top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ንዴትን እንዴት መቆጣጠር ይቻላል?

ንዴትን እንዴት መቆጣጠር ይቻላል?

ተናዶ የማያውቅ ሰው አሳዩኝ እና አምጣ የወለደች በቅሎ አሳያችኀለሁ፡፡ ሁላችንም የሆነ አጋጣሚ ላይ እንናደዳለን፡፡ ልዩነቱ ንዴትን የምንቆጣጠርበት መጠን ነው፡፡ ተናደን የምንወስናቸው ውሳኔዎች ጊዜ ሲያልፍ ዋጋ ያስከፍላሉ፡፡ ዋጋው፦ ጊዜ ማባከን፣ እንቅልፍ ማጣት፣ ከሚወዱት ሰው መቆራረጥ፣ መታሰር...ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡


ንዴትን ለመቆጣጠር የሚረዱ የተወሰኑ ነጥቦች እነሆ፦

1. መናደዳችንን መቀበል-

እንዳልተናደድን ለማስመሰል መሞከር ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ የሚያናድደንን ሁኔታ እንዴት እንደምንለውጥ እንዳናስብ ከማድረግ አልፎ ለአእምሮ ጤንነታችን፣ ለጨጓራችን እንዲሁም ለደም ግፊታችን ጥሩ አይደለም፡፡ መናደዳችንን ስንቀበል ራሳችንን ማረጋጋት እንችላለን፡፡ ( "የማናውቀውንና የማንቀበለውን ችግር መለወጥ አንችልም፡፡" የሚለው አባባል በግልባጩም ትክክል ነው፡፡)


2. ዘርዝሮ መመልከት-

መናደዳችንን ከተቀበልን በኃላ ለምን እንደተናደድን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ቢቻል የተፈጠረውን ነገር ብንፅፈው የበለጠ ግልፅ ይሆናል፡፡ መፍትሄውም እንደዚያው፡፡ ስንዘረዝረው አንዳንዶቹን ችላ ብለን ማለፍ ያለብን ሌሎቹ ደግሞ ከመርሀችን ጋር ስለሚጋጩ ለመለወጥ የሆነ ነገር ማድረግ ያለብን እንደሆኑ እንረዳለን፡፡ ሁለቱን እንዳናቀያይር በዝርዝር ማየቱ ጥሩ ነው፡፡ ( ታክሲ ግፊያ ላይ አንድ ሰው ቸኩሎ ረግጦን ታክሲ ውስጥ ሲገባና ሞባይላችንን ለመውሰድ ኪሳችን ውስጥ ሲገባ የምናደርጋቸው ነገሮች ይለያያሉ፡፡)


3. እንቅስቃሴ ማድረግ-

ንዴት አእምሯዊ ስሜት የሆነውን ያክል አካላዊ መገለጫዎችም አሉት፡፡ እጃችን ይጨበጣል፤ ሰውነታችን ይወጣጠራል፡፡ ይህንን አካላዊ ውጥረት ለማርገብ አካላዊ እንቅስቃሴ ፍቱን ነው፡፡ ቢቻል ቢቻል ሣኮ መደብደብ፤ ካልሆነ የኤሮቢክስ እንቅስቃሴ፤ ቢያንስ ግን ፈጣን የእግር ጉዞ ማድረግ ጥሩ ነው፡፡


4. የሚያናድዱን ነገሮች መመዝገብ-

የሚያናድዱንን ነገሮች ብንመዘግብና ብናሰላስላቸው የሆነ አይነት ድግግሞሽ እየታየን ይመጣል፡፡ ይህ ደግሞ ራሳችንን የበለጠ እንድንረዳ ያደርገናል፡፡ ራሳችንን ስናውቅ የምንሄድበትን መንገድ እና እንዴት እንደምንደርስ ግልፅ ስለሚሆንልን የተረጋጋና ንዴትን መቆጣጠር የሚችል ሰው እንሆናለን፡፡


መልካም ጊዜ፡፡

http://yonaslakew.blogspot.com/

34 views0 comments
bottom of page