውን በግ በዙፋኑ ተቀምጦ ያየ ሰው ሃሳቡ ሁሉ በጉ ነው:: በጥቃቅን መገለጥ መሳይ ሃሳቦች ጊዜውን አያጠፋም:: የተማረውም ያልተማረውም ; የጠቢቡም የጥበብ አልባው; የባለ አእምሮውም የየዋሁም አምላክ እውነት እንዲህ አሁን በዚህ ዘመን ባለው በእውቅት ልክና መልክ ወደ ደረቱ እንድንጠጋ የሚያስብ አይመስለኝም:: አንድ ፍርሃት አለኝ:: በዘመኑ አንድ ፊደል ያልቆጠረ, አልያም ከመጽሃፍ ቅዱስ በቀር ሌላ መጽሃፍ አንብቦ የማያውቅ, ዮ ቲዩብ,: ፌስ ቡክ: ኢንተርኔት ከነመፈጠሩ አይቶ የማያውቅ: መጽሃፍ ቅዱስ ት/ቤት በበሩ አልፎ እማያውቅ ሰው; ግን ቃሉን አንብቦ በቅንንት መንፈስ ቅዱስ ባበራለት እውነት ጌታውን ለመምሰል የተጋ; በመክሊቱም ነግዶ ያተረፈ: በዚያች በቁርጥ ቀን አይናቸን እያየ አንተ ታማኝ በጎ ባሪያ ሲባልና የክብር አክሊል ሲቀበል: ይሄ በተለያየ ጥቃቅን መገለጥ መሳይ ሃሳቦች ወደ ጌታ የተጠጋ መስሎት በቃላት ጨዋታ ህዝብን ግራ ሲያጋባ ና ጊዜውን ሲያጠፋ የኖረው “ባለራኢ” አማኝ ምን ይሰማው ይሆን:: አበስኩ ገበርኩ!!

እናማ ዛሬ እዚህ ውዠምብር የበዛበት ጊዜ ላይ ሆኜ ግራ ግብት ሲለኝ እኚህ እናት ደጋግመው ወደልቤ እየመጡ ሰነበቱ :: እናም ፈጣሪዬን ለመንኩት:: ጌታ ሆይ እያንዳንዱ ቀን ብዙ አስጨናቂ ነገር ይዞ በሚመጣበት በዚህ ዘመን እንድኖር ፈቃድህ ከሆነ እባክህ በህልውናህ ውስጥ ደብቀኝ፡: አይኔን በዙሪያዬ ካለው ትርምስና ውዥምብር ላይ አንስቼ አንተ ላይ ብቻ የማደርግበት: ቃልህ ውስጥ ድብቅ እምልበት ጥብብ ስጠኝ:: አንተ እንደምታይ እንዳይ አይኔን አብራልኝ :: ሳበኝ ወደ ደረትህ አስጠጋኝና ድብቅ አርገኝ:: አንተ የናቅከውን ሳከብር፡ አንተ ቦታ በማትሰጠው ጥቃቅን ነገር ላይ ጊዜዬን ሳጠፋ እንዳልገኝ ማስተዋልን ስጠኝ:: በጥቅስ ኳስ ስራገጥ በመክሊቴ እንደሚገባ ሳልነግድ እንደሚገባ ሳላፈራ ይቺ እንደሸማኔ መወርወሪያ እብስ የምትል ህይወቴ ያበቃላትና ኋላ ጸጸቱ ለኔ ነው :: እናማ ደብቀኝ: በህልውናህ ውስጥ ደብቀኝና አንተን በማወቅ አሳድገኝ:: አዎ! እውነተኛው እረኛዬ አንተው ጋ ድብቅ አርገኝ!!!

60 views0 comments

Comments


bottom of page