• የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የሼህ ሁሴን ጅብሪል ትንቢታዊ ግጥሞች (ክፍል - 12)የሼህ ሁሴን ጅብሪል ትንቢታዊ ግጥሞች (ክፍል - 12)

81.ተፈሪ መኮንን አሥመራ እጁን ሰዶ

ትግሬን በጠቅላላ አደረገው ባዶ

ዘለዓለም እንዲኖር በሐዘን በመርዶ

እኩሉም ይኖራል ቤቱ ነዶ ነዶ

እኩሉም ይሄዳል ወደ ገርብ ተሰዶ::


82. የትግሬን መከራ የወሎን ችግር

የሚበላው አጥቶ ኸልቁ ሲቸገር

ሐበሻ የዚያን ቀን የለውም ቀራር

ውሸት እንዳይመስልህ በወሬም አይቀር

ያችን ቀን ካለፈ የለውም ችግር::


83. ወሎ በረሃብ አልቆ ሞት የበዛ እንደሆን

የሸዋ መኳንንት ዳርቻው ምን ይሆን?

(በቁም ይጋለጣል ይሆናል እንዳይሆን

ተፈሪ የዚያን ቀን ምን ይበጀው ይሆን?)

የጁን አግኝቶታል እንግዲህ ሰው አይሆን::

84. ተፈሪ መኮንን የተያዘ እንደሆን

እንግዲህ ሐበሻ ምን ይበጀው ይሆን፣

(እህል ያልገዛ ሰው ምን ይበጀው ይሆን?)

አሥመራና ሸዋ ይሆናል እንዳይሆን

ወያኔ ተነሥቶ አሥመራ እሳት ሲሆን::


86. ካለፉት ይሻላል ለማልማት ነው እንጅ

ተፈሪ መኮንን ለእስላም አይበጅ

እኩሉን ሲያስለቅስ እኩሉን ሲያበጅ፣

ሃምሳ ዓመት ይነግሣል ዘር የለውም እንጅ

እንቁላሉ ገምቶ ጠፋ በሰው እጅ::


87. ተፈሪ መኮንን ትልቁ ልጃቸው

አልጋውን ለመያዝ ያስባል ልባቸው

የኋላ የኋላ ከቲማም የላቸው

ሸዋ ክፉ ሰው ነው ከሥር ነቀላቸው

ዳግሚያ እንዳይገኙ ከእነልጅ ልጃቸው::


88. አልጋው በወደቀ በሁለት ዓመት

ፊንጭር ፊንጭር ይላል አይሆንም መስሎት

ለዕለት ደስ ይለዋል ያገኘሁ መስሎት

ማለቁን ሳያውቀው በረሃብ በጥማት

ጌታውን ይገድላል ቦታና መሬት

ሀብታም የዚያን ጊዜ ይወድቃል መሬት::


89. ባሪያ ሁር ተብሎ ከሆነ ፈራጅ

ገላጋዩ ማነው? እርስ በርስ ሲፋጅ

የድህነት አዋጅ ሲታወጅ አዋጅ

ተፈሪዋን ጥላ ጅብ አበቀለች

አንበሶቿ ሞተው ባዶዋን ቀረች::


90. ከአሕመድ ነጋሽ አገር አንድ ሰው ተወልዶ

ሸዋ አልጋው ቢናወጥ ሄደ ባሕር ማዶ፣

መሄድም ችግር ነው ቢያዝ አይ ምን ገዶ?

ሐበሻ ጉድ አየ አንበሳ እባብ ወልዶ፣

ትግሬ መርዙን ተፋው ሻንቅላ ጅብ ሰዶ::


91. ቀልድና ዛዛታ በውሸት መማማል

እቤት ሲያሳስቁ ከሴት ጋር መዋል

ዲኑን ለማጥፋት ነው የያዙት ትግል

እሱ ተካ ይላል ባሏ ወጣ ሲል

የሐሳሉን ዕቃ ገብቶ ሊያማስል::


92. ምክሬን ሰምተህ ያዘው የመንደር ውርጋጥ

መጭውን አይተነዋል እንዳትደነግጥ

ሴቶች ያስበቁሃል ስትቆናጠጥ

የአባወራውን ምስት ቀሚሷን ስትገልጥ

እንደ ፍየል ቅልጥም ከንፈሯን ስትመጥ::

41 views0 comments

Copyright © 2018 Meskan Media Network - All Rights Reserved. E-mail : meskanmedia@gmail.com

  • YouTube - White Circle
  • White Spotify Icon
  • White Apple Music Icon
  • White Amazon Icon
  • White Facebook Icon
  • Twitter Clean