top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

“ባለ…ቀን” (በእሙ ኢሳን )


ሶስት ሰዎች እስር ቤት ገብተዋል። አንደኛው ለሌላኛው ምን አድርገህ ነው የታሰርከው ሲለው “መንግስቱ ሃይለማርያምን ደገፌ ነው” አለ። ወደ ሌላኛው ዘወር ብሎ አንተኛውስ ሲለው “እኔ መንግስቱን ነቅፌ ነው” አለ። ለሶሰተኛው አንተስ ቢለው “እኔ መንግስቱ ነኝ” አለ። ወዳጄ ሆይ ደገፍክም፣ ነቀፍክም ፣ ተቃወምክም ወይም ባለቤቱም ሁን ለሌላው ፍጆታ እና ፍላጎት ሲባል ብቻ ወይም በጎጠኛውና በመንጋው አለም ወንጀል ባትሰራም ወንጀለኛ ነህ።

የሰው ልጅ በሰውነቱ ብቻ የራሱ የሆነ ጥሩ እና መጥፎ ጎን አለው። ታዲያ አጼዎቹ ቢሆኑም ጥሩውንም መጥፎውን ሰርተው አልፈዋል። ኢማም ግራኝ አህመድ በገሚሶቹ ዘንድ በመልካምነታቸው ሲታወሱ በሌሎቹ ዘንድ ግን ወራሪ ተብለው ይፈረጃሉ። የሆነው ሆኖ 60% ጥሩ 40% መጥፎ ቢሆኑ እንኳን በ100% መጥፎነታቸው ተባዝቶ በመጥፎ ሲታወሱ ይኖራሉ።


በእዚህኛው ትውልድ አእምሮ ውስጥ እንደየፍረጃቸው እና አቅማቸው ቢለያይም ለብዙ አመታት ወደ ዃላ ተመልሰን ዛሬ እና የዛሬውን ትውልድ ተወቃሽ የምናደርገው ለምንድ ነው? ቅድም አያቴ ለሰረቁት እኔ ሌባ ልባል አልችልም። ወይም በአያቴ ወንጀል እና መጥፎ ስራ የምጠየቅበት የህግ አግባብ የለም። ፖለቲከኞቹ እና እውነቱ ያለተገለጸላቸው ብዙሃን እንደሚናገሩት ሚኒሊክ ጡት አልቆረጡም ወይም ኢማም አህመድ ወራሪ አልነበሩም። እነዚያ ቀደምት መሪዎች ዘግናኝ የሆነ በደል ፈጽመዋል ተብሎ የሚተረከው በየትኛው መጽሃፍ ተጽፎ ነው የሚገኘው? ተጽፎ እንኳን ቢገኝ ታሪክ በእራሱ አወዛጋቢ አይደለምን? በማህበራዊ ሚድያዎች እንደሚታየው ጥራዝ ነጠቅ እውቀትን ይዘን ድምዳሜ ላይ ከመድረስ ለምን፣ መቼና የት ብለን የታሪክ ምሁራንን ብንጠይቅ ወይም የታሪክ መዛግበትን ብናገላብጥ ለሰላማችን፣ለጤንታችንና ለኑሮአችን ስኬት እና እድገት ትልቅ እገዛ ያደርግልናል። የታሪክ መዛግብት ማገላበጡ መረጃዎችን ለማግኘት የሚረዳን ሲሆን ሁሉም በታሪክ መጽሃፉ ላይ የተቀመጡት መረጃዎች ትክክል እና እውነተኛ ናቸው ማለቱ የሚከብድ ነው። በሃገራችን ያሉት የታሪክ መጽሃፍቶች ተጽፈው የነበሩት በእምነት ተቋማት እና በነገስታቶቹ ተጽእኖ ስር ሆነው ነው ። የሚገርመው ከመቶ አመት በፊት ምን ተደረገ እያልን ወደ ዃላ ተመለሰን በከንቱ ከምንዳክር ቆም ብለን በሰከነ መንፈስ እራሳችንን፣ ቤተሰባችንን እና ኑሮአችንን እንዲሁም ሃገራችንን እንገንባ። ለዘመናት ጠፍንጎን ከቆየው ድህነት ለመላቀቅ ከዃላ ቀርና ከወፍ ዘራሽ አመለካከት ራስን ማላቀቁ የግድ ይላል። ትልቁ ጠላታችን እኮ ድህነት ነው። ሃብቱና እውቀቱ ቢኖረን ኖሮ ሲጀመር ለፖለቲካ ፍጆታቸው ባላዋሉን ነበር። “እውቀት ቢኖረን” ብዬ ያልኩት ከትምህርት ተቋም የተመረቀ ለማለት አይደለም። ያወቀ እና ጤነኛው የሌላውን ሰላም አያደፈርስም። ያወቀ የራሱን መብት ሲያስከብር የሌሎችን መብት አይነካም። ከእዚህ ቀደም የተከሰቱት ያወቁ ቢሆኑ ኖሮ ዛሬ ላይ መልሶ በመክፈሉ አይጠመዱም ነበር። “በሰፈሩት ቁና መሰፈሩ አይቀርም ይሉሃል የዚህ አይነቱ ነው”።


በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በማህበረሰብ እና ግለሶቦች ላይ የተፈጸሙት በደሎች አስተማሪዎች የነበሩ ሲሆን ወደ አጼዎቹ ቀርቶ ወደ ደርግም ሆነ ትላንት ስለ ተከሰተው የቂሊንጦ ጫፍ መመለስ የሚፈልግ አንድም ሰው የለም። ሁሉም ባለቀኖች የሰሯቸው ጥሩና ደካማ ጎን አላቸው። ሰው “እንደታየው” ሆኖ እንጂ ዛሬም ቢሆን ባለው አገዛዝ ግማሹ በዳይ ሲሆን የተቀረው ደግሞ ተበዳይ ነው። የትኛውም ባለቀን በስልጣን ዘመኑ የሚጥለው አሻራ አለው። ለግማሹ ህዝብ ጥሩ ለሌላው ደግሞ መጥፎ ሆኖ የሚያልፍበት ብዙ የታሪክ አጋጣሚዎች ነበሩ(አሉ)። ነገር ግን ወደድክም ጠላህም ያው… ባሉት ባለቀኖች እስከ ቀናቸው ድረስ ትተዳደራለህ ስለዚህ የተቀጣጠለውን እኩይ አመለካከት ከምናራግብና ከምናፋፍም ቀናችን ይረዝም ዘንድ እኒያ… መሪ ይህንን መጥፎ ፈጽመዋል ወይም አስፈጽመዋል ለምንለው ግፍ ዛሬ ላይ አዲሱን ትውልድ ዋጋ ክፈል ብለን ተረት ተረት ባናወራ ይሻላል ባይ ነኝ ። አለበለዚያ ግን አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ አይነት ነው።


ጎበዝ… ሁል ጊዜ ትላንትን እያጠፋን ዛሬን ለመገንባት የምንጥር ከሆነ ሁሌም ቢሆን ከዜሮ እና ዜሮ ነው የምንኖረው። ስለዚህ ትላንትን እንደ ትላንት ተቀብለን ዛሬን በዛሬነቱ አስተናግደን ሃገራችንን ለማበልጸግ ብዙ ይጠበቅብናል። የትላንቱ አሻራ ለዛሬው ትውልድ የወደፊት እጣ ፈንታ መሰረት ሲሆን ደህናው ለማስቀጠል እንዲሁም መጥፎን ለማስተካከል ከሁሉም ጋር በእኩል መስራቱ ብቻ ነው የሚበጀው።

አንተ… ባለቀን ሆይ የትላንቱን ለመድገም ከሻህ… ያንተው እጣ ፋንታ የትላንቱ እራሱ ነው የሚሆነው።

ማስተዋሉን ይስጠን… ይስጣችሁ!


እሙ ኢሳን

ሪያድ ሳኡዲ አረቢያ

100 views0 comments
bottom of page