top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

“ለበጎ ያለታደለ አዕምሮ” - (በSemu Bint Shifa)


"ስራ መፍጠር ያልቻለ አእምሮ ለክፋት ተወዳዳሪ አይገኝለትም"

በተለምዶ የአእምሮ ህመምተኛ ብለን እንጠራቸዋለን። በርግጥ ሰዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ይታመማሉ ወይም የአእምሮ ህሙማን ይሆናሉ። በተፈጥሮ ከእናታቸው ማህፀን ውስጥ እያሉ የሚታመሙ እንዳሉ አዋቂዎች ይናገራሉ። ሌሎቹ ደግሞ ባላሰቡት አጋጣሚና አደጋ ይታመማሉ። ገሚሶቹ ደግሞ ተምረው እና ተመርቀው እራሴንና ቤተሰቤን እንዲሁም ሀገሬና ወገኔ እጠቅማለሁ ብለው ተስፋ ሰንቀው ነገር ግን በተመረቁበት የስራ መስክ ስራ ሳያገኙ ሲቀሩ በመጨናነቅ ብቻ ወደ ህመሙ ይገባሉ። ሌሎችም አሉ በሰዎች መውደድና ሰውን በመውደድ በፍቅር የሚታመሙ። በርግጥ እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ሁሉ ለሰው ልጅ በህይወት ዘመኑ ከሚደርሱበት ፈተናዎች ጥቂቶቹ ናቸው ብዬ አስባለሁ። ለዚሁም አልሃምድሊላህ (ተመስገን) ማለቱ የተሻለ ነው።

እላይ ስለ አእመሮ ህሙማን የተብራራው በገሃዱ አለም በተለያዩ ምክንያቶች የአእምሮ እክል የገጠማቸው ለማሳየት ሲሆኑ ነገር ግን አሁን ባለንበት ዘመን እና አመለካከት ያወቁ መስሏቸው ታመው ያሳመሙን በርካታዎች ናቸው። ምንድን… ነበር የሚባለው ? አዎ… አውቆ አበድ ወይም ንክ እንበላቸው ? በእነዚያ…በእነርሱ ሰበብ በሃሳብ የነገር ሰረገላው ተሳፍሬ በመጓዝ ላይ ሳለሁ እህት ሚስጥረ አደራው የፃፈችው ትዝ አለኝ። ምን አለች መሰላችሁ ሚስጥረ አደራው አባባሏ በሀገራችን ያለውን ወቅታዊው ሁኔታና ዘመነኛውን ሰው በመታዘብ ያሰፈረችው ይመስላል። እንዲህ ብላ ነበር “ሁሉ ዳኛ ሁሉ ተከሳሽ” ህምም… እውነቷን እኮ ነው “እኛው ከሳሽ! እኛው ፈራጅ! እኛው ዳኛ”። እኛው ስለ ሀገራችን ተቆርቋሪ እየሆንን ሌሎች ሲቆረቆሩ ለምን እንላለን። እራሳችንን መውቀስ እና መተቸት ሳንችል በሌሎች ላይ የወቀሳ እና የትችት ናዳ እናወርድባቸዋለን። እናንተ… ሆዬ እንዴው እውነቱን ለመናገር ስለ ሰዎች ብንጠየቅ ብዙ ነገር እንፅፋለን እንተርካለን። ከአይናችሁ ጉድፍ አለ እንላለን። ስለራሳችን ግን ፍፁም… ከምንም እክል የፀዳ አይነት እንሆናለን ። በምንፈልገው የአላማ መስመር መጓዝ ስንችል ያልበላንን በማከክ ከንቱ ጊዜያችን እናባክናለን። በርግጥ የጊዜ ከንቱ ባይኖርም የከንቱዎች ጊዜ ግን ዋጋ ቢስ ነው። ሰልዚህ ከንቱና የጊዜ ከንቱ ሁሉም አንድ ናቸው። አዎን ከንቱ እርባና ቢስ…

ጎበዝ… ፍላጎትና አላማን ለማሳካት ፅናትን ይጠይቃል እኮ! ፅናት ደግሞ ዝም ብሎ አይመጣም። ብዙ መንከራተትና ፈተናዎች ይበዙበታል። ፈተናዎቹን ማለፍ ያሻል። ወይም በቀላሉ ከሱቅ የሚገዛ ሸቀጥ አይደለም። ተስፋ አስቆራጭም ነው ። ግና… የኋላው የተስፋ ጭላጭል ካለ ተስፋ መቁረጥ ጣጣ የለም። የበርካታዎቹ ስር ነቀል ችግር መጓዝ ያለባቸው ቀጥተኛ መንገድ እያለ ጠማማውን እና ጠመዝማዛውን ይመርጣሉ ። በርግጥ ሰዎች ወይም እነርሱ… እንደገባቸው ነው የኖሩት። እንዲሁም እየኖሩ ያሉት።

በሀገራችን በሚታየው ነባራዊ ሁኔታ ነፃነት ናፈቀን ስንል ኖረን ነፃነት ሲሰጠን የገዛ ወገናችንን መግደል፣ ማቁሰል፣ ቀዬ አስለቅቆ ለስደት መዳረግ፣ በንብረቱ ላይ ውድመት ማድረስ እና በእዚህ ሳያበቃ ንፁሀን ያለወንጀላቸው ታሰሩ ። ታዲያ ይህ ሁሉ ሲሆን ወይም ክሰተቱ እና ንጹሃኑን የማሳሰረ እና የማሰር ድራማው ከህዝብ አቅም እና ጆሮ የተሸሸገ አልነበረም። ብቻ እማማ ኢትዮጵያዬ በልጆችዋ ወዴት እያመራች እና እየተመራችበት የነበረችበትና ያለችበት አቅጣጫ መንግስት ነበር/አለ እንዴ ? የሚለው ከጥለቅ ስጋት ውስጥ ይከታል።

አንዳንዶቹ ፈላጭ ቆራጩ እኛው ነን በማለት ያለ እውቀታችን ወይም ምንም በሚባል የእውቀት ደራጃ ላይ ሆነን የላቀ እውቀት ያለቸውን ወይም የእውቀት ባለቤቶችን እንንቃለን። እንደ ሃይማኖተኛ የታዘዘውንና የተከለከለውን በቅጡ ሳንረዳ የሀይማኖት አባቶችን (ኡለማዎችን) ስንንቅና በመጥፎ ስናነሳ ይስተዋላል። ሰለ እምነቱ እና ስለ መጽሃፉ በትንሽ የተረዳው ደግሞ እንደዚሁ ያወቁትንና የላቁትን ሲንቅና ሲያመናጭቅ ተስተውላል። የመብት ተሟጋችና አክቲቪስቶች ባላዋቂዎች ሲተቹ ይውላሉ ። “የሆነው ሆኖ ትችት መድሃኒት ነው ! ለመልካምና በመልካም ከተቀመመ”።

ሌሎቹ ደግሞ ዝምታ መርጠው እና እውነታውን ይዘው “ይሻላል” ብለው የተቀመጡት ደግሞ ገንዘብ በይና ውሸታም ይደረጋሉ። እውነታው ግን ማን ጋር እንዳለ እነሱና ፈጣሪያቸው ብቻ ነው የሚያውቀው። አንዱ ከአንዱ ጋር እጅ ለእጅ በመያያዝ መከታ እና ጥንካሬ መሆን ሲችል ያለ… አቅሙ ለማፈረስ ይደራጃል። ለራስህ እወቅ ስትለው እራስህን ጣል ያልከው ያህል ይከፋዋል። እራሱን ጤነኛ አድርጎ ሌላውን እብድ የሚል ስያሜ ይሰጠዋል። በርግጥ እብዱ እና የተበላሸ አእምሮ ያለው ማን እንደሆነ ለመለየት ከብዷል። ሁሉም ካበደ ጤነኛው ከየት ይገኝና? “ከኑግ የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ” ይሉሃል እንዲህ ነው። ብቻ… ምን አለፋችሁ በሀገራችንም ይሁን በግል ህይወታችን ያሉ እውነታዎች እንደዚሁ ናቸው። እራሳችን ፍፁም አደርገን ሌሎችን ጭቃ እንቀባለን። ቢሆንም ቀቢ እና ተቀቢው ሁለቱ በጭቃ ይነኩ የለ? ሃሃሃሃ… ሁሉም… ጭቃ !!!

ኧረ… ጎበዝ ንቃ… ሳትንቃቃ! ለእነርሱ እና ለእኛ የሚያስፈልገን አንድነት ነው። አንድነት ሃይልም አይደል? 21ኛው ክፍለ ዘመን የልማት እንጂ የጦርነት ወይም አላዋቂነት እና የአላዋቂዎች መንፈላሰሻ ዘመን መሆን የለበትም ። እናም… ወዳጆቼ ሁሌም ቢሆን ለሰዎች ስም ከመስጠታችን በፊት “እኛ ማነን” ? እንበል!! በዙሪያችን ለሚከሰቱት ደህናና መጥፎ ጉዳዮች ሀላፊነት ይሰማን። በትንሽ በትልቁ እኛ ነን አዋቂ እና ፈላጭ ቆራጭ በሚል የቀን ቅዠት ውስጥ እየኖርን ጥቅምና ጉዳታችን እየለየን አይደለም። ለትርፍ ብለን የገዛነውን አክስረነው አንሽጠው። ማስዋልና ንቃት በራቀው ጉዞችን ለምን እንደከሰርን ስንጠየቅ ተራ እና የወረደ ምክንያት ይዘን አንገኝ። እናስብ…እናስተውል ምክሩን አልሰማ ካልክ ደግሞ “እንካ ይኸውለህ”… “እውር ቢሸፍት እሰከ ጓሮ ነው”። መአሰላማ…!


በSemu Bint Shifa

ሪያድ ሳዑዲ አረቢያ

39 views0 comments
bottom of page