top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ንጉሥ መሆን! – ኤፍሬም ሥዩም


ንጉሥ መሆን! – ኤፍሬም ሥዩም

ምናልባት… ከቤተ መንግስቱ በአፋ – ከዙፋኑ እግር ድንኳን ጥሎ ለሚኖር – ከሜዳ ላይ ወድቆ ለሚያድር የለት ስቃዩን – የማግኘት ርሃቡን የማጣት እርካታውን – የድህነት ቀንበሩን የጉስቅልናውን ስንክሳር – ንጉስ ይፈታል ብሎ ለሚያስብ ለአንድ ትንሽ ምስኪን የድሃ ልብ፤ ንጉስ መሆን – ቀላል ነው ያለ ጭንቅ ፣ ያለ ሃሳብ – በድሎት መኖር ነው። ንጉስ መሆን ግን ይከብዳል … ምናልባት ለመንገስ – መጋደል ይቀላል። በአንድ ወቅት ንጉሱ … ከንግስናው በፊት – የድሃ ልጅ ነበር ምስኪን ብላቴና – ተጨቁኖ የሚኖር የፍርድን መጓደል: የድሃን መበደል፡ ይህን ሁሉ ያውቃል፤ ንጉስ መሆን ደግሞ… እውቀትን ያስንቃል፤ ከሜዳ ላይ ወድቆ – መኖርን ያስመኛል።

ሌላው… ከጠረፍ ላይ ሰፍሮ፡ ሚስት ልጁን ሩቅ ጥሎ፤ የርስቱን ድንበር … ወጥቶ ለሚጠብቅ፡ ላንድ ምስኪን ወጥቶአደር (ወታደር)፤ ንጉስ መሆን ምንም ነው፡ ተራ ትንሽ ቀላል ነገር፡ ፀሃይ ተከልሎ … በጥጋብ መሳከር። ንጉስ መሆን ግን ይከብዳል፤ ምናልባት ለመንገስ – መጋደል ይቀላል። ምክንያቱም ያ ንጉስ … ከዘመናት በፊት – ድንበሩን ጠባቂ … በራሱ ጭፍራ ነው፤ ወይም ያንድ ወታደር … የአብራኩ ክፋይ ነው። ስለ ሀገር ፍቅር ስለ ድንበር ክብር ጥይት መታኮስም የሚቀለው ነበር።

ንጉስ ሲሆኑ ግን … ነገር ሁሉ ይለወጣል፤ የንጉስን ጭፍራ መሆንን ያስመኛል። ምናልባት … የሰማይን በረከት በመጠበቅ … በውሃ እጦት ለሚሳቀቅ… ላንድ ምስኪን አርሶአደር – ማዳበሪያ ላስጨነቀው፤ ማዳበሪያ ማግኘት ማለት… በንጉሱ ፈቃድ … በቀጭን ትዕዛዝ … መምጣት የሚችል ነው።

የዛች ድሃ አገር … ንጉስ ገዢያቸው ግን፡ ስለ ገበሬዎች መፈክር አንስቷል በስማቸው ምሏል ራሱንም ሰጥቶ በብዙ ተጋድሏል። ንጉስ ሲሆኑ ግን – ይህ ሁሉ ይቀራል መሃላው በተራ – ከጉሮሮ ያንቃል ጠልቶ የጣሉትን – ይቅርታ ያስብላል። ለምን? ከመንገስ … መጋደል … እጅጉን ይቀላል። ሌላው … ንጉስነትን ፈልጎ – ንጉሱን ለሚተች አውቅልሃለሁ ለሚል – ለድሃ ተሟጋች ንጉስ ይሁን እንጂ… ለሁሉም ነገሮች – መፍትሔው ቀላል ነው ንጉስ መሆን ነው የችግሮች መፍችያው። የድንበር መከበር… የገበሬው ችግር … የፍርድ መጓደል … የድሆች መበደል … ባገሪቷ ያለው የስቃይ ስንክሳር… መፈታት ይችላል – ባንዲት ምሽት ጀምበር። ንጉስ ሲሆኑ ግን – ይህ ሁሉ ይጨንቃል፤ የንግስናው ዙፋን – ላፍ ዳገት ይሆናል።

24 views0 comments

Recent Posts

See All
bottom of page