top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

አፈንጋጭነትና እብደት! (በፍቃዱ ቀነኒሳ)


መቼም ፍልስፍና እንደሚባለው ቃል በበጎም ሆነ በክፉ በተደጋጋሚ የሚነሳ የጥበብ ዘርፍ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ፍልስፍናን አንዳንዶች ከእብደት ጋር፣ ሌሎች ደግሞ ከአፈንጋጭነት ጋር ያያይዙታል፡፡ በርግጥ ፍልስፍናዊ አፈንጋጭነት ከማህበረሰብ ፍልስፍና ተለይቶ በግለሰባዊ ፍልስፍና የመመራት ውጤትና መገለጫ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡

በተመሳሳይ “በብዙ እብዶች መካከል የሚገኝ አንድ ጤነኛ እንደ እብድ ይቆጠራል!” እንዲሉ፤ ብዙዎች የአንድን ጉዳይ ትክክለኝነት በአመክንዮ ሳያረጋግጡ በስሜት፣ በሃማኖታዊ አስተሳሰብና በማህበረሰብ ፍልስፍና ብቻ ተነድተው እውነት ነው ብለው የተቀበሉትን ጉዳይ በግለሰባዊ አመክኗዊ ፍልስፍና የሚመራው ፈላስፋ፣ ሀሰት መሆኑን ገልጾ በመቃወም ራሱ የሚያምንበትን ፍልስፍና ማራመዱን የሙጥኝ ካለ፣ እንደ እብድ መቆጠሩ የማይቀር ነው፡፡ በርግጥም በፍልስፍና ታሪክ የምናውቃቸው ታላላቅ የዓለማችን ፈላስፎች፣ በራሳቸው መስተሃልይ በመመራት በኖሩበት ዘመን በነበረው ማኅበረሰብ ያልታሰበውን ቀድመው በማሰባቸውና በጭፍን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ቱባ ማህበረሰባዊ እሴት መሰረት በማናጋታቸው አፈንጋጭና እብድ ተብለዋል፤ ከማህበረሰቡ ተገልለዋል፣ ከቀዬያቸው ተሰደዋል፣ በድንጋይ ተወግረዋል፤ በመርዝም እንዲሞቱ ተፈርዶባቸዋል፡፡ ምንም እንኳ ፍልስፍና፣ አፈንጋጭነትና እብደት ከፍልስፍና ጋር የሚገናኙበት መንገድ ቢኖርም ፍልስፍናን፣ አፈንጋጭነትንና እብደትን አንድና ተመሳሳይ አድርጎ መውሰድ ጉልህ ስህተትን መፈጸም ይሆናል፡፡

ብዙዎች ይህን ስህተት የሚፈጽሙት ደግሞ ስለፍልስፍና ምንነት ያላቸው ግንዛቤ በመዛባቱ ምክንያት ነው፡፡ ለዚህ ነው በዛሬው ጽሁፌ ስለፍልስፍና ትክክለኛውን ግንዛቤ ለማስጨበጥ የወሰንኩት፡፡ ፍልስፍና ያለምንም ውጪያዊ ግፊት በግለሰቡ ውስጣዊ ተነሳሽነት (Curiosity) ብቻ ገንፍሎ የሚወጣ ተፈጥሮአዊ የእውቀት ጥማት ወይም ጉጉት ነው፡፡ ይህም ስለ ራስ ማንነትና ምንነት፣ ስለ ዓለም አፈጣጠር፣ ስለ ውበት፣ ስለእውቀት፣ በአጠቃላይ የሰው መስተሃልይ (mind) ስለሚያመላልሳቸው የሚታዩና የማይታዩ ነገሮች ህልውና፣ አመጣጥ፣ ምንነት፣ አሰራርና ፍጻሜ የመጨረሻው እውነት ላይ ለመድረስ የሚደረግ ውስጣዊ ትግል ነው፡፡ ይህ ውስጣዊ ትግል የቀለም፣ የዘር ወይም የቋንቋ ልዩነት ሳይገድበው አእምሮ በተሰጣቸው የሰው ልጆች ሁሉ ውስጥ በተለያየ ደረጃ የሚገኝ ነው፡፡ ይህንንም ዑደት ከህጻናት ባህርይ መረዳት ይቻላል፡፡

የማህበረሰቡን ወግና ባህል ጠንቅቀው የማያውቁ ህጻናት አእምሮአቸው ውስጥ የሚመላለሰውን ጥያቄ መልስ ለማወቅ ካላቸው የተነሳ ብቻ ያለምንም ፍርሃትና ይሉኝታ አውጥተው እንደሚጠይቁ ሁሉ ፍልስፍናን የህይወታቸው መንገድ ያደረጉ ግለሰቦችም ማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ፣ የባህል ወይም የሃይማኖት አስተሳሰብ ሳይገድባቸው ነጻ ሆነው አእምሮአቸው ላቀረበላቸው ጥያቄ የመጨረሻውን እውነተኛ መልስ ለማግኘት የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ሁሉ ይከፍላሉ፡፡ በሌላ በኩል የሚነሳባቸውን መሰረታዊ ጥያቄ ዋጋ ቢስ አድርጎ በማሰብ ወይም ለጥያቄው አንድ የመጨረሻ እውነተኛ መልስ አይኖረውም ብሎ በማመን፣ ወይም ለጥያቄው በተለምዶ የሚሰጠውን ምላሽ እንደ እውነተኛ መልስ በመቁጠር የተነሳውን ውስጣዊ ጥያቄ ችላ የሚሉ ሰዎች በተፈጥሮ ያገኙትን የፍልስፍና ዝንባሌ ስለሚያደበዝዙት ወደ ፍልስፍና መንገድ ለመግባት ወይም የመጨረሻው እውነት ላይ ለመድረስ የሚኖራቸው ጉጉት በእጅጉ አነስተኛ ይሆናል፤ ሲከፋም እንደሰው እስካለማሰብ ሊያደርሳቸው ይችላል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ በተፈጥሮ የተገኘን የፍልስፍና ዝንባሌን በፍልስፍና ትምህርት ወይም በልምምድ በማዳበር ላቅ ወዳለ የፍልስፍና ደረጃ ማሸጋገር ይቻላል፡፡

ፍልስፍና ከሚመልሳቸው መልሶች ይልቅ የሚጠይቃቸው ጥያቄዎች ይበልጥኑ ዋጋ ይኖራቸዋል፡፡ በፍልስፍና ማንኛውንም ዓይነት ጥያቄ በየትኛውም የጥልቀት ደረጃ መጠየቅ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ሁሉንም ጥያቄዎች ያነሳው ፈላስፋ፣ ጥያቄዎቹን ሙሉ በሙሉ በአጥጋቢ ሁኔታ እንዲመልስ አይገደድም፤ ይልቁን እያንዳንዱ ፈላስፋ ካመላለሳቸው ጥያቄዎች መካከል አንዳንዶቹን ሙሉ በሙሉ፣ ሌሎቹን ደግሞ በከፊል በራሱ አተያይ ሊመልስ ወይም ደግሞ አንዱ ፈላስፋ ያነሳቸውን ጥያቄዎች ሌሎች ፈላስፎች ሊመልሷቸው ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ በፍልስፍና ለሚነሱ ጥያቄዎች በአንድ ፈላስፋ የተሰጡ መልሶችን የመጨረሻና ብቸኛ እውነት ብለን በእርግጠኝነት ልንቀበል አይገባም፤ የተሰጠውን መልስ እውነትነት ለማረጋገጥ ተጨማሪ ጥያቄዎችን ልናከታትል እንጂ! በዚህ ምክንያት ነው እንግዲህ ፍልስፍና በማያቋርጥ የጥያቄዎች ሰንሰለት የተመሰለውና መሰረታዊ የፍልስፍና ጥያቄዎች በየዘመናቱ እንደ አዲስ እንዲነሱ ምክንያት የሆነው፡፡ ፍልስፍና ለመሰረታዊ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጠው በትክክለኛ የአስተሳሰብ ቀመር (Logic) ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ የትክክለኛ አስተሳሰብ መርህ ደግሞ አመክንዮ (reason) ነው፡፡ በምክንያታዊነት የሚመራ ሰው የአስተሳሰብ ህጸጽን (Fallacy) ለመቀነስ ብሎም ለማስወገድና ውሳኔዎቹን ሁሉ በሰላ አስተሳሰብ (critically) መዝኖ ለማስተላለፍ አቅም ይኖረዋል፡፡

ይህ አቅም ነው ፈላስፎችን ከእውነተኛ አስተሳሰብ ያፈነገጠ ሃሳብን ወይም ድርጊትን በጭራሽ እንዳይታገሱና በቀጥታም እንዲተቹ የሚያስገድዳቸው፡፡ ፍልስፍና አንድን እውነት በራሱ ፈትሾ ካልደረሰበት በቀር ፈጽሞ አይቀበልም፡፡ ፍልስፍና ሰዎች ለአንድ ውሳኔ ምክንያት ነው ብለው ያቀረቡትን ሁሉ እንደ ተገቢ ምክንያት ላይወስደው ይችላል፤ ምክንያቱም ግለሰቦቹ የእውነተኛ አስተሳሰብ ቀመርን የማይከተሉ ከሆነ ድምዳሜያቸው ከስሜታዊነትና ከጋርዮሽ ፍልስፍና ወይም ከይሉኝታ፣ ከባህላዊና ሃይማኖታዊ እስተሳሰቦች ተጽዕኖ ነጻ ላይሆን ስለሚችል ነው፡፡ ፍልስፍና የአንድ ርዕዮተ ዓለም አገልጋይ ሳይሆን ሁሉም ሃሳቦች የሚገለጹበት የጋራ መሳሪያ ነው፡፡ ፍልስፍና የራሱ የሆነ አንድ አቋም (position) የለውም:: በዚህም ምክንያት ፍልስፍና የራሱን ሳይሆን የተጠቃሚውን ግለሰብ የእምነት ፈለግ ተከትሎ በምክንያታዊነት ብርሃን እየተመራ የሚጓዝ ብርቱ የሃሳብ ባቡር ነው፡፡ ለምሳሌ ስለዓለማትና በውስጣቸው ስለያዟቸው ነገሮች ምንነትና የትመጣነት ዙሪያ የሚነሱ ዲበአካላዊ (metaphysical) ጥያቄዎች መልስ የሚሰጡ የተለያየ ዓይነት እምነት ያላቸው ፈላስፎች፣ ሁሉም ፍልስፍናን የሃሳባቸው ማስኬጃ መሳሪያ አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡

ለምሳሌ እንደ ቶማስ አኳይናስና፣ ቅዱስ ኦገስቲንና አንሰልምና ፓሊ የመሳሰሉ የመካከለኛው ዘመን ፈላስፎች በፈጣሪ ህልውና የሚያምኑ (Theist) ፈላስፎች ሲሆኑ ለዚህች ዓለም ፈጣሪ፣ አስገኚ፣ መጋቢ አላት የሚለውን እምነታቸውን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ፍልስፍናን ተገልግለውበታል፤ የነርሱ ተከታዮችም እንዲሁ፡፡ በተቃራኒው በፈጣሪ መኖር የማያምኑ (Atheist) አቋም ያላቸው ፈላስፎችም ሆኑ የፈጣሪ መኖርም ሆነ አለመኖር ሊታወቅ ወይም ሊረጋገጥ አይችልም የሚል እምነት ያላቸው ግኖስቲክ (Agnostic) ፈላስፎች የዚሁ እምነታቸውን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ፍልስፍናን በተመሳሳይ ሁኔታ ይገለገሉበታል፡፡ ፍልስፍና ለሚያጠነጥንበት ርዕሰ ጉዳይ ወሰን ወይም ድንበር (boundry) የለውም፡፡ ፍልስፍና በሁሉም የጥበብና የዕውቀት ዘርፎች ውስጥ ታላቅ ስፍራ አለው፡፡ ከልዩ ልዩ የዕውቀት ዘርፎች ቀዳሚ እንደመሆኑ መጠን ፍልስፍና ለሌሎች ዘርፎች መነሻ ወይም አባት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ፍልስፍና መነሻ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የእውቀትና የጥበብ ዘርፎች እንዲዳብሩ፣ እንዲያብቡና እንዲያፈሩ የሚኮተኩት፤ ለሁሉም በሚሰጠው የሰላ ትችት፣ ዘርፎቹ ድክመቶቻቸውን እንዲመለከቱና ለተሻለ እውነት እንዲተጉ የሚቀሰቅስ ንቁ አሰልጣኝ ነው፡፡

በተጨማሪም ፍልስፍና ባሉት መሰረታዊና ተግባራዊ ቅርንጫፎች ማለትም በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በሳይንስ፣ በኪነጥበብ፣ በትምህርት፣ በቋንቋ፣ በምጣኔ ሃብት፣ በባህል፣ በስነምግባር፣ በስነውበት፣ በለውጥ (በልማት) እንዲሁም በሞትና ህይወት ወዘተ ላይ ለየት ያሉና እጅግ ጠቃሚ ጥታቄዎችን የሚያነሳና አዲስ ዓይነት ምልከታ እንዲኖራቸው የሚቆሰቁስ ነው፡፡ ምንም እንኳ ፍልስፍና ግላዊ አስተሳሰብ ነው የሚለው ሃሳብ በፍልስፍና ባለቤትነት ላይ የበላይነት ቢኖረውም ፍልስፍና ሁልጊዜ ግላዊ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ ግን ስህተት ይሆናል፡፡ የአንድ ሰው የግል ፍልስፍና በጊዜ ሂደት ተቋማዊ ወይም ማህበረሰባዊ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ ዲሞክራሲ፣ ካፒታሊዝምና ሶሻሊዝም ያሉ በርካታ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሃብታዊ ፍልስፍናዎች መነሻ ምንጮቻቸው ግላዊ ፍልስፍና (individualistic Philosophy) ሲሆን ባለንበት ወቅት ግን ሀገራዊ ወይም ማህበረሰባዊ ፍልስፍናዎች ሆነዋል፡፡ በሌላ በኩል ወርቃማው ህግን የሚመስሉ የስነ-ምግባር ፍልስፍናዎች መነሻቸው ሃይማኖት ወይም ባህል (Communal Philosophy) ሊሆን ይችላል፡፡ በርግጥ አንዳንድ ሰዎች ፍልስፍና አስተሳሰብ ነው በሚል የፍልስፍናን ትርጉም አስፍተው በመመልከት የማንኛውም ግለሰብ፣ ተቋም ወይም ማህበረሰብ አስተሳሰብ፣ እምነት (belief)፣ እሴት (value) ሁሉ ፍልስፍና ነው ይላሉ፡፡

ይሁንና በበርካታ ግለሰቦች፣ ተቋምና በማህበረሰብ ውስጥ ያለው ፍልስፍና በቡድን እምነት (dogma) ተጽዕኖ ውስጥ የወደቀ በመሆኑ በሰላ አስተሳሰብና በምክንያታዊነት ሚዛን ያልተቃኘ እንዲሁም ለትችት ዝግ የሆነ ነው፡፡ ለትችት ወይም ለለውጥ ክፍት ያልሆነ አስተሳሰብ ደግሞ የፍልስፍና ዋነኛ መገለጫዎች ስለማይታዩበት መደቡ ከፍልስፍና ወገን አይደለም ማለት ነው፡፡ ፍልስፍና ትምህርት ቤት ገብተው በዘርፉ በሰለጠኑ የተማሩ ባለሙያዎች (professional philosophers) ወይም በተፈጥሮ ብርቱ የፍልስፍና ዝንባሌ ባላቸው ግለሰቦች ሊካሄድ ይችላል፡፡ በመጨረሻም አንድን የጥበብ ስራ ፍልስፍና ነው ለማለት ከሚያበቁን መስፈርቶች አንዱ፣ ፍልስፍናው በፅሁፍ መቅረቡ ነው የሚል የሙግት ነጥብ ይዘው የሚቀርቡ ሰዎች አይጠፉም፡፡

ይሁንና ፍልስፍና በጽሁፍ ወይም በቃል ሊቀርብ እንደሚችል መገንዘብ ይገባል፡፡ እንደ ኢትዮጽያ ባሉ ባህላቸው ሃይማኖታዊ እሴቱ የሚያመዝንባቸው ወይም የስነ-ጽሁፍ ባህላቸው ያልዳበረ ሃገሮች፣የግለሰቦችን ፍልስፍና በጽሁፍ የማስቀረት ባህላቸው በእጅጉ ደካማ በመሆኑ፣ በርካታ ፍልስፍናቸው በቃላዊ - በቅኔ፣ በተረት፣ በዘይቤ፣ በምሳሌያዊ አነጋገሮች፣ በወጎች እና በመሳሰሉት የሥነ-ቃል ዘርፎች አማካኝነት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ ኖሯል፤ ይተላለፋልም፡፡ በዚህም የተነሳ ነው በእንደዚህ ዓይነት ማህበረሰብ ውስጥ በርካታ ፍልስፍናዎች የጋርዮሽ (communal) መስለው የሚታዩት ወይም መጀመሪያ ፍልስፍናውን ያመነጨው ግለሰብ ማንነት የማይታወቀው፡፡ ግለሰባዊ የስነ-ጽሁፍ ባህላቸው በእጅጉ ከዳበረ ማህበረሰብ ውስጥ የወጡ ፈላስፎች፣ ሃሳባቸውን በቀጥታ በጽሁፍ ሊያሰፍሩ ካልሆነም ተማሪዎቻቸውና ተከታዮቻቸው ፍልስፍናቸውን በፈላስፎቹ ስም ጽፈው እንዲተላለፍ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡


ፍቃዱ ቀነኒሳ

በአዳማ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር

45 views0 comments
bottom of page