top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የራስ ምታት



ራስ ምታት በአብዛኛው በራሱ በሽታ ከመሆን ይልቅ የሌላ በሽታ መገለጫ ነው፡፡ብዙ የራስ ምታት አይነቶች ቢኖሩም ሁሉም አንድ የሆነ መለያ አላቸው፡፡ይኸውም ህመም ማስከተላቸው ነው፡፡ አንዳንዶቹ በራስ ህመም ብቻ ሲያቆሙ ሌሎቹ ደግሞ እንደ ማቅለሽለሽ እና ማስታወክ የመሳሰሉትን ያስከትላሉ፡፡ ራስ ምታት በብዛት አደጋ የሌለውና በቀላሉ ልትከላከለው የምትችለው ነገር ነው፡፡

አልፎ አልፎ ደግሞ እንደ ማጅራት ገትር እና የአእምሮ ካንሰር የመሳሰሉ ከበድ ያሉ በሽታዎች መገለጫ ነው፡፡ራስ ምታትን ሊያስነሱብህ ከሚችሉ መንስኤዎች መካከል ጭንቀት፣ የእንቅልፍ ማጣት፣ ጉንፋን፣ የሆርሞኖች ለውጥ(በተለይ በሴቶች ላይ)፣ አልኮል፣ ሲጋራ፣ ፍርሃት፣ ድብርት የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አንዳንድ መድሃኒቶችም ራስ ምታትን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡

ዋና ዋና የራስ ምታት መንስዔዎች

ራስ ምታት በራሱ በሽታ ሲሆን እና የሌላ በሽታ ምልክት ሲሆን በማለት ራስ ምታትን በሁለት አይነት መንገድ ልናየው እንችላለን፡፡ ማይግሬን ፣ በጭንቀት ምክንያት የሚመጣ ራስ ምታት፣ ከመጠን ያለፈ ስራ ጋር ተያይዞ የሚመጣ እንዲሁም ምክንያቱ የማይታወቅለት በማለት ራስ ምታትን እንደበሽታ ልናየው እንችላለን፡፡ ከዚህ ባለፈ ራስ ምታት የተለያዩ የሰውነት ክፍል ኢንፌክሽንን፣ ጭንቅላት ላይ የሚኖር አደጋን፣ የደም ስር ችግሮችን፣ የጭንቅላት ካንሰርን ተከትሎም ሊመጣ ይችላል፡፡

ራስ ምታት መቼ ሊያሰጋኝ ይገባል?

  • ከአንድ ሳምንት በላይ ከቆየ፣

  • ምንም እንኳን በተደጋጋሚ ማስታገሻ ብትወስድም ከመሻል ይልቅ እየባሰ ከሄደ፣

  • ለመጀመሪያ ጊዜ ሃይለኛ ራስ ምታት ሲያምህ ከሃምሳ አመት በላይ ከሆንክ፣

  • ከዚህ በፊት የነበረውን አይነት ቀይሮ አዲስ ፀባይ ካመጣ፣

  • ህመሙ ከየእለት ኑሮህ የሚያስተጓጉልህ ከሆነ፣ ለምሳሌ ስራ ለመስራት የማያስችል አይነት ህመም ካለህ፣

  • ከራስ ምታቱ በተጨማሪ የተለያዩ የበሽታ ምልክቶች ለምሳሌ ከአፍንጫ የሚወጣ ፈሳሽ፣ ሳል…ወዘተ ከታዩብህ ወደሆስፒታል ሄደህ ዶክተርህን ማማከር አለብህ፡፡

በጭንቀት ምክንያት የሚመጣ እራስ ምታት

በጭንቀት ምክንያት የሚመጣ እራስ ምታት ምንድን ነው ?

በህፃናትም ሆነ በጎልማሶች በብዛት የሚታየው የራስ ምታት አይነት ነው፡፡ ህመሙ በጣም የማይጠና ሲሆን ከመውጋት ይልቅ የጭንቅላትን ሁሉንም አካባቢ የሚሸፍን የመጠዝጠዝ ስሜት አለው፡፡ ከ90 በላይ የሚሆነው ራስ ምታት በዚህ ስር የሚመደብ ሲሆን ምንም ጉዳት የሌለውና በራሱ ጊዜ የሚጠፋ ነው፡፡ ፍርሃት፣ ጭንቀት፣ ድካም እና ከመሳሰሉ የሰው ልጅ ስሜቶች ጋር ተያይዞ ይመጣል፡፡ ትክክለኛ ያልሆነ የሰውነት አቋም፣ በቂ ብርሃን የሌለው የሥራ ቦታ፣ ከፍተኛ እና የሚጮኹ ድምፆችንም ተከትሎ ሊከሰት ይችላል፡፡

በጭንቀት ምክናይት የሚመጣ ራስ ምታት ምልክቶች ምንድን ናቸው?

በሁሉም የጭንቅላትአካባቢ እኩል የሚሰማ በጣም ከባድ ያልሆነ የመጠዝጠዝ አይነት ህመም ዋና ምልክቱ ነው፡፡ በራስ ዙሪያ በጨርቅ ድብን ተደርጎ የመታሰር ወይም የመጨምደድ አይነት ስሜት ሊሰማም ይችላል፡፡ የሚያሙና የተኮማተሩ የአንገት ጡንቻዎች እንዲሁም በመንጋጋ አካባቢ የሚኖር የህመም ስሜት አብሮት ይኖራል፡፡ ይህ ራስ ምታት በተደጋጋሚ የሚመጣ ሲሆን ከሰአታት እስከ ቀናት ሊቆይ ይችላል፡፡ ምንም እንኳን የህመም መጠኑ እንደየሰዉ ቢለያይም ቀን ቀን የመባባስ አዝማሚያ ቢያሳይም ከሰውነት እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ብዙ ለውጥ አይታይበትም፡፡

ለረዥም ጊዜ የቆየ ከሆነ ትከሻን የመክበድ፣ ቶሎ የመድከም ፣ ሀሳብን የማሰበሰብ ችግር እና ድብርት(depression) ሊያስከትል ይችላል፡፡

ይህንን በሽታ እንዴት ልከላከል እችላለሁ?

የሚያዝናኑ እና ሊያፍታቱህ የሚችሉ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን አድርግ፡፡ እንቅልፍ እና ምግብ ለሁሉም ነገር ቁልፍ ናቸው እና የሚበቃህን ያህል ተኛ፤ ተመጣጣኝ ምግብም ብላ፡፡ ቀላል ስፖርቶችን ስራ፡፡ አልኮል፣ ሲጋራ እና ቡና አታብዛ፡፡ ማሳጅ (massage) ሰውነታችንን እንዲሁም አእምሮን ፈታ ስለሚያደርግ እንድትሞክረው እንመክርሃለን፡፡

እንደስራህ ሁሉ እረፍትህም አስፈላጊ ነውና በስራህ መካከል ትንንሽ እረፍቶችን አድርግ፡፡ ለብዙ ጊዜ ተቀምጠህ የምትሰራ ከሆነ በየመሃሉ እየተነሳህ ዞር ዞር በል፡፡ አሊያም የምትሰራውን ነገር በመቀየር ሌላ ሥራ ጀምር፤ ይኽም ስራህን ሳታቆም እራስህን ለማሳረፍ ጥሩ መፍትሔ ነው፡፡

ራስ ምታት በተደጋጋሚ የሚያስቸግርህ ከሆነ ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ህመሙ በሚነሳብህ ጊዜ ማስታወሻዎችን በመያዝ መቼ ፣እንዴት እና ምን እንደሚያስነሳብህ በመለየት ጥንቃቄ ማድረግ ትችላለህ፡፡ ቀላል ራስ ምታት ከሆነ እና ሌላ ተያያዥ የህመም ስሜቶች ከሌሉት ወደ ሆስፒታል መሄዱ ብዙም አስፈላጊ አይደለም፡፡ ትኩረትህ ሊሆን የሚገባው በሽታው ላይ ሳይሆን የሽታው መንስኤ ላይ ነው፡፡ ይህንን ነገር ካላስወገድከው በስተቀር ራስ ምታትህን ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት ያስቸግራል፡፡

ምን አይነት መድሃኒቶችን በመጠቀም ህመሙን ልቀንስ እችላለሁ?

ራስ ምታትን የመቀነስ ችሎታ ያላቸው የተለያዩ መድሃኒቶች አላቸው፡፡ እነዚህን መድሃኒቶች በየጊዜው መውሰድ ግን የራሱ ጉዳት አለው፡፡ በተደጋጋሚ በወሰድካቸው ቁጥር መድሃኒቱ ላይ ያለህ ጥገኝነት እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ከዛም አልፎ መውሰድ በምታቆምበት ጊዜ የሚነሳ አይነት ራስ ምታት ልታተርፍ ትችላለህ፡፡

ማይግሬን

ማይግሬን ምንድን ነው?

ማይግሬን ከፍተኛ እና በተደጋጋሚ የሚከሰት ራስ ምታት ሲሆን የተለያዩ ምክንያቶችን ተከትሎ የሚነሳ እና እነዚህ ምክንያቶች ሲወገዱ ደግሞ የሚቀንስ በሽታ ነው፡፡ ህመሙ የሚከሰተው አእምሯችን ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ የደም ስሮች መካከል ተለቅ የሚሉት ሲያብጡና ሲሰፉ ነው፡፡ የነዚህ የደም ስሮች እብጠት በዙሪያቸው ከሚገኙ ነርቮች የተለያዩ ንጥረ ነገሮች እንዲለቁቀ ያደርጋል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ እነዚህ የተመረቱ ንጥረ ነገሮች አእምሮአችን ለህመም ያለውን ስሜት ከፍ ያደርጉታል፡፡ በመሆኑም ለትንሽ የህመም መንስኤ ከፍተኛ የህመም ስሜት እንዲሰማ ያደርጋሉ፡፡በዚህ የሚመጣ ህመምም ወጋ ወጋ የሚያደርግ አይነት ነው፡፡

ይህ በሽታ ከ40 አመት በፊት ይጀምር እና ከ60 በላይ ሲሆኑ በተለይ በሴቶች ዘንድ ይቀንሳሉ እስከመጥፋትም ይደርሳል፡፡ በዚህ በሽታ ህፃናት ተጠቂ ሊሆኑ ቢችሉም በብዛት ግን አይታይባቸውም፡፡ምንም እንኳን ፈውስ የሌለው በሽታ ቢሆንም በተለያዩ መድሃኒቶች እና የአኗኗር ዘይቤዎች ልትቆጣጠረው ትችላለህ፡፡

የማይግሬን ምልክቶች ምንድናቸው?

ከፍተኛ የሆነ በተደጋጋሚ የሚነሳ እና በመሃል እረፍት የሚሰጥ አይነት የራስ ምታት የመጀመሪያው ምልክት ነው፡፡ህመሙ ቀስ በቀስ የሚጨምር ሲሆን ከእቅልፍህ ስትነሳ እያመመህ ከሆነ ግን ከፍተኛው የህመም ደረጃ ላይ ልታገኘው ትችላለህ፡፡

በጭንቅላትህ ግማሽ ክፍል ብቻ የሚኖር ህመም የተለመደ መገለጫው ሲሆን ከግራ ወደቀኝ (ወይም በተቃራኒው) እያለ በተለያየ ጊዜ የተለያየ ክፍልን ሊያጠቃ ይችላል፡፡ ህመሙ ከአራት ሰአት እስከ ሁለት እና ሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ከጭንቅላት እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ይባባሳል፡፡ ሰውነትህን ሁሉ ከመክበድ ባለፈ ሊያስመልስህም ይችላል፡፡ በተጨማሪም ለሽታዎች፣ ለድምፅ እና ለብርሃን ያለህን ስሜት ይጨምራል፡፡

ህፃናት ላይም ተመሳሳይ ምልክቶች ሲኖረው የሚቆይበት ጊዜ ግን አጠር ይላል ይህም ከግማሽ ሰአት እስከ አንድ ቀን ቢሆን ነው፡፡

ራስ ምታቱ ከመምጣቱ አስቀድሞ የሚታዩ ምልክቶች አሉ፡፡ እነዚህ ምልክቶች ሁሉም ህመምተኞች ላይ የሚከሰቱ ባይሆኑም ለሚታዩባቸው ሰዎች ግን ማይግሬን ሊነሳባቸው እንደሆነ ጥሩ ማመላከቻዎች ናቸው፡፡ በአማካይ ከአንድ ቀን በፊት በጣም ንቁ የመሆን በአንዳንዶች ላይ ደግሞ ቶሎ የመድከም ፣ የመናደድ፣ ጣፋጭ ምግቦችን የመፈለግ እና የመሳሰሉ ባህሪዎችን ያሳያሉ፡፡ የአይን ብዥታ፣ የእጅ ጣት መጠዝጠዝና መደንዘን፣ የንግግር መጓተት የመሳሰሉት ምልክቶች ማይግሬን ከመምጣቱ ከጥቂት ደቂቃወች በፊት ይታያሉ፡፡ እነዚህ ምልክቶች ከታዪ በኋላ ማይግሬን ሊከተል ወይም ደግሞ ምንም እንኳን ያልተለመደ ቢሆንም ማይግሬኑ ላይከሰትም ይችላል፡፡

አንዳድ ሰዎች ራስ ምታቱ ሊነሳ እንደሆነ አስቀድመው ያውቃሉ፡፡ ማይግሬኑ ከሄደ በኋላም ድካም፣ ቶሎ መናደድ፣ መደበት ብሎም የተለያዩ የቆዳ ክፍሎችህን መበለዝ ልታስተውል ትችላለህ፡፡

የማይግሬን መንስኤዎች ምንድን ናቸው?

ከ 50% በላይ የሚሆኑ በማይግሬን የተያዙ ህመምተኞች ከቤተሰባቸው ይወርሱታል፡፡ ስለዚህ በቤተሰብሽ ውስጥ የማይግሬን በሽተኛ ካለ በተለይ ደግሞ እናት፣አባት፣እህት፣ወንድም በዚህ በሽታ ተጠቂ ከሆኑ አንቺም በበሽታው ተጠቂ የመሆን እድልሽ ይጨምራል፡፡ በሽታው ከተለያዩ ሆርሞኖች ጋር ተያያዥነት ስላለው ሴት መሆን በራሱም በበሽታው የመጠቃት እድልን በትንሹ ይጨምራል፡፡

ማይግሬንን የሚቀሰቅሱ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

የተለያዩ በሽታዎች በተለያዩ ምክንያቶች እንደሚነሱ ሁሉ ማይግሬንም የራሱ ቀስቃሽ ምክንያቶች አሉት፡፡ ከነዚህ መካከል ብዙ ጊዜ የሚጠቀሰው ጭንቀት ነው፡፡ ጭንቀት በራሱ ራስ ምታትን የሚያመጣ ሲሆን ማይግሬን ላለበት ሰው ግን ዋና ቀስቃሹ ነው፡፡

ረሃብ፣ የፈሳሽ ምግብ ብቻ ተመጋቢ መሆን ወይም የተዘበራረቀ የምግብ ፕሮግራም በሽታውን ሊያባብሱ ይችላሉ፡፡ አልኮል መጠጦች፣ ኮምጣጣ ምግቦች፣ ቸኮሌት እና ቺዝ የመሳሰሉ ምግቦች በሽታንውን ያሰነሳሉ፡፡ ብዙ ወይም ትንሸ እንቅልፍ፣ የአየር ሙቀት ለውጦች፣ ሀይለኛ ሽታ፣ፀሃይ፣ ከፍተኛ ድምፆች በሽታውን ከሚያስነሱ ምክንያቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

በሴቶች በኩል ደግሞ የወር አበባ ኡደትን ተከትለው የሚጨምሩ እና የሚቀንሱ የሴት ሆርሞኖች ይህንን በሽታ ያባብሱታል፡፡ በተለይ የወር አበባሽ በሚመጣበት ጊዜ በሽታው ከድሮው በበለጠ ይጨምራል፡፡ ስለዚህም አንድ ሴት ስታርጥ የማይግሬን በሽታዋ ከመቀነስ አልፎ ሊጠፋም ይችላል፡፡ እርግዝናም የራሱ የሆነ ለውጥ ያስከትላል፡፡

ማይግሬንን እንዴት ልከላከል?

ማይግሬን የማይድን በሽታ ቢሆንም የሚከሰትባቸውን ጊዜያት ለመቀነስ የተለያዩ ነገሮች ማደረግ ትችያለሽ፡፡ በሽታውን ምን እንደሚያስነሳብሽ ለይተሸ ማወቅ እና ከነዚህ ነገሮች እራስሽ መጠበቅ የመጀመሪያው እና ዋናው ተግባርሽ ሊሆን ይገባል፡፡ ራስ ምታቱ በሚጀምርሽ ጊዜ መቼ እንደጀመረሽ፣ ህመሙ ሀይለኛ ወይስ ለዘብ ያለ እንደነበር፣ መድሃኒት ወስደሽ ከሆነ የወሰድሽውን መድሃኒት፣እና ሌሎች ምክንያቶችን በመፃፍ እና በተለያዩ ጊዜያት የወሰድሻቸውን ማስታወሻዎች በማመሳከር ምክንያቶቹን በቀላሉ ማወቅ ትችያለሽ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የአኗኗር ዘይቤሽን መቃኘት ተገቢ ነው፡፡ጭንቀትን ማስወገድ፣ ምግብ በሰአቱ መብላት፣ እንቅልፍ በልኩ መተኛት፣ አልኮል መጠጦችን ማስወገድ እና ከላይ የተጠቀሱ ምግቦችን ባለመብላት ራስ ምታቱን መቀነስ ትችያለሽ፡፡ የተለያዩ ረጋ ያሉ የሰውነት እንቅስቃሴዎችን መስራት እና እራስን ከማዝናናት በተጨማሪ ደረቅ መርፌ (acupuncture) መጠቀምም ሊረዳሽ ይችላል፡፡

ራስ ምታቱ ከጀመረኝ በኋላ ምን ላደርግ እችላለሁ?

አንዴ ራስ ምታቱ ከጀመረህ በኋላ መድሃኒት በመውሰድ ፀጥ እና ጨለም ያለ ቦታ ላይ እረፍት አድርግ፡፡ ቀዝቃዛ ነገር ለምሳሌ በፎጣ የተጠቀለለ በረዶ ግምባርህ ላይ ማድረግ እንዲሁም ቡና መጠጣት ሊረዳህ ይችላል፡፡

የማይግሬን ህክምና ምንድን ነው?

ምንም እኳን በሽታው የማይድን ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ብዙ መድሃኒቶች እየተፈበረኩ ሲሆን ከብቃታቸው አንፃር ስናይም በጣም ጥሩ ናቸው፡፡ አንዳዶቹ ራስ ምታቱ ከመጀመሩ በፊት የሚከላከሉ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ ህመሙ ከጀመረ በኋላ ህመሙን የመቀነስ ስራ ይሰራሉ፡፡ ነገር ግን መድሃኒት ከመጀመርሽ በፊት ሀኪምሽን ማማከር አለብሽ፡፡

Source: addishealth.com


54 views0 comments
bottom of page