top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ቆንጆ ሆነሽ ታድጊያለሽ እንጂ አትወለጂም!


"ውበት የሚወለድ ሳይሆን የሚለመድ ነው"

የሚጥም መልክ፣ የሚጥም ሙዚቃ፣ የሚጮኽ ቀለም ፣ የተረጋጋ ስዕል የሚሉ የውበት አገላለለጾችን ሰምተው ይሆናል፡፡ እነዚህን አገላለጾች በድጋሚ ለአፍታ በአጽንኦት ቢመረምሯቸው ሙዚቃን በምላስ እንደመቅመስ፣ ቀለምን በጆሮ እንደመስማት፣ እንዲሁም ስዕልን በሰው ፀባይ እንደመግለጽ ነው። ስለ ውበት ስናነሳ በተለምዶ ከምንጠቀምባቸው ቆንጆ እና አስቀያሚ፤ ወይም የሚያምርና የሚያስጠላ ከሚሉት ቃላት ባሻገር ከላይ የጠቀስናቸውን ዓይነት ሌሎች ጽንሰ ሃሳቦች ጥቅም ላይ መዋላቸው ስለ ውበት ያለን ግንዛቤ፣ ምልከታና ግምገማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መምጣቱን ያመለክታል፡፡

ከመብላትና ከመጠጣት ባሻገር የሰው ልጅ እርካታን ከሚጎናጸፍባቸው መንገዶች አንዱ ውበት ነው፡፡ በየትኛውም ባህል ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች ውበትን ያደንቃሉ፤ ቆንጆ ሆነው መታየትን ይፈልጋሉ፤ ያማረ ነገርን ማየትንና መስማትን ይወዳሉ፡፡ ዓለማችን ስለውበት ብዙ ብላለች፤ በየዕለቱ ቀላል የማይባል ገንዘብ ውበትን ለመጠበቂያ ታወጣለች፡፡ በየወቅቱ ቄነጃጅቱን እያወዳደረች ትሸልማለች…ሌላም ሌላም፡፡ ለመሆኑ ውበት ምንድን ነው? ውበት በምን መስፈርት ይለካል? በምን ቋንቋ ይገለጻል? ውበት ከሥነ-ምግባር ምን ዝምድና፤ ከሃብት ጋርስ ምን ግንኙነት አለው? ሥነ-ውበት (Aesthetics) የውበትን ጽንሰ ሃሳብ ምንነት፣ እሴቶች፣ አተያዮች እንዲሁም የመገምገሚያ መስፈርቶችን የሚያጠና ዐቢይ የፍልስፍና ዘርፍ ሲሆን የዛሬው ጸሁፌ ዋና ዓላማም ስለ ውበት አጭር ሐተታ ማቅረብ ይሆናል፡፡ የሥነ-ውበት ፈላስፎች ውበት የሚለው ጽንሰ ሃሳብ በአጠቃላይ የሰው ልጅን፣ ኪነ-ህንጻን፣ ስዕልን፣ ሙዚቃን፣ ቅርጻ-ቅርጽን፣ ቲያትርን፣ ስነጽሁፍን፣ ፊልምንና የመሳሰሉትን የሰው ልጆች የጥበብ ስራዎች፤ እንዲሁም የተፈጥሮን መስህቦች አካቶ የሚያጠና ዘርፍ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ውበት ማለት የአንድ ነገር የሚስብ፤ የሚያረካ ወይም የሚያስደስት ገጽታ ወይም ሁኔታ ማለት ነው። ውበት ውጫዊ ቅርጽን፣ ቀለምን፣ መጠንን፣ መልክን ወይም ደምግባትን (pure aesthetics) የሚያመለከት አልያም ውስጣዊ ማንነትንና ሥነ-ምግባርን (moral) የሚመለከት ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን አስቸጋሪው ጥያቄ ማንን የሚስብ፣ ማንን የሚያስደስት ወይም የሚያረካ የሚለው ነው - የውበቱን ባለቤት? ማህበረሰቡን? ማንን? የዓለማችን ሊቃውንት እነዚህን መሰረታዊ የሥነ-ውበት ጥቄዎች ለመመለስ በሁለት ታላላቅ ጎራ ተሰልፈው ለበርካታ ዘመናት ተሟግተዋል፤ መጻህፍትን ጽፈዋል፤ የሰው ልጆችን የአስተሳሰብ አድማስም አስፍተዋል፡፡ በመጀመሪያ የምናገኘው የሁሉን አቀፎች (universalists) ወይም የፍጹማውያኑን ርዕዮተ ዓለም ሲሆን ይህም ውበት መለካት ያለበት ነገሮቹ በራሳቸው ባላቸው ማንነት እንጂ ከእነርሱ ውጪ በሚገኝ ማንኛውም ነገር ላይ ማለትም በማህበረሰቡ ወግ፣ አመለካከት ወይም እምነት ላይ ተመስርቶ መሆን የለበትም የሚል አቋምን የሚያራምድ ነው፡፡

በፍጹማውያኑ ፍልስፍና ውበት በቦታና በጊዜ የማይለዋወጥ በሁሉም የሰው ልጆች ዘንድ በተመሳሳይ ሁኔታ የሚገኝና አንድ ወጥ መስፈርት የሚተገበርበት (objective) ነው፡፡ እንደነዚህ ፈላስፎች እምነት፤ አንዲት ሴት በአንድ ሃገር በሆነ ወቅት ቆንጆ ከተባለች በየትኛውም ዘመን፣ በማንኛውም ቦታና ባህል ቆንጆ ናት ማለት ነው፤ ይህን ለማለት ካልደፈርን ግን ስለሴቲቱ ቁንጅና በርግጠኝነት መናገር አልቻልንም ማለት ነው፤ ወይም ቆንጆ አይደለችም እንደማለት ነው፤ ወይም ቁንጅና የሚባል ሃሳብ የለም ማለት ነው። በሌላ በኩል አንድ የሥነ-ጥበብ ወይም የኪነ-ህንጻ ሥራ ያማረ ነው ካልን በማንኛውም ቦታ፣ በየትኛውም ዘመንና ባህል ቢመዘን እኩል ውብ ሆኖ ይገኛል ማለት ነው፡፡ ሁሉን አቀፍ ፈላስፎች ውበት በአጠቃላይ የራሱ የሆነ አለምአቀፋዊ መለኪያ መስፈርት ያለው ጽንሰ ሃሳብ መሆኑን ይቀበላሉ እንጂ ስለመስፈርቱ ምንነት ወጥ አቋም የላቸውም፡፡

እንደ አብዛኛዎቹ የሁሉን አቀፍ እምነት አራማጆች ማሳመኛ የማንኛውንም ነገር ውበት መለኪያ አመክኗዊ መስፈርቶች ሥርዓት (harmony)፣ ጆሜትሪያዊነትና (geometricness)፣ ወደረኝነት (proportionality) ናቸው፡፡ ለምሳሌ የህንጻ ግንባታ ተጠናቆ እንደተረከብክ የዋናውን መኝታ ክፍል ውበት ገምግመህ አስተያየት እንድትሰጥ ብትጠየቅ በጂኦሜትያዊነትና በወደረኝነት ቀመር የክፍሉ የወለል ስፋት ከጣራው ቁመት ጋር ወደረኛ ከሆነ፣ የክፍሉ ግድግዳዎች እንዲሁም በሮቹና መስኮቶቹ አንድ የታወቀ ጆኦሜትሪያዊ ቅርጽ እንዲኖራቸው ተደርጎ ከሆነ፣ እንዲሁም በሥርአት መርህ ክፍሉ የተቀባው ቀለም ከተገነባበት ዓላማና የብርሃን ጽምረት እንጻር በተገቢው መንገድ ተመርጦ ከሆነ የሚያምር ክፍል ነው ለማለት ይቻላል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ አንድ ግለሰብ የግንባሩ፣ የዓይኑ፣ የአፍንጫው ወይም የከንፈሩ መጠን ከጠቅላላው የፊቱ ስፋት ጋር፤ እንዲሁም ቁመቱ ከክብደቱ ጋር ወደረኛ ከሆነ፤ የአካል ክፍሎቹ አቀማመጥ ጂኦሜትሪካል ከሆኑና በአጠቃላይ የሰውነት ክፍሎቹ በተለመደው ተፈጥሯዊ ሥርኣት ከተደረደሩ ቆንጆ ነው ለማለት ይቻላል፡፡

ከነዚህ ባሻገር በተለይ እንደ ስዕል፣ ቅርጻ ቅርጽ፣ ፊልም፣ ቲያትር፣ ሙዚቃ የመሳሰሉት የጥበብ ስራዎችን ለመገምገም መጠቀም ስለሚገባን መስፈርት ከጥበብ ስራዎቹ በአፍ የሚገኝ የተመልካቾችና አድማጮች ስሜትና አመክኗዊ ግብረ መልስ መሆን እንዳለበት ይሞግታሉ፤ሌሎች የዘርፉ ምሁራን፡፡ የጥበብ ስራው ከሚሰጠው ተዝናኖታዊ ወይም አስተምህሮታዊ ፋይዳ፣ ከስራው ወጥነት (originality)፣ የራስን ማንነትን ከማንጸባረቅ ወይም አዳዲስ ስልት ከማስተዋወቅ አንጻር ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ድምጻዊ ጥላሁን የተጫወተውን ዜማ ድምጻዊት ዘሪቱ አስመስላ በድጋሚ ብትጫወተው የዘፈኑን ውበት መለካት የሚገባን በአዘፋፈናቸው ብቃት፤ ወይስ ከስራው ቅጂነትና ወጥነት አንጻር ነው የሚለውም ሌላው የሁሉን አቀፎች ርዕዮተ ኣለም መገለጫ ነው፡፡ ሃሳባውያን (idealist) ፈላስፎች በሁሉን አቀፎች አስተሳሰብ ከሚመሩ ሊቃውንት ይመደባሉ።

ለምሳሌ ታላቁ የግሪክ ፈላስፋና የሂሳብ ሊቅ ፓይታጎረስ በዓለማችን ላይ ሥርዓትንና (harmony) ወደረኛነትን (proportionality) ለመሳሰሉ ሃሳቦች መሰረታቸው ቁጥሮች መሆናቸውን ይናገራል። በዚህም ሙዚቃዊ ውበት በቁጥር ፍልስፍና ውስጥ እንደሚገለጽ በተለያየ መንገድ ለማስረዳት ሞክሯል፡፡ ለምሳሌ አንጥረኛው የጋለውን ብረት በመዶሻ ሲደበድበው የሚሰማው ድምጽ በቁጥሮች ቀመር ከተደረደረ ከመዶሻው ክብደት ጋር ተዋህዶ የሚወጣው ድምጽ ጣዕም ያለው ሙዚቃዊ ቃና ሊኖረው እንደሚችል ማለት ነው፡፡ ሌላው የፓይታጎረስ ተከታይ ፕሌቶ በዚህ ዓለም የሚገኙና በስሜት ህዋሳቶቻችን በምናገኘው መረጃ የምንገነዘባቸው ነገሮች በሙሉ በአወቃቀራቸው ግዙፋን፣ ህጸጽ ያለባቸው፣ የሚለዋወጡ፣ የሚከፋፈሉና የተለያዩ ስለሆኑ የውበትን እውነተኛ ምንነት የሚያንጸባርቁ አይደሉም ይላል፡፡ በሌላ በኩል በሃሳባዊው ዓለም የሚገኙ ነገሮች (Form) ረቂቃን፣ የማይለዋወጡ፣ የማይከፋፈሉ፣ ምንም ህጸጽ የሌለባቸውና ፍጹማን ስለሆኑ የሚታዩና የሚጨበጡ ግዙፋን ነገሮች እውነተኛ ውበት የሚታወቀው በረቂቁ ሃሳባዊ ዓለም (ideal world) ካላቸው ምስል ጋር በማነጻጸር ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ሰው የሥጋና የነፍስ ውሁድ ስለሆነ የአንድ ሰው የሥጋ ውበት የሚታወቀው የግለሰቡ ነፍስ ባህርይን ከሥጋው ማንነት ጋር በማነጻጸር በሚገኝ መስተጋብር ነው፡፡

አንድ የክብ (circle) ስዕል ቆንጆ ክበብ ነው የምንለው ስዕሉ በሃሳባችን ውስጥ ከሚገኘው ፍጹም እውነተኛ ክብ ስዕል ጋር ከሚኖረው ቅርበት አንጻር ነው፡፡ የአስራ ሰባተኛው ክፍለዘመን ጀርመናዊ ፈላስፋ ኢማኑኤል ካንት፤ ውበትን ከሥነ-ምግባር ጋር ያያይዘዋል “Beauty is a symbol of morality” ይላል:: ካንት በሥነ-ምግባር ፍልስፍናው ውስጥ በሚመራበት የcategorical imperative መርህ እንደ ስነ-ምግባር ጽንሰሃሳቦች ሁሉ ውበት መለካት ያለበት በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ በሚያስከትለው አወንታዊ ወይም አሉታዊ ውጤት ሳይሆን በራሱ ብቻ (as an end) ነው ይላል፡፡ ይህም ማለት ውበት የሰው ልጆችን ሁሉ በአንድነት የሚያግባባ የጋራ ቋንቋ እንጂ እንደማህበረሰቡ ስሜት የሚፈስ ጅረት አይደለም ማለት ነው፡፡ በፀሀይ ግባት ወቅት አድማስ ላይ የሚፈጠረው ውበት (sunset) በማንኛውም ማህበረሰብ ውስጥ የሚገኙ ህዝቦች ዘንድ በጋራ ሊደነቅ የሚችል የተፈጥሮ ውበት ሲሆን ከዚህም የሚገኘው ደስታ በራሱ የመጨረሻ የእርካታ ምንጭ (end) ነው እንጂ ይሄ ውበት ከማህበረሰብ ሊገኝ ወደሚችል ሌላ ደስታ የሚመራ መንገድ (means) አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንዲት ሴት ተረከዙ በጣም ረጅም የሆነ (heel) “ቆንጆ”፣ ነገር ግን የማይመች፣ ጫማ መጫማቷ ቆንጆ ጫማ አድርጋለች አያስብላትም- እንደ ካንት እምነት፡፡

ምክንያቱም በጫማው ልታገኝ ያሰበችውን ደስታ የምታገኘው በቀጥታ ከጫማው ሳይሆን የጫማውን ዋጋ ወይም ማህበራዊ ፋይዳ ከሚገነዘቡ አካላት አድናቆትና አክብሮት በመሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው የሥነ-ውበት ፈላስፎች ጎራ የአንጻራውያን (relativists) ጎራ ይባላል፡፡ ከሁሉን አቀፎች በተቃራኒ አንጻራውያን ውበት የሚለካበት አንድ ወጥ መስፈርት መኖሩን አይቀበሉም። ይልቁንም “ውበት እንደተመልካቹ ነው” እንደሚባለው ለአንድ ግለሰብ ውብ የሆነው ነገር ለሌላው አስቀያሚ ሊሆን ይችላል የሚለውን ሃሳብ የሚደግፉ ናቸው፡፡ አንጻራውያን ማንም ሰው ቆንጆ ወይም መልከ ጥፉ ሆኖ አይወለድም፡፡ በተፈጥሮ የሚያምር ወይም የሚያስጠላ ፍጡርም ሆነ የሰው የጥበብ ስራ የለም፡፡ ውበት የሚወለድ ሳይሆን የሚለመድ ነው፡፡ ለምሳሌ የሴት ልጅ ውፍረት በአንዱ ባህል እንደ ውበት ሲቆጠር በሌላው ደግሞ እንደ ውርደት ሲቆጠር አስተውለን ይሆናል።

“ቆንጆ ሆነሽ ታድጊያለሽ እንጂ አትወለጂም!” የሚለው የጽሁፌን ርዕስም በአንጻራውያን እይታ ለአንዲት ሴት የጸጉር መርዘም፣ የአፍንጫ መሰልከክ ወይም የወገብ መቅጠን የውበት ምልክት እንደሆነ የነገራት ያደገችበት ማህበረሰብ እንጂ ከማህበረሰቡ ተጽእኖ ውጪ እነዚህ መስፈርቶች ምንም ናቸው የሚለውን ሃሳብ ለማጉላት የመረጥኩት ነው። በተመሳሳይ ከአንድ ዓመት በፊት ስለውበቱ በሰፊው የተነገረለትና በርካታ ሰዎች የገዙት አንድ ፋሽን ልብስ ወይም ጫማ ዛሬ አስቀያሚና ለመልበስም አሳፋሪ ሆኖ መገኘቱ፤ እንዲሁም የአንድ ሙዚቃ አልበም ወይም የስነጽሁፍ ሥራ ውበት በተሸጠው ወይም በተሰራጨው የኮፒ ብዛት (best selling) አንጻር መወሰኑ ባለንበት ዘመን ውበት ምን ያህል በማህበረሰቡ አስተሳሰብ ተጽዕኖ ስር እንደወደቀ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በመሆኑም ውበት ላይ ተመስርተን ማንኛውንም ዓይነት ውሳኔ ከመወሰናችን በፊት ስለውበት የጠራ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል እላለሁ፡፡


ፍቃዱ ቀነኒሳ

(በአዳማ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር)

37 views0 comments
bottom of page