top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

መደመር ወይስ መቀነስ ? (በመምህር ካሚል ሁሴን)


ምንም እንኳን መደመር የሚለው እሳቤ በጥሬ ትርጉሙ ጥሩ መልእክት የሚያስተላልፍ ቢሆንም አሁን… አሁን ላይ ሳስብው የሚያስፈልገን መደመር ሳይሆን መቀነስ የሚለው እሳቤ ይመስለኝል። ድሮ… ድሮ በልጅነታችን ሂሳብ መማር እንደ ጀመርን በመጀመሪያ የተማርነው መደመርን ነው። በርግጥ የሂሳብ ምሁራን ለምን ከመደመር እንደሚጀምሩ ባለውቅም እየቆየ ሲሄድ ግን ለእኛ ማህበረሰብ መጀመሪያ መደመርን ከማስተማር መቀነሱን ማስተማር የተሻለ ይሆናል ብዬ አምናለሁ።

እንደ ማህበረሰብ ወይም እንደ የሰው ዘር መቀነስ፣ ማጥፋት እና ማስወገድ የሚገባን በርካታ ችግሮች አሉብን። ለምሳሌ ሐሜት፣ ክፋት፣ ሸር፣ ሳይጣሩና ሳያረጋግጡ ማውራት፣ ብሔርተኝነት፣ መከፋፈል ወይም ማራራቅ፣ ውሃ ማባከን፣ ኤልክትሪክ ማባከን፣ አላስፈላጊ ወጪ ፣ ከስራ ሰአት ማርፈድን ፣ የስራ ሰአትን ያለአግባብ መጠቀምን፣ ውሸት፣ ችግርን፣ ረሃብን ፣ ጦርነትን፣ የባህል ብክለትን እና ተዘርዝረው የማያልቁ ለዘመናት ጠፍንገው የያዙን ብዙ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲታዊ ውስብስበ ችግሮችን ቢቻል እስከ ወዲያኛው ማስወገድ። የማይቻል ከሆነ ደግሞ መቀነስ እንዳለብን የውስጤ ደህናው ክፍል ሰርክ ይጎተጉተኛል።

የህክምን ባለሙያዎች ብዙውን ጊዜ ታመን ወደ ሆሰፒታል ስንሄድ ከሚያዙልን መድሃኒት በተጨማሪ አበክረው የሚያሳስቡን መጨመርን ወይም መደመርን ሳይሆን መቀነስን ነው። ታካሚው የስኳር ህመምተኛ ከሆነ ስኳርንና ሌሎች በርካታ ጣፋጭ ነገሮችን እንዲቀነስ ወይም እንዳይመገብ ይመከራሉ። ታካሚው የደም ግፊት ችግር ያለበት ከሆነ ደግሞ ጨው እና ጨዋማ ምግቦችን እንዲቀንስ ወይም እንደይመገብ ነው የሚያስጠነቅቁት። ሌላው ለብዙ ሃገራት የእድገት ማነቆ ከሆኑት ችግሮች ውስጥ በዋነኝት ከሚጠቀሱት ችግሮች አንዱ ሙስና (corruption) የተባለው አጥፊ ተግባር ነው። ይሁን እንጂ ሃገራት ይህንን አስከፊ ችግር ለማጥፋት ወይም ለማስወገድ ብዙ ቢጥሩም በተወሰነ መልኩ መቀነስ ቢችሉ እንጂ ማጥፋት አልተቻላቸውም።

ውድ አንባብያን የእስከ ዛሬውን አለም የደረሰችበት የስልጣኔ ደረጃና እና አመለካከት ወይም አስተሳሰብን በጥልቀት ወይም ረጋ ብለው ይመርምሩ… ያገናዝቡም ከዚያ በዃላ ከመደመር እና ከመቀነስ የሚያዋጣዎን ይምረጡ ! ጊዜው የምርጫ ነውና። ታዲያ ሲመርጡ የሚጠቅመውንና ደህናው ብቻ ይምረጡ። የሚጠቅመው የእኛ ወይም ከእኛ ወገን የሆነው ብቻ ሳይሆን ለሁሉም በእኩል መልካም አሳቢና ሰሪው ብቻ ነው። ይህንን ስል ዘረኛው ደህና ነው እያልኩኝ አይደለም። ስለ መቀነስ ብዙ ማለት ይቻላል። ነገር ግን በመደመር ዘመን እና የሳሳ ደስታ ውስጥ ስላለን የደስታንውን ድባብ ላለማደፍረስ ሲባል በተጠቀሱት ነጥቦች ብቻ ሃተታዬን እቋጫለሁ።

ወዳጆቼ ሆይ እላይ የተጠቀሱት ሃሳቦች የእኔና እኔ አመለካከት ብቻ ሲሆኑ በሌሎች ዘንድ ልክ… ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላል። ጊዜው የምርጫም አይደል? ከመረጡት ጋር ይሁኑ።


ሰላማችሁን ያብዛልኝ!


መምህር ካሚል ሁሴን

ሪያድ ሳዑዲ አረቢያ

75 views0 comments
bottom of page