top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

በአንድ እጅ አይጨበጨብም - ክፍል ሁለት (በእሙ ኢሳን)


ከቀደምት ታሪካችንና ባለስልጣናት የተማርነው ወይም የወረስነው በስልጣን እርካብ ላይ የነበረውን በሃይል ካስወገደ በዃላ በደም በተጨማለቀ የስልጣን ወንበር ላይ ተቀምጦ እኔ ለሃገሬ እንዲህ እያሰብኩ ነው ከማለትና ከመሰማት ያለዘለለ የማይዳሰስ ውጤት አልባ ብቻ ልፈፋ የነበረ ሲሆን ከሁለት መንፈቅ በፊት ግን እጅግ በተለየ መልኩ ክብርን ለህዝብ ሰጥቶ፣ የፍቅርን እጅ በፈገግታ ዘርግቶ እና የህዝብን ህመም ተጋርቶ የነገን መልካም አየር እንተነፍስ ዘንድ ችግኝ በመትከል በጭቃ የተጨመላለቁ እጆችን ማየት እና ደም ከማፍስስ ይልቅ ደም በመለገስ የሚታወቀወ መሪ ማግኘቱ ምንኛ መታደል ነው። ታዲያ ምን ዋጋ አለው “በአንድ እጅ አይጨበጨብም” አንድ እጅ ብቻውን የሚሰራው የለም። ለሰው ሰው ያስፈልገዋል።

በየትኛውም የአለም ክፍል እንሰሳ እንኳን በጀመዓ ወይም በመንጋ ነው የሚኖሩት ከመንጋው ተነጥሎ የሚሄድ በአውሬ ይበላል። ስለዚህ እሱም ከመንጋው ተነጥሎ ብቻውን ምንም አያደርግም። በህብረት ያድናሉ በህብረት ይበላሉ። በተጨማሪም በህብረት ይኖራሉ። የዘመናችን ሰዎች ግን በህበረት ይታያሉ ነገር ግን ለብቻቸው ይበላሉ። ለመብላት ሲያስቡ ከመንጋው በመለየት አላስበላ ወይም ለመጋራት የመጣውን ያስወግዳሉ። በዚህ ዘመን ያፈራናቸው መልካምና የፈጣሪ ጸጋ የሆኑት ውስን ሰዎች ካጣናቸው ምናልባትም እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎችን መልሶ ለማግኘት 20 እና 30 አመት ይፈጅብናል። ይህ ማለት ደግሞ ሃገራችን በአመለካከት ማደግ ከሚገባት 20 አመት ባለችበት ቆማለች ወይም ወደ ዃላ ትሄዳለች ማለት ነው።


ወገኖቼ ሆይ… ያለፈው አልፏል ግን ለነገው ወይም ለማይዘልቀው ስልጣን ብለን የሚገዳደሩንን ከማስወገድ ይልቅ ልዩነታችንን አጥብበን፣ የሌላውን መብትና ፍላጎት አክበረን በመልካም አስተሳሰብ ተደራድረን መስማማት ችለን ቢሆን ኖሮ በእኔነት ልክፍት የጠፋው የሃገር ሃብት እና የተማረ ጭንቅላት በከንቱ አይባክንም ነበር። ዛሬም ቢሆን አልመሸም ከስህተታችን ታርመንና በአንድ እጅ እንደማይጨበጨብ ከተረዳን ኢትዮጵያ የሙህር ድሃ አይደለችምና በርካቶች ሃገርን የመምራት እና በደህና ወደ ደህና የመቀየር አቅም ያላቸውን ታላላቅ ሰዎችን ያፈራች ሃገር እንደ መሆንዋ መጠን ዛሬም ቢሆን በእኔነቱ ልክፍት ያልተለከፉ ውስንና የተሻሉ ምሁሮች እና ያለ ቦታቸው የተከሰቱ አዋቂዎች አሉን። ነገር ግን ትልልቅ ሰዎች እንጂ ታላላቅ ሰው በጠፋበት በዚህ ዘመን ያሉን ከእንቁ የላቁ ውድ የሆኑት ታላላቅ ሰዎቻችን ከማለፋቸው በፊት ካልተጠቀምንበታቸው እጣ ፈንታችን በየትምህርት ተቋማት ተሰግስገው የሚገኙና ልክ ከአንድ ማሽን ለአንድ አላማ ብቻ የተፈበረኩ በሚመስሉት እና በእኔነቱ ህመም ተጠቂዎች እጅ ላይ መውደቅ ነው የሚሆነው። ስለ እዚህ የመለወጫ እና መልካምን የመቀበያ ጊዜው አሁን ነው። “በእጅ የያዙት ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል” ይሉ ነበር ቀደምት ቤተሰቦቻችን። የገባው ብቻ ይገባዋል!


ቸር... እንሰንብት !

እሙ ኢሳን

ሪያድ ሳውዲ አረቢያ

51 views0 comments
bottom of page