top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

"አለምን በአንድ ፊሽካ" (በመምህር ካሚል ሁሴን)


የትራፊክ መብራት ሶስት አይነት ቀለማት ያለው ሲሆን አረንጓዴው ለመንዳት ቢጫው ለጥንቃቄ ቀዩ ደግሞ ለማስቆም የተሰየሙ ናቸው። በዚህ የመንገድ የትራፊክ መብራት ትዕዛዝ ተቀባዮች በአብዛኛው እግረኞች እና ተሽከርካሪውች ናቸው። አዲሱ ቀይ የትራፊክ መብራት የሚስቆመው የመኪናዎችን እንቅስቃሴ ብቻ አይደለም። አዲሱ የትራፊክ መብራት ብዙ የሚንስትር መስሪያቤቶችን (ት/ሚ ቱሪዝም/ሚ የስፖርት ሚ ወዘተ) በአንድ ፊሽካ ብቻ የመቶ አመታት ስራቸውን ቀጥ አድርገው እንዲያቆሙና አስገድዷል። ተማሪዋች ከሚወዱት የትምህር ገበታ ተገተዋል። የአለማችን ቱሪስቶች ነጋዴዎች በአየር ከአንድ ጫፍ ወደ ሌላ መብረር አልቻሉም። መላው የአለማችን የእግር ኳስ አፍቃሪዋች ቁጭ ብድግ የሚሉላቸው እንቅልፍ የሚያጡላቸው የእንግሊዚ የስፔን የጣሊያን የጀርመን የፈረንሳይ ሊጎች በአንድ ፊሽካ ደብዛቸው ጠፍቷል። አለም በኮረና ቫይረስ ተጠፍንጋ የምትይዝው የምትጨብጠው ግራ ገብቷታል።የአለም ሳይንቲስቶች አለምን ከዚህ አደጋ ለመታደግ እንኳን መሰብሰብ ከማይችሉበት ሁኔታ ላይ ደርሰዋል። በጣም የሚገርመው እና የሚያስፈራው ሰዋች ተሰብስበው የሚያለቅሱበትና ጌታቸውን ምህረት የሚጠይቁት የፀሎት ቦታም እንዳይሄዱ የተከለከሉበት አደገኛ ቀይ መብራት መሆኑ ነው። ወዴት ይኬድ! በዚህ ፊሽካ አለማችን እስከአሁን ብቻ ወደ 8ሺ ሞቶችን አስተናግዳለች። በርካታ የአለማችን ሐገራት ይህን በሽታ ለመከላከል ይረዳ ዘንድ አዲስ በጀት በመመደብ ከባዱን ጦርነት ተያይዘውታል። መጀመሪያ ቀላል ነው ብላ በሽታውን ያጣጣለችው አሜሪካ ወደ 1ትሪሊየን ዶላር ለዚህ መቅሰፍት መድባለች እየተባለ ነው።

ውድ አንባብያን ልብ ብለን ከሆነ ከዚህ አስደንጋጭ ክስተት በፊት አለማችን የነበረችበት ቀውስ በምድራችን ላይ አንድ አደገኛ ነገር ሊከሰት እንደሚችል የሚያመላክቱ ውዝግቦች ይስተዋሉባት ነበር። ሶስተኟው የአለም ጦርነት ፣ የቻይና ሙስሊሞች ዘግናኝ እልቂት ፣ ለረጅም አመት የቆየው የሶሪያ መፈራረስ ፣ የሊብያ ያልተጠበቀ ውድመት ፣ የየመን መፈራረስ ፣ የፍልስጤማውያን መቆሚያ እና ማለቂያ የሌለው ሞትና ሰቆቃ ወዘተ በአጠቃላይ በምድራችን ላይ እየተንሰራፋና እየጨመረ የመጣው የሰው ልጆች የመብት ጥሰት ኢሰባዊነት ፣ የአሜሪካን እኔ ሀያል ነኝ ማለት የቻይና NO…! ማለት የሩስያ የቱርክ የኢራን የሰሜን ኮርያ እኛም ከማንም አናንስም ብሎ መፎከር መሸለል ከዚህም… ከዚያም ሲቀጣጠል የነበረው እሳት በኮረና መደብዘዙ አስገራሚ ክስተት ነው ። አሁን አለማችን በአንድ ጭቅላት ስለ አንድ ነገር በቻ ነው የምታስበው(ኮቪድ 19)። በሽታው ሀብታም ሀገር ፣ ድሀ ፣ ሀያላን፣ ደካማ፣ ኒውክለር ያለው፣ የሌው፣ ዝነኛ ታዋቂ፣ የማይታወቅ፣ ስልጣን ያለው ፣ የሌለው ብሎ አልመጣም። እንዲያውም ዱላውን የጀመረው ከሀብታም ነን ስልጣን አለን ብለው ከሚፎክሩት ነው። ያ… በአለም የሰው ልጅ ታሪክ ምንጊዜም የማይረሳው ፊራኦን ሁለት እጅግ በጣም የሚገርሙ ፀባዮች ነበሩት። እነሱም አንደኛ ለጋስነቱ እና ሁለተኛ ደግሞ ፍትሀዊነቱ ነበር። ዳሩ ምን ዋጋ አለው ሀብቱና ስልጣኑ አሳስተውት እኔ ጌታ ነኝ! እኔን ነው የምትገዙት በማለት ከፈጣሪ ጋር ግብ ግብ ተያያዘ። በመጨረሻም ዋጋውን አገኘ። የሰው ልጅ አሁን አለም በቁጥጥሬ ስር ናት ይህን ሰርቻለሁ ይሄ አለኝ እያለ እየፎከረ ከፈለኩ ምድርን አጠፋለሁ በማለት ማቅራራት ከጀመረ ቆየት ብሏል። በኛ... በድሀዋ ሀገር እንኳን ባሳለፍነው ሁለት አመት ብቻ በሁሉም የሀገራችን ክልሎች በሚያስብል መልኩ እኔ ሃያል ነኝ! ይሄ መሬት የኔ ነው! አንተ እስላም ! አንተ ክርስቲያን ! አንተ መጤ ! ወዘተ እየተባባለ አይተን እና ሰምተን የማናውቀውን ብዙ ኮረና አስተናገደናል። ውድ ወገኖች ከዘረኝነት በላይ ምን አስፈሪ ነገር አለ? ዛሬ ላይ ከጌታ በተላከ አንድ አጣብኝቅ ውስጥ ገብተናል። እንደ ልጅነታችን እጃችሁን በውሀ አይበቃም! በሳሙና እሱም አይበቃም! በሳኒታይዘር በአልኮል ታጠቡ እየተባለ ነው።

እኛ… ኢትዮያውያን በክፋት፣ በተንኮል እና በትቢት ተወጣጥረን እያለ የኮሮና ቫይረስ ከች…አለና “በዘር እና በሀይማኖት እየተከፋፈላችሁ እርስ በርስ ለመጨራረስ የተዘጋጃችሁት እስቲ መጀመሪያ የግል ንፅህናችሁን ጠብቁ በገዛ መዳፋችሁ የያዛችሁትን ቫይረስ አስወግዱ” በማለት ተሳለቀብን። አሁን የብልፅግና የኢዜማ የኦፌኮ የሽኮኮ ምናምን ወሬ ወደ ጐን ብለን እጃችን እስኪላጥ መታጠብ ብቻ ነው የሚያዋጣን። ከቫይረሱም ከሃጢአቱም መጽዳት አለብን። ከዚህ ታሪካዊ ክስተት ተምረን ትንሽነታችንን አውቀን የዘረኝነት ኮረና አውልቀን ወደ ትክለኛ አእምሯችን ወደ ሰውነታችን ሰው ወደ መሆናችን እንመለሳለን ወይስ ክትባት ሲገኝ አንደገና እጃችንን አቆሽሸን ወደ ዘረኝነት ጉድጓድ እንገባለን?

ውድ ወገኖቼ ፈጣሪ በሰው ልጆች ላይ አንድን መጥፎ ነገር አያመጣም ወይ እንዲከሰት አያደርግም እንዲማሩ እና ከስህተታቸው እንዲታረሙ ቢፈልግ እንጂ...! አሁንም ቢሆን ንሰሀ መግባት ጌታን መማፀን ማልቀስ ይጠበቅብናል። ይህን ካደረግን አለምን በአንድ ፊሻካ ቀጥ ያደረጋት ኮሮና ቫይረስ ራሱ ቀጥ ይላል። ኢንሻ አላህ…!

ሰላማችሁ ይብዛልኝ


መምህር ካሚል ሁሴን

ሪያድ ሳኡዲ አረቢያ


78 views0 comments
bottom of page