የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ
አንጥረኛው እና አራጋቢው (በእሙ ኢሳን)
Updated: Jun 17, 2019
አንጥረኛው የእለት ስራውን በብቃት ለመወጣት ያነጥራል፣ ይቀጠቅጣል እንዲሁም በውብ አዕምሮውና እጆቹ ይቀርጻል። ባለሙያ እንደመሆኑ መጠን እያነጠረ የሚያወጣውን በደረጃ ያስቀምጣል። ሲሻው ወርቅ፣ ብር አልያም ደግሞ ነሃስ ወዘተ እያለ እንደሚፈልገው እየቀረጸና እያሳመረ ይሰራል። አራጋቢው ወይም ያንን.. ብረት ለማቅለጥ የሚያግዘውን እሳት የሚያቀጣጥለው ደግሞ ያለ ማቋረጥ ያራግባል። ትንሽ ያርፍና ደግሞ እንደገና እሳቱ በደንብ እንዲቀጣጠል በመቆስቆሻው ይቆሰቁሳል። የሚገርመው አንጥረኛው እና አራጋቢው የማንጠር ሙሉ ስራውን ለማከናወን የሚወስድባቸው ጊዜ የተለያየ ነው። አንጥረኛው ያ.. ብረት ከቀለጠ በዃላ የሚፈለገውን ቅርጽ ለማምጣት ምንም ባለክህሎት ቢሆንም እንኳን ረጅም የሆነ ወቅት ይወስድበታል። አራጋቢው ከአንጥረኛው ቀድሞ እሳቱን የሚያቀጣጥል ቢሆንም የማቅለጥ ተግባሩ ከተከናወነ በዃላ እሳቱን ለማጥፋት የሚወስደው ጊዜ ቀላል ነው። ወይም ውሃ በመቸለስ ለማቅለጥ የተዘጋጀውን እሳት ማጥፋት ይቻለዋል። ነገር ግን በማያውቅ የተለኮሰን የነገር እሳትን ለማጥፋት የማቀጣጠሉን ያህል ቀላል አይደለም።
የአንጥረኛውና የአራጋቢውን ጉዳይ በደንብ እናስተውለው! አገልግሎት ለመስጠትና መልካምን ነገር ለመቅረጽ አንጥረኛው ያነጥራል። ሲያነጠር የሚነጥረውን እንጂ የማይነጥረውን አያነጥረውም። የሚነጥረው ቀላጭ መሆን አለበት። ወይም እሳት የሚገባው መሆን አለበት። እሳት የማይገባው ያው… አይገባውምና ጌጥ ወይም ብርቅ የመሆን እድል አያገኝም ። አንጥረኛው የሚነጥረውን ከማይነጥረው ከማቅለጡ በፊት አያውቀውም ። ብረቱን ከማቅለጫው ይጨምራል። ከዚያም የማይቀልጠውን ከሚቀልጠው ይለየዋል። ያው… የማይቀልጠው አይቀልጥምና በአንጥረኛው ህግ የማይቀልጥ ወይም እርባና ቢስ ተብሎ ይጣላል። ታዲያ በእዚህ ሁሉ የስራ ሂደት ውስጥ አንጠረኛው ያለ ረዳት ለመስራት የሚከብደው ሲሆን በማራገብ ስራ የተሰማራው የስራ አጋሩ ጥረት እና ድካምን ጠንቅቆ ያውቃል።
አራጋቢው ግን ብረቱ ለማቅለጥ የሚፈለገው ሙቀት ይገኝ ዘንድ ከማራገብ የዘለለ ሙያ የለውም። ነገር ግን ከአንጥረኛው በዋለ ቁጥር ባለሙያ የሆነ እየመሰለው ከአንጥረኛው የላቀ ባለሙያ እንደ ሆነ ይሰማው ጀምሯል። እንዲሁም በሙያው ምን ያህል እንደተካነ ያውቁለት ዘንድ በቀየው ለሚገኙ ወዳጅ ዘመዶቹ ለማውጋት እና እኔ ነኝ! ባለሙያው ለማለት ጓጉቷል። በሆነ አጋጣሚ እንኳን በቀየውም ከሚገኙ ሰዎች ከተገናኘ አንጥረኛው ስለየማንጠር ሙያው ደፍሮ በማይናገርበት ሁኔታ ውስጥ አራገቢው ግን ለሰዎቹ ሹክ ይላል። እኔ ነኝ አንጠረኛው እኔው ነኝ! ባለሙያው ብሎ ያወራል… ያራግባል። በማራገብ ስራው ፍጹም ስለተኩራራ መሆንን መምሰል ለየቅል መሆኑን አልተረዳውም። ባለንበት የዘመነ - ዘመን ውስጥ ያለው ማህበረሰብ ሁሉም ባይሆን በርካቶቹ እንደእዚህ ናቸው ። ወይም የእዚሁ ቅጂ ነው። በርካቶቹ ከባለሙያ ወይም ከእውቀት ባለቤቶች ስለዋሉ ብቻ እራራሳቸውን የሙያው ባለቤት እንደሆኑ ሲያሰመስሉ ይስተዋላል። አበው “ለፈጣሪው እና ለህሊናው የሚሰራ አዋቂ አያወራም ተመልካችና ወረኛ ቢሆን እንጂ” ይላሉ።
የሚሰራ ሰው ብዙ አያወራም። ባለሙያ ወይም ታካች ሰራተኛ በሙያው የተካነ በመሆኑ ሌላው እንዲያውቅለት አያወራም ድምጹን አጥፍቶ ይሰራል እንጂ። ሁሌም ቢሆን ከረጅም የጥረት አቀበት በዃላ ደርሶበት እና ደርሶ ያየው ባለስኬት ጉዳዩን ከመላመዱ የተነሳ ነገረ ስራው ሜዳ ሆኖ ይታየውና እርሱ ያከናወናቸው ክንውኖች ቀላልና ተራ ይሆንበታል። ቢሆንም እርሱ የደረሰበት የስኬት ደረጃ በተመሳሳይ ሙያ ላይ የሚገኙ ካልሆኑ በቀር በብዙሃኑ የሚሰራ ወይም ልክ መኪና እንደ ማሽከርከር ቀላል አይደለም።
ይቀጥላል...
በእሙ ኢሳን
ሪያድ ሳዑዲ አረቢያ