top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ሥነ-ምግባር በሃይማኖት ወይስ በፍልስፍና? (ፍቃዱ ቀነኒሳ)


ማህበረሰብ ከሌለ ወግና ስርዓት አይኖርም፡፡ ወግና ስርዓት ከሌለ ደግሞ ነውር ወይም ክብር አይኖርም፤ ሥነ-ምግባር ደግሞ በማህበረሰብ ውስጥ ተቀባይነት ያለውንና የሌለውን ድርጊት መለየትና ነውር የሆነውን ድርጊት የማስወገድ ሂደት ነው፤ ስለሆነም ለማህበረሰባዊ ስነ ምግባር (morality) መከሰት የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ የማህበረሰብ መገኘት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ግለሰብ ባዶ ቤት ውስጥ ሙሉ ቀን ራቁቱን ቢዘዋወር ምንም ነውር የለውም፤ ነገር ግን ያው ግለሰብ ለአንድ ደቂቃ ያህል ከተማ ውስጥ እርቃኑን ቢዘዋወር እንደ “ነውረኛ” ወይም “እብድ” መቆጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ በሌላ በኩል ታላቁ አትዮጵያዊ ጸሐፊ ከበደ ሚካኤል በግጥማቸው “ጽድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም፤ ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም” ብለዋል፡፡

ወግና ስርዓት፣ ነውርና ክብር ስለክፋትና ደግነት፣ ጥሩነትና መጥፎነት፣ እንዲሁም ስለ ስነ ምግባር ጽንሰ ሃሳቦች ትክክለኝነትና ስህተትነት ምንነት፣መስፈርትና አስፈላጊነት የመሳሰሉትን ሃሳቦች የሚያጠና ዓቢይ የፍልስፍና ዘርፍ ሥነ-ምግባር (Ethics) ይባላል፡፡ ሥነ ምግባር “አንድን ድርጊት ጥሩ ወይም መጥፎ ብለን የምንመዝነው ከምን አንጻር ነው?” የሚል መሰረታዊ ጥያቄን ማብራራት ላይ ያጠነጥናል፡፡ በዚህ ሂደት ላይም “ጥሩ” ወይም “መጥፎ” ማለት ራሱ ምን ማለት እንደሆነና ሰዎች ለምን መልካም ምግባርን ለማድረግ እንደሚነሳሱ፣ “የሥነ ምግባር ጽንሰ ሃሳቦች በሁሉም ማህበረሰብ ውስጥ ወጥ ትርጉም ያላቸው ናቸው ከሚለው የሁሉንአቀፎች (universalist) አቋምና፤ ስነ ምግባር ከሰው ሰው፣ ከማህበረሰብ ማህበረሰብ ይለያያል ከሚለው የአንጻራውያን (subjectivist) እይታ አንጻር አመክኗዊ ማብራሪያ ይሰጣል፤ የስነምግባር ፍልስፍና፡፡ ሥነ-ምግባር የግለሰቦችን ማህበራዊ ኑሮ ከማስመሩም ባሻገር በሀገር ልማት አጀንዳ ላይ ታላቅ ስፍራ አለው፡፡

በአንድ ሃገር ውስጥ ሙስና፣ ስርዓት አልበኝነትና ወንጀል ከተንሰራፋ፤ እንዲሁም ዜጎች የሃገርን ክብር፣ የወገንን ፍቅር የማያውቁ ከሆነና ራስ ወዳድነት ከነገሰ፤ ግለሰቦች ለሃገር ልማት ምንም ዓይነት ቦታ ስለማይኖራቸውና ሃላፊነት ስለማይሰማቸው ለሀገራቸው ዕድገት እንቅፋት መሆናቸው የማይቀር ነው፡፡ ለዚህም ነው በራሳችን ሀገር ስነ ምግባር የጎደላቸው ዜጎች ለህዝብ አገልግሎትና ለሀገር ልማት የተመደበ በጀት ለግለሰቦች ጥቅም ሲውል፣ በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች፣ በቆሻሻ ሲደፈኑ፣ የቱቦዎቹ መሸፈኛ ብረቶች፣ የመንገድ ላይ ምልክቶች፣ በህዝብ ስልኮች ላይ የተገጠሙት ሶላር ፓኔሎች ፣ በመንግስት የትምህርት ተቋማት ህንፃዎች ላይ የሚገኙት ማብሪያ ማጥፊያና ሶኬቶች ተነቅለው ሲወሰዱ፣ በመንገድ ዳር የተተከሉ ዛፎች በለጋነታቸው ሲቀጠፉ፣ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ዕቃ ባለበት ሁኔታ ቆሻሻ በየቦታው ሲጣልና ይህን የመሳሰለውን ነውር በተደጋጋሚ መመልከትና መስማት የተለመደ እየሆነ የመጣው፡፡ የዜጎች በሥነ-ምግባር መዝቀጥ በግለሰቦች የዕለት ተዕለት ህይወትና በሀገር እድገት ላይ ሊያሳርፍ የሚችለው ጫና ከፍተኛ ነው፡፡

በመሆኑም ወላጅ ልጆቹን፣ የሃይማኖት መሪም ተከታዮቹን፣ መንግስትም ዜጎቹን በስነ ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ የማድረግ ቀዳሚ ሃላፊነት እንዳለበት መገንዘብ ይኖርበታል፡፡ ነገር ግን ትልቁ ፈታኝ ጉዳይ “ስነ ምግባርን እንዴት ማስተማር ይቻላል?” የሚለውን ጥያቄ መመለስ ይሆናል፡፡ ይህም ከሃይማኖታዊና ከፍልስፍናዊ ስነ ምግባር የማስተማሪያ አቀራረቦች መካከል የበለጠ ውጤታማ መሆን የሚቻለው በየትኛው መንገድ እንደሆነ ለማጥናት የሚሞክር ነው፡፡ ስለ ሥነ-ምግባር ምንነት፣ መኖር ወይም አለመኖር እንዲሁም መቼ እንደተጀመረና ስለ ሥነ-ምግባር የተሻለ የማስተማሪያ መንገዶች የሚሰጠው ምላሽ እንደየመላሾቹ ማንነትና እምነት በእጅጉ የተለያየ ነው፡፡ ለምሳሌ ፕሮታጎረስ የተባለው ሶፊስት (sophist) የግሪክ ፈላስፋ፣ የስነ ምግባር ጽንሰ ሃሳቦች ጥሩ ወይም መጥፎ ሊባሉ የሚችሉ አይደሉም፤ ጥሩነታቸውም ሆነ መጥፎነታቸው የሚወሰነው በድርጊቱ ፈጻሚ ግለሰብ ብቻ ነው፡፡

ስለሆነም ስነምግባርን ማስተማር አይቻልም፤ አያስፈልግምም ሲል፤ ትራዚማከስ ደግሞ ማንኛውንም ድርጊት ትክክል የሚያደርገው ኃይል (ገንዘብ ወይም ጉልበት) ነው “might makes right” ይላል፡፡ በሌላ በኩል ሶቅራጠስ የመልካም ስራ ምንጭ ዕውቀት፤ የክፋት ሁሉ ምንጭ ደግሞ አለማወቅ በመሆኑ ሰዎች መልካምነት ምን እንደሆነ ሲያውቁ ብቻ መልካም ይሆናሉ፤በመሆኑም በትምህርት የሰዎችን ስነ ምግባር ማሻሻል ይቻላል ብሎ ይደመድማል፡፡ የአፍላጦን ተማሪ አሪስጣጣሊስ “Nicomachean Ethics” በተባለው የስነ ምግባር ስራው ውስጥ ስነ ምግባር ሁልጊዜ በሁለት ጽንፎች መሃል የሚገኝ ድርጊት ነው ይላል፡፡ የስነ መለኮት ምሁራን የስነ ምግባርን ህግጋት በአምላክ የተሰጡና በፍጡራን ህሊና (በህገ ልቡና) ውስጥ በደመነፍስ የሚታወቁ ፍጹማዊና ሁለንተናዊ፤ በቦታና በጊዜ የማይቀያሩ ዘለዓለማዊ ሃሳቦች መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ የሰው ልጅም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ የስነ ምግባር ህግጋቱ አብረውት እንደነበሩ፣ ኋላም በየዘመናቱ በፍጡራን ልቡና ውስጥ የታተሙትን የስነ ምግባር ህግጋትን ለማደስ አምላክ የጽሁፍ ህግን እንደሰጠ፣ በነብያትና በሐዋርያት አድሮም እንዳስተማረ ያብራራሉ፤ የመለኮታዊ ትዕዛዝ (Divine Command theory) ንድፈ ሃሳብ አራማጆች፡፡

በሃይማኖታዊ ሥነ-ምግባር መርህ መሰረት፣ አንድ ድርጊት ጥሩ ወይም መጥፎ ተብሎ የሚፈረጀው ድርጊቱ በቅዱሳት መጻህፍት “አድርግ” ወይም “አታድርግ” ተብሎ ከመጻፉ ወይም ካለመጻፉ አንጻር እንጂ ጥሩ ወይም መጥፎ ለመሆኑ በሚቀርብ ዝርዝር ምክንያት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ምክንያቱ የሰውን ህይወት ለማዳንም ይሁን ለማጥፋት በሀሰት መመስከር ሁልጊዜ በማንኛውም ቦታ መጥፎ ድርጊት ነው፤ ምክንያቱም የአምላክ ቃል “በሀሰት አትመስክር” ይላልና፡፡ ሁለተኛው የሥነ-ምግባር ንድፈ ሃሳብ የስነ ምግባር ጽንሰ ሃሳቦችን የሰዎች ወይም የማህበረሰብ ስምምነት ውጤት (social contact theory) መሆናቸውን ይሰብካል፡፡

የዚህ ስነ ምግባር ንድፈ ሃሳብ ሊቃውንት ጆን ሎክና (Locke) ራውልስ (Rawls) የሰው ልጅ ራሱ በፈጠራቸው የስነ ምግባር ህግጋት ተገዝቶ ለመኖር ከመስማማቱ በፊት በተፈጥሮ እንዳለ (state of nature) ይኸውም ስለ ዘር፣ ብሄር፣ ጎሳ፣ ወሲባዊ ባህርይ ትክክል ወይም ስህተት የሚለውን ውሱን አስተሳሰብ ከመያዙ በፊት በኖረባቸው በነዚያ ዘመናት፤ ወይም ሃይማኖት፣ ህግ፣ መንግስትና ስነምግባር ህግ ባልነበረበት ሁኔታ በምን ዓይነት ትርምስና የማያቋርጥ ጦርነት ውስጥ ይኖር አንደነበር በምናባችን እንድንስለው በማድረግ ማሳመኛቸውን ይጀምራሉ፡፡ በዚህ የማያቋርጥ ጦርነት ብርቱዎቹ ደካሞቹን በኃይል በመርታት ንብረታቸውን ይዘርፋሉ፣ ነጻነታቸውን በመግፈፍ በባርነት ይይዛሉ፣ ህይወታቸውንም ያጠፋሉ፡፡

ነገር ግን ይህ ሁሉ ትክክል እንደሆነ ይቆጠር ነበር፤ ምክንያቱም ከኃይል በስተቀር የስነ ምግባርም ሆነ የፖለቲካ ህግ የለምና፡፡ እንደ ንድፈ ሃሳቡ አራማጆች ከዚህ ችግር ለመውጣት የሰው ልጅ በስምምነት መንግስትን፣ ህግን፣ የስነምግባር እሴቶችን መሰረተ፡፡ በመሆኑም ስነ ምግባርን ለማስተማር ስምምነቶቹ ለጋራ ጥቅም ያላቸውን ፋይዳና የስነ ምግባር ህግጋትን አለማክበር በጋራ ደህንነት ላይ ሊያደርስ የሚችለውን አደጋ ዜጎች እንዲገነዘቡት በማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ የሰውን ንብረት መስረቅ መጥፎ የሆነበት ምክንያት አምላክ “አትስረቅ” የሚል ትዕዛዝ ስለሰጠ ሳይሆን የጋራ ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ የማህበረሰቡ አባላት በአንድ ወቅት ስለተስማሙበትና ይህን የሚጥሱ ሰዎችን ነውረኛ አድርጎ ከማህበረሰቡ በማግለልና ክብር በመንሳት ለመቅጣት ስለወሰኑ ነው፡፡

ስምምነት የተደረገባቸው የስነ ምግባር ልማዶች አስፈላጊነታቸው ሲጎላና በማያከብሯቸው ሰዎች ላይ ጠንከር ያለ ቅጣት መጣል አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የስነ ምግባር ወጎችና ልማዶች ወደ ህግ ደረጃ እንዲድጉ ይደረጋል፡፡ በፍትሃብሄርም ሆነ በወንጀል ህግጋት ላይ የተከለከሉት አብዛኞቹ ህጎች መነሻቸው የማህበረሰቡ ነባር የስነ ምግባር እሴቶች ናቸው፡፡ ሶስተኛው የስነ ምግባር ንድፈ ሃሳብ፣ አንድ ድርጊት ጥሩ ወይም መጥፎ መሆኑ የሚታወቀው ድርጊቱ ከሚያስከትለው ውጤት (consequence) አንጻር እንጂ በራሱ ጥሩ ወይም መጥፎ የሚባል ድርጊት የለም የሚል ነው፡፡ ድርጊቱ በመጨረሻ ውጤቱ ጥሩ ከሆነ ድርጊቱ ጥሩ ነበር ማለት ነው፤ ነገር ግን ውጤቱ መጥፎ ከሆነ ግለሰቡ የተነሳበት ሃሳብ ምንም ይሁን ድርጊቱ በመጥፎነት ይፈረጃል፤ ይህም “The end justifies the means” ከሚለው ምሳሌያዊ አነጋገር ጋር የሚስማማ ነው፡፡

ለምሳሌ መዋሸት ለማስታረቅ ከሆነ መልካም፤ ሰውን ለመጉዳት ከሆነ ግን መጥፎ ድርጊት ሊሆን ይችላል፡፡ ሄዶኒዝም (hedonism) የዚህ ንድፈ ሃሳብ ዋነኛ መገለጫ ሲሆን ይህም አንድ ድርጊት ጥሩ ነው የሚባለው እርካታን የሚያስገኝ ከሆነ ብቻ ነው፤ መጥፎ የሚባለውም ስቃይ ካለው ነው የሚል መሰረተ እምነት የያዘ ነው፡፡ ለምሳሌ መስረቅ፣ ማመንዘር፣ መዝፈን፣ መስከር፣ ራስን ማጥፋት የመሳሰሉት ድርጊቶች እርካታን የሚያስገኙ ከሆነ ወይም ስቃይን የሚያስወግዱ ከሆነ በጥሩ ድርጊትነት ይፈረጃሉ፡፡ የዚህ አስተሳሰብ የመጨረሻው ጽንፍ ላይ የምናገኘው ኤፒኪውረስ (Epicurus) የተባለው የግሪክ ፈላስፋ፤ በዓለም ላይ ትልቁ የህይወት ግብ ሥጋዊ እርካታን ማግኘት ነው ይላል፤ በተለይ ከወሲብ ስሜት ጋር የተገናኘና ህሊናን የሚቃወም ዓይነት፡፡ የአንድን ድርጊት ጥሩና መጥፎነት ድርጊቱ ከሚያስከትለው ውጤት ወይም እርካታ አንጻር ስንመዝን የሚገጥመን ትልቁ ፈተና “ለማን ያስከተለው ውጤት/ ያስገኘው እርካታ” የሚለውን መወሰኑ ላይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የዚህ ንድፈ ሃሳብ አራማጆች በሶስት ጎራ ይከፈላሉ፡፡ የመጀመሪዎቹ “ለእኔ ባዮች” (egoists) ሲሆኑ እነዚህም ሰው በተፈጥሮው ራስ ወዳድ ስለሆነ የማንኛውም ድርጊት ጥሩነት ወይም መጥፎነት መለካት ያለበት ድርጊቱ ለአድራጊው ግለሰብ ከሚያስገኘው እርካታ ወይም ከሚያስከትለው ስቃይ አንጻር ብቻ ነው ይላሉ፡፡ እዚህ ላይ መገንዘብ የሚገባን ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ሌሎችን (ሃገርን፣ ወገንን) ከግምት የማያስገባ ስለሆነ እንደ ሃገር አደገኛ ፍልስፍና ነው፡፡

በዚህ ፍልስፍና የሚመራ ሰው ለሌሎች ደንታ ስለማይኖረው በሙስናና መሰል የራስ ወዳድነት አፍራሽ ተግባራት ከመሰማራቱም በላይ በድርጊቱ የአሸናፊነት እንጂ የጸጸት ስሜት አይኖረውም፤ ከስህተቱም አይታረምም፡፡ የማንኛውም ድርጊት ጥሩነት ወይም መጥፎነት መለካት ያለበት ድርጊቱ ከአድራጊው ግለሰብ ውጪ ላሉ ለሌሎች ሰዎች ከሚያስገኘው እርካታ ወይም ከሚያስከትለው ስቃይ አንጻር ብቻ ነው የሚሉ ደግሞ “ለወገኔ ባዮች” (altruists) ይባላሉ፡፡ በዚህ የሥነ ምግባር ፍልስፍና የሚመሩ ግለሰቦች ከራሳቸው ይልቅ ለሌሎች ወገኖች አብልጠው ስለሚያስቡ ለስነ ምግባር ብለው ህይወታቸውን አሳልፈው እስከመስጠት ይደርሳሉ፡፡ ኢትዮጵያዊው ሰማዕት ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ ሃገሬንና ህዝቤን ለጨካኙ የጣልያኖች አገዛዝ አሳልፌ አልሰጥም፤ አልክድም በሚል ህይወታቸውን ስለሃገራቸውና ስለወገናቸው ክብር አሳልፈው የሰጡትና ለሰማዕትነት የበቁት በዚህ የስነምግባር ፍልስፍና ይመሩ ስለነበር ነው፡፡

“ለእኛ ባዮች” (utilitarianism) የሥነ ምግባር ፍልስፍና የሚመሩ፤ ሥነ ምግባር ከሚያስከትለው ውጤት አንጻር ብቻ መመዘን አለበት የሚል አስተሳሰብ ከሚያራምዱ ግለሰቦች በሦስተኛ ደረጃ የሚቀመጡ ናቸው፡፡ የማንኛውም ድርጊት ጥሩነት ወይም መጥፎነት መለካት ያለበት ድርጊቱ አድራጊው ግለሰብ ጨምሮ ለብዙሃኑ ወይም በርካታ ቁጥር ላላቸው ሰዎች ከሚያስገኘው እርካታ ወይም ከሚያስከትለው ስቃይ አንጻር ብቻ ነው ብለው ያምናሉ፤ የ“ለእኛ ባዮች” የሥነ ምግባር ፍልስፍና አራማጆች፡፡ የዚህ ፍልስፍና መስራች እንግሊዛዊው ፈላስፋ ጀረሚ ቤንታም፤ አንድን ድርጊት ጥሩ ነው ብሎ የሚያምነው ድርጊቱ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው ሰዎች እጅግ ከፍተኛ ደስታ (እርካታ) የሚያመነጭ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ቤንታምና ተከታዮቹ አንድ ድርጊት የሚያመነጨውን የደስታ ወይም የስቃይ መጠን ለመለካት የሂሳብ ስሌት መጠቀም ይቻላል የሚል ማሳመኛ አቅርቧል፡፡ በዚህም መሰረት እንድ ድርጊት ከፍተኛ እርካታ ያመነጫል ማለት የሚቻለው ድርጊቱ ሊያመነጭ ከሚችለው ጠቅላላ እርካታ ላይ ድርጊቱ ሊያመጣ የሚችለውን ጠቅላላ ስቃይ በመቀነስ የሚገኘው የተጣራ እርካታ ሲሰላና ጠቅላላ እርካታው ከጠቅላላ ስቃይ የበለጠ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ሌላው ዓቢይ የስነ ምግባር ንድፈ ሃሳብ ኃላፊነት ተኮር (Duty Based theory) ይባላል፡፡

ከዚህ ንድፈ ሃሳብ መገለጫዎች አንዱ በሆነው የኢማኑኤል ካንት ህሊናዊ ትዕዛዝ (categorical imperative) የስነ ምግባር ማሳመኛ መሰረት፤ አንድ ድርጊት መልካም ወይም ክፉ መሆኑ የሚታወቀው ድርጊቱ በሚያስከትለው ውጤት ሳይሆን ግለሰቡ ድርጊቱን ለመፈጸም ከተነሳበት ውስጣዊ ምክንያት አንጻር ነው፡፡ መጀመሪያ በጎ ህሊና ይኑርህ፤ከዚያ ህሊናህ ትክክል ነው የሚልህን ነገር አድርገው፤ ጥሩ ስራ ነውና፤ ነገር ግን ህሊናህ የሚቃወምህ ከሆነ ክፉ ስራ ነውና አታድርገው ይላል፤ ካንት፡፡ ህሊናህ ትክክል ያለህ ነገር በርግጥ ትክክል መሆኑን ለመፈተሽ እንድትችል ትክክል ነው ብለህ ያሰብከው ነገር ከወርቃማው ህግ ማለትም “አንተ በሌሎች ላይ ልታደርግ ያሰብከውን ነገር ሌሎች አንተ ላይ ቢያደርጉብህ እንደምትፈቅድ ራስህን ጠይቅ” ይላል፡፡ “Act as if the principle on which your action is based were to become by your will a universal law of nature.” በሌላ በኩል ሰዎች ጥሩ ነገር ማድረግ ያለባቸው የሚመጣላቸውን በጎ ነገር አስበው ወይም የሚመጣባቸውን ክፉ ነገር ፈርተው ሳይሆን ያለምንም ውጫዊ ምክንያት መልካም ስራ መስራት እንዲሁ ሃላፊነታቸው ስለሆነ ብቻ (as an end in itself) መሆን አለበት የሚል ነው፡፡ በመጨረሻ የምናገኘው የስነ ምግባር ፍልስፍናዊ ንድፈ ሃሳብ የክፉ-ደግ ጥናት (virtue ethics theory) ይባላል፡፡ አንድ ድርጊት ጥሩ ወይም መጥፎ የሚባለው ከአድራጊው አንጻር ነው ይላሉ፡፡ ምድራችን በተቃራኒዎች የተሞላች እንደመሆኗ መጠን ሰዎችም ክፉ ወይም ደግ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

መጥፎ ሰዎች ስራቸውም ሁልጊዜ መጥፎ ሲሆን ጥሩ ሰዎችም ስራቸው ሁልጊዜ ጥሩ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ስነ ምግባርን ማስተማር የሚቻለው ጥሩ ሰዎችንና በጎ ስራቸውን በአንድ ወገን፤ክፉ ሰዎችንና መጥፎ ስራዎቻቸውን በሌላ ወገን በዝርዝር በማስጠናትና ተከታዮች በጎ ሰዎችን አብነት እንዲያደርጉና ክፉ ስራን እንዲያወግዙ በማለማመድ እንጂ ስለድርጊቱ ውጤት ወይም ምክንያት በማስላት አይደለም ይላሉ - የዚህ አስተሳሰብ አራማጆች፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የበርካታ ባህሎችና አስተሳሰቦች መናኸሪያ በሆኑ ሃገሮች ውስጥ አንድ የስነ ምግባር ፍልስፍናን ብቻ በመከተል ዜጎችን በስነ ምግባር ለማነጽ የሚቻል አይደለም፡፡ ይልቁንም የስነ ምግባር ጽንሰ ሃሳቦችን ከሚያስከትሉት እርካታና ስቃይ፣ከህሊና ፍርድና ከህግ እንዲሁም እንደየግለሰቡ የህይወት ፍልስፍና ከሃይማኖትም አንጻር በአመክንዮ ላይ ተመስርቶ ማስተማሩ በእጅጉ የሚመከር ነው፡፡


88 views0 comments
bottom of page