top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

አስሩ ድንቅ የስኬት መርህዎች – ከናፖሊዮን ሂል


አስሩ ድንቅ የስኬት መርህዎች – ከናፖሊዮን ሂል

ስኬት አንድ የሆነና ሁሉንም የሚያስማማ ወጥ ትርጉም ሊኖረው አይችልም። እስከዛሬ ከቀረቡ የስኬት ትርጉሞች መካከል ለብዙ ሰዎች የሚስማማው የታዋቂው የኽርል ናይቲንጌል ትርጉም እንደሆነ ብዙ የዘርፉ ሰዎች ይመሰክራሉ። ናይቲንጌል ስኬትን እንዲህ አድርጎ ነው ይተረጉመዋል። “Success is the progressive realization of a worthy goal or ideal.”። ትርጉሙ ስኬት ማለት አንድ ጠቃሚ ብለን የምናስበውን ሃሳብ እውን ማድረግ ነው እንደማለት ሲሆን፤ እርግጠኛ ነኝ ይህ ትርጉም ብዙዎቻችንን ያስማማል፤ ምክንያቱም ስኬት በግል ሚዛን የሚለካ፤ በግል መነጸር የሚታይ፤ በግል አይምሮ የሚተረጎም ግላዊ ስለሆነ።

የአንዱ ሰው ስኬት ለሌላው ትርጉም ላይሰጥ ይችላል። አላማ ብለን የምንጠነስሳቸው ውጥኖች በሌሎች ዘንድ ዋጋ አይኖራቸው ይሆናል። ለምሳሌ የአንድ ሯጭ የስኬት ትርጉም የአለም ኦሎምፒክን ሬከርድ መስበር ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል የአንድ ዘፋኝ የስኬት መመዛኛ የዘፈኑ ተደማጭነት ነው። የአንድ አስተማሪ ስኬት፤ የተማሪዎቹን በጎ ውጤት መመልከት ይሆናል። ለዚህ ነው ናይቲንጌል ስኬትን ሰፋ ባለ መልኩ ሊትረጉመው የተገደደው። እሱ እንዳለው ስኬት ማለት ለኛ ዋጋ የሚሰጠንን ሃሳብ ወይም ግብ እውን ማድረግ ነው። በራሳችን መንገድ ሁላችንም ስኬታማ ሰዎች መሆን እንደምንፈልግ እርግጥ ነው። በዚህ መሰረታዊ ሃሳብ ከተስማማን፤ ሃሳባችንን እውን እንድናደርግ፤ ግባችንን እንድናሳካ ከኛ ምን ይጠበቃል?

አለማችን ላይ ስለስኬት ከተጻፉ መጻሕፍት ውስጥ ቁጥር አንድ እንደሆነ የሚነገርለት የ “Think and Grow rich” ደራሲ ናፖሊዮን ሂል፤ ምንም እንኳን የምንፈልጋቸው ነገሮች ቢለያዩም ሁላችንንም ለስኬት የሚያበቁ ድንቅ መመሪያዮችን በመጽሃፉ አስፍሯል። እናም እኛንም በመረጥነው የህይወት ጉዞ ላይ ከረዳን ብዬ አስሮቹን የስኬት መርህዎች ኸርል ናይቲንጌል ካሰናዳው ላይ እንዲህ አቀናብሬ አቅርቤያቸዋለው።

1ኛ)- ፍላጎት (Desire) – የመጀመሪያው ደረጃ ፍላጎት ነው። ከልብ የመነጨ ፍላጎት፤ ፍላጎታችንን እንደ ዘር ልናየው እንችላለን። ፍሬ እንደሚያፈራ አምነን የምንዘራው ዘር። ዛሬ ዘርተነው ዛሬውኑ ፍሬ የሚሰጠን ተክል የለም። ፍላጎታችንም ልክ እንደ በቆሎ ወይም ማንኛውም ዘር ዛሬ ተዘርቶ በቂ ውሃ፤ በቂ ጸሃይ፤ በቂ እንክብካቤ ፤ካገኘ በኋላ በግዜው የሚያሽት ነው። የምንፈልገውን ነገር ጥርት ባለ መልኩ ማወቁ ይጠቅመናል። ለመረጥነው ነገር ምን ያህል ፍላጎት እንዳለን ለማወቅ የምናደርጋቸውን ነገሮች መቃኘት ያስፈልገናል። ከምንም በላይ በውስጣችን ያለው የትዕግስት መጠን ፍላጎታችን ምን ያህል እንደሆነ ያስረዳናል። ለምሳሌ ሰዓሊነት ፍላጎቱ የሆነ ሰው ባይከፈለው እንኳን ስዕል መሳሉን አያቆምም። አላማ ብለን ለመረጥነው ነገር በቀላሉ ሊገደብ የማይችል ፍላጎት ሊኖረን ይገባል። ጥልቅ ፍላጎት ማለት ወደኋላ እንዳናፈገፍግ የመመለሻውን ድልድይ እንደማቃጠል ያህል ነው።

2ኛ)-እምነት (Faith)- እምነት አላማችን የሚገነባበት መሰረት ነው። የምንፈልገው ነገር ምንም ይሁን ምን እምነት ከሌለን ነዳጅ የሌለው መኪናን ለመንዳት እንደመሞከር ይሆንብናል። ደግነቱ እምነት በመጀመሪያ ባይኖረንም፤ በሂደት ልንገነባው የምንችለው ጥበብ ነው። ለአይምሮዋችን ቀና የሆኑ ነገሮችን በመመገብ እምነትን በሂደት ማዳበር ይቻላል። የምንፈልገውን ነገር ለማግኘት እምነት እጅግ ወሳኝ ነገር መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ማርቲን ሉተር ኪንግ ስለ እምነት ደስ የሚል አባባል አለው ” እምነት ማለት ሙሉውን ደረጃ እስከየት እንደሚደርሰን ባናውቅም እንኳን የመጀመሪያውን ደረጃ መውጣት ነው” ይላል።

3ኛ)- እራስን ማሳመን -Auto Suggestion (አውቶ ሰጀሽን)- አይምሮዋችን እውነት ብሎ የሚቀበለው ነገር ደግመን ደጋግመን የምንመግበውን ነው። እዚህ ላይ ይህንን በደንብ የሚያስረዳ አንድ ታሪክ ትዝ አለኝ። ታሪኩ እንዲህ ነው ሁለት ውሾች የነበሩት አንድ ሰው ነበር። አዘውትሮ እኒህን ውሾች አደባባይ እየወሰደ እንዲደባደቡ ያደርግ ነበር። ታዲያ ተመልካቾቹ የትኛው ውሻ በእለቱ እንደሚያሸንፍ ሲጠይቁት “በደንብ የምመግበው ውሻ ነው” ሲል መለሰላቸው። ሁላችንም ውስጥ ሁለት ዉሾች አሉ የመልካም እና የክፋት፤ የልማት እና የጥፋት፤ የእውቀት እና የድንቁርና፤ የውድቀት እና የድል ውሾች። የበላይ ሆኖ የሚመራን ውሻ ዘወትር የምንመግበው ነው። ለዚህ ነው ናፖሊዮን ሂል “አውቶ ሰጀሽን” ወይም ለራስ መልካም ነገሮችን ደጋግሞ በመንገር አይምሮዋችንን ወደፈለግነው መንገድ መምራት እንደምንችል የሚነግረን። መንገር ብቻም ሳይሆን የሚያሳስበን!

4ኛ)- በአንድ ነገር ላይ እራስን የተካኑ ማድረግ (ስፔሻላይዝድ ኖውሌጅ)- “Mastermind group- associate with men who know what you want to specialize in”. ልንሰማራበት በመረጥነው ወይም ፍላጎት ባለን ሙያ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን መተዋወቁ እና ቅርርብ መፍጠሩ ወሳኝ ነገር ነው። ጊዜያችንን የምናሳልፈው ከነማን ጋር ነው? የምናውቃቸው ሰዎች ወይም ጓደኞቻችን ለምንፈልገው ሙያ የሚያግዙን ናቸው? ለምሳሌ ፕሮፌሰር ለመሆን ፍላጎት ያለው ሰው በተቻለው መጠን ዩንቨርሲቲ አካባቢ ካሉ ሰዎች ጋር ግንኙነቱን ቢያዳብር ይጠቅመዋል። ተዋናይ መሆን የሚመኝ ሰው እራሱን ከቲያትር መድረክ አካባቢ ማራቅ የለበትም። ሁላችንም የምንማረው ቀድመውን ካወቁት ነውና፤ የምንፈልገውን ነገር በቅጡ የሚያውቁ ሰዎችን ማወቁ ይጠቅመናል።

5ኛ)-ነገሮችን በህሊናችን መሳል- “Imagination- It’s the workshop, the impulse. men can create what he can imagine. what the mind conceives it achieves”. ሁሉም ነገር ሃሳብ ነበር። ምንም ነገር እውን ሆኖ ከማየታችን በፊት በአንድ ሰው አይምሮ ውስጥ የተጠነሰሰ ሃሳብ ነበር። የምንፈልገውን ነገር እውን ሆኖ ከማየታችን በፊት በህሊናችን መሳል ትልቁ የስኬት ሚስጥር እንደሆነ ብዙዎች የተስማሙበት ነው። አላማችን ቁልጭ ብሉ በህሊናችን ከታይን ለጉዞዋችን ትልቅ ጉልበት አገኘን ማለት ነው። ምክንያቱም የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ እንደሚሳካ አይምሮዋችን እየነገረን ነው።

6ኛ)- እቅድ ማውጣት- Organized planning- እቅድ ማውጣት ጊዜን በአግባቡ እንድንጠቀም ከማድረጉም በላይ፤ በአንድ ጊዜ አንድ ደረጃ እየወጣን ጉዞዋችን አድካሚ እንዳይሆን ያደርግልናል። እቅድ ስናውጣ ነገሮች ሳይደራረቡብን ቀስ በቀስ ወደ ግባችን እንደርሳለን። እቅድ ስናወጣ ግን እራሳችንን በሚያጨናንቅ እና ካልፈጸምነው የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማን በሚያደርግ ሁኔታ ሳይሆን፤ ከጊዜያችን ፤ ከባህሪያችን እንዲሁም ከማንነታችን ጋር የሚስማማ እቅድ ነው ማውጣት አለብን። ምክንያቱም ሌላው ያቀደበት መንገድ ለኛ ላይስማማ እና ከግባችን ላያደርሰን ስለሚችል።

7ኛ)- ውሳኔ-Decision- “lack of decision is the top reason for failing. if you make a decision its worth sticking to it. don’t let others opinion to sway you” .የሰው ልጅ ውድቀት አንደኛው መንስዔ የውሳኔ ማጣት ነው። አንድ ሰው ምንም ያህል እምቅ እውቀት ቢኖረው፤ ምንም ይህል የሚያስደንቅ ሃሳቦችን ማመንጨት ቢችልም ውሳኔ መወሰን ካልቻለ ግን አቅሙ ሁሉ ከውስጡ አይወጣም። ውሳኔ በማጣት የተነሳ ብዙ ሙዚቃዎች ሳይሰሙ፤ ብዙ መጽሐፎች ሳይጻፉ፤ ብዙ ግኝቶች ሳይገኙ፤ ወደ መቃብር ይወርዳሉ።.በሁላችንም ውስጥ ለኛ ብቻ የተሰጠ ስጦታ አለ፤ ይህን ስጦታ ግን አውጠን ሌሎች እንዲያዩት ማድረግ የምንችለው ውሳኔ መወሰን ስንችል ብቻ ነው። የምንወስነው ምንድን ነው ካላችሁ፤ መልሱ የምንወስነው መሆን የምንፈልገውን ነው።

8ኛ)- ጽናት -(Persistence)- “the power of will. This quality distinguishes the success from the failure. it’s a state of mind and can be cultivated”. ውሳኔ ብቻውን አቅም የለውም። ውሳኔያችን ባህሩን አቋርጦ ከአላማችን ዳርቻ እንዲደርስ የሚያደርገው ሃይል ጽናት ነው። ብዙዎⶭችን የተለያዩ ውሳኔዎችን እዚህና እዚህ እንወስናለን ነገር ግን ጽናት ኖሮን አንገፋበትም። ለዚህ ነው ናፖሊዮን ሂል የወድቀት እና የስኬት ዋናው መለያ ጽናት ነው ያለው። ለምሳሌ ከመጠጥ ሱስ መላቀቅ የሚፈልግ ሰው መቶ ጊዜ ለማቆም ቢወስንም ከውሳኔው ጋር ጽናት ካልተደመረበት በቀር ውሳኔው ብቻውን ምንም ዋጋ የለውም። ስለዚህ በውስጣችን ያለውን የጽናት መጠን መፈተሹ እጅግ ወሳኝ ነገር ነው።

9ኛ) -ጥምር ሃይል -(Power of the master mind)-” No two minds ever come together without thereby creating a third, invisible intangible force, which may be likened to a third mind [the master mind]”. “ሁለት ጭንቅላቶች አንድ ላይ ሲሆኑ ሶስተኛ ጭንቅላት ይወለዳል”። አንድ ሰው የራሱ የሆነ ሃሳብ ወይም ግኝት ሊኖረው ይችላል፤ ከሌሎች ሰዎች ሃሳብ ሲደመር ይበልጥ ይሰምራል። “ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሐኒቱ” እንዲል የሃገራችን ሰው። በጋራ የመስራትን ልምድ ማዳበር መቻል አለብን። አብሮ መስራት መቻል ትልቅ ክህሎትም ጭምር ነው።

10ኛ) የምታደርገው ነገር ደስታን ሊስጠህ ይገባል– (Enthusiasm)- ስቲቭ ጆብስ በህይወት በነበረበት ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር “የምንሰራውን ነገር የማንወደው ከሆነ እስከመጨረሻው ለመሄድ አንችልም፤ የሚሰራውን የማይወድ ማንኛውም ሰው ተስፋ ቢቆርጥ አይፈረድበትም”። እውነት ነው የምንወደውን ነገር ስናደርግ በቀላሉ ተስፋ አንቆርጥም። ሙያችን እንዲሆን የምንመርጠው ነገር የምንወደው ነገር ከሆነ በዛ ነገር ላይ እውቀታችንን ለማዳበርም ሆነ ልምድ ለማግኘት ፍላጎት ይኖረናል። አስቡት ሰውን መርዳት የማይወድ ወይም ለሰ ሰው ምንም ግድ የለለው ሰው የህክምና ባለሙያ ቢሆን፤ በሽተኞቹን እንደ ገንዘብ ማግኛ ከመቁጠር በቀር ለጤንነታቸውም ሆነ ለደስታቸው ዴንታ አይሰጠውም። ስለዚህ የምንሰራው ነገር ምን ያህል ደስታ ወይም እርካት ይሰጠናል የሚለው ጥያቄ በተሰማራንበት መስክ ሁሉ እራሳችንን ልንጠይቀው የሚገባን ጥያቄ ነው።


ምንጭ - asharaye.net


70 views0 comments
bottom of page