top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

አንጥረኛው እና አራጋቢው - ክፍል ሁለት (በእሙ ኢሳን)


በዚህ በዘመነው - የእኛው ዘመን ያለው የሰው ልጅ በቃላት ተነጋግሮ መግባባት አልተቻለውም። ሰው እንዴት በአንድ ቋንቋ እያወራ አይግባባም ጎበዝ ? ላለመግባባቱ መንስኤው የሚሰማውና የሚተነትነው እንደገባው አና በገባው መጠን ስለሚሆን ተናጋሪው ምን እንዳለ ሳይሆን ያ…አድማጩ ለእራሱ ተናጋሪው ምን ለማለት እንደፈለገ በእሱኛው ለእራሱ ያብራራዋል። አንዳንዴ ሁሉም ሰው በምልከት ቋንቋ ቢግባባ ይሻላል ያስብላል! የምልክት ቋንቋ ተጠቃሚዎች ቋንቋውን ከሚናገሩት ወይም ከጤነኞቹ በተሻለ ሁኔታ ሲግባቡ ይስተዋላል። የምልክት ቋንቋ ለቋንቋው ምልክት የሚሰጠው ትርጉም ተመሳሳይ ስለሆነ የቋንቋው ቃል ከአንደበታቸው ሳይፈልቅ በምልከት ብቻ ይግባባሉ። ከሌላው በተሻለ መልኩ ይደማመጣሉ። የምልክት ቋንቋ ተናጋሪዎቹ ያስተላለፉት መልዕክት አድማጮቹ ወይም ተመልካቾቹ ሳይበርዙና ነገሩን ሳይሰነጥቁ ስለሚረዷቸው በቃ ! ይደማመጣሉ። ሳይናገሩ በምልከት ብቻ ተግባብተው ይሰራሉ። መልካም ካልሆን የቃላት ስንጠቃ ይልቅ ተግባር ስለሚያስቀድሙ እና በገባቸው መልኩ ዝም ብለው ስራን ሰለሚሰሩ ፍሬአቸው ጎምርቶና አብቦ በሚያስደምም መልኩ ይስተዋላል። አረዳዳቸው የሚሰነጠቅና የሚብራራ ነገር የለውም። ስራ ብቻ ነውና። ለዚህም ነው እኮ ያ…አንጥረኛው ቢራገብበትም ቢራገብለትም ዝም ብሎ የሚሰራው። አዎን…አንጥረኛው ይቀጠቅጣል፣ ቅርጽ ያወጣል ተግባሩ መልካም ብቻ ሰለሆን እና ያ… መልካም ለሌላውና ለተተኪው ጭምር ይደርስ ዘንድ ተግቶ ይሰራል። በተጨማሪም ባለሙያ ነውና ሙያውን እና ስራውን ያከብራል። ስራ ያስከብራልና።


የሰው ልጅ የሞራል ድቀት የሚጀምረው እራስ ባለመሆን ከሚመነጭ ችግር ነው። ይህ ችግር ለማንነታችን ከሌለን እኛነታችን የምንሰጠው ግነት ዝቅጠትን ያመጣል። ከመምሰል አልፎ ለመሆን ደግሞ ስራ ያስፈልጋል። ስራን ለመስራት ደግሞ ማወቅን ይጠይቃል። እውቀት ከማንበብና ከመስራት ወይም ከልምድ ይመጣል እንጂ ከአዋቂዎች ጋር በመታየት ብቻ ሊሸመት የሚችል ጉዳይ አይደለም። የሚቻለን ከሆነ ግን ከእኔነት በሽታ በፈጣሪ እገዛና በአዋቂዎች ምክር ተፈውሰን ያንተ የእኔ ነው! የእኔም ያንተ ነው ብለን ከተቀበለን ከማጣጣል ይለቅ መደጋገፍን! ከመተቸት ይልቅ ማድነቅን እንለምዳለን። እንዲሁም የሚሰራውን ከማንቋሸሽ ይልቅ ጥረቱን አድንቀን ያልሰራውን እንዲሰራ አበረታተን! ስህተት ካለ እንዲያርም ብናደርገው ከሙያው እና ከጥረቱ የምንማረው ነገር ይኖራል።

ወዳጆች ሆይ! አንጥረኛው የተሻለ ስራ እንዲሰራ ወይም ቆንጆ… ቆንጆ ቅርጾችን እንዲያበጅ እድል እንስጠው እንጂ ! ወደ ፊት እንዳይራመድ ማነቆ አንሁንበት ጃል። በሚሰራው ስራ ላይ መጥፎ ተግባራት ለመስራት የምንጠቀመውን ጊዜ ከአንጥረኛውና በአንጥረኛው ብንማርበት ከአራጋቢነት ወጥተን ወደ አንጥረኛነት የምንሸጋገርበት እድልና መንገድ የሰፋ ይሆናል።

ወዳጄ ሆይ! መምሰልና መሆን በጣሙን ይለያያሉ። ከቻልከ ሁነህ ተገኝ ! ካልቻልክ ደግሞ የመልካም ስራ አድናቂ ሁን! በዚች አለም የሚገኙ ህዝቦች በሙሉ በእኩል አያወሩም ወይም አይሰሩም ። ገሚሱ ሲያወራ ገሚሱ ያደምጣል። አብዛኛው ሲሰራ ውስኑ ደግሞ ያሰራል ወይም አሰሪ ነው ። ይህ ነው የአለም እጣ ፈንታ እስከ ፍጻሜዋ ወደድክም ጠላህም።

ይቀጥላል

እሙ ኢሳን

ሪያድ ሳዑዲ አረቢያ

51 views0 comments
bottom of page