top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

"እንግልትና በደል" በቡታጅራ ከተማ ማዛገጃ ቤት ደርሶብናል ይላሉ ነዋሪዎቹ


በደቡብ ክልል በጉራጌ ዞን አሉ ከሚባሉ ከተሞች ተርታ ግንባር ቀደም ከተሞች በግንባር ቀደምነት ተጠቃሽ ነው ። ቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ከተማው የህዝብ ብዛት 60,000 – 80,000 ይሆናል ተብሎ ይገመታል። በአምስት ቀበሌዎች በሁለት ክፍለ ከተማ አወቃቀር የተመሰረተ ነው ። ክፍለ ከተሞቹም እሬሻ ክፍለ ከተማ እና እሪንዛፍ በመባል ይጠራሉ ። የቡታጅራ ከተማ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በሰላምና በፍቅር ይኖሩባታል ። የቡታጀራ ከተማ የሰላም ሰገነት በመባል የምትጠራ ከተማ ናት። በውስጧ ለብዙ አመታት በጉርብትና በዝምድና በነዋሪነት ብዙ ሰዎችን አስተናግዳለች ። በቡታጀራ ከተማ ብዙ በሚባል መልኩ ቢለያይም የመንግስት እና የግል ተቋማት መንግስታዊ ያልሆነ ተራ ድርጅት ጭምር በሰፋፊ እርሻ መሬት ላይ አስተናግዳለች። የመንግስት የቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታል የቡታጅራ ከፍተኛ ፍርድቤት የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ሰፋፊ መሬት ከያዙ የመንግስት ተቋማት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ተመዝግበው ወደ ስራ ከገቡ ድርጅቶች ዱኩማን የነጭ አይጥ ደም ማምረቻ (እስካንቲቦዲ) ሴራሚክ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ እና የዱቄት ፋብሪካዎችን ጭምር እነዚህ ተቋማት መንግስት ያወጣውን መመሪያ ተገን በማድረግ ሰፋፊ መሬት በማጠር ፊት ለፊት በማልማት የህብረተሰብ እሮሮ የሚያስተናግዱ ሆነዋል ።

የመስቃን ሚድያ ኔትወርክ አባላት ማዘጋጃ ቤቱ እንግልትና በደል አድርሶብናል በማለት አቤቱታ ያቀረቡ ከተለያዩ የቡታጅራ ክፍለ ከተማ ቀበሌ ነዎሪ የሆኑ ባለ ጉዳዮችን አነጋግረናል።

ወይዘሮ ጀሚላ ሽፋ ይባላሉ ። በ04 ቀበሌ ነዋሪ ሲሆን 9 ወንዶችና ሀለት (2) ሴቶ ልጆች ያሏቸው ሲሆን በድምሩ 11 ልጆች አሏቸው። ለመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ጥየቃ ለአመታት ቡታጅራ ማዘጋጃ ቤት ተመላልሰዋል ። ነገር ግን ጉዳዩ ምላሽ ማግኘት አልቻለም ። ምላሽ ያልተሰጠበት ምክንያት ሲናገሩ ፦ እትብቴ የተቀበረበት ወልጄ ከብጄ የዳርኩበት ቦታ ነው ። ማዘጋጃው ግን ባይተዋር አድርጎኛል ። ለጥያቄዬ ምላሽ መስጠት አልቻልንም የሚሉት የባለ ስልጣን መቀያየር ነው ይላሉ ። እንዴት ብለን ጠይቀናቸዋል ። እሳቸው የሚሉት መጀመሪያ የነበረው የማዘጋጃ ባለስልጣን አልመለሰላችሁም ? እኔም ላጣራ ይሉኛል ። ላጣራ ያለውም አካል ስድስት (6) ወር ሳይቆይ ከስልጣኑ ይወርዳል ። የመጣውም ላጣራ ነው እያለ እሱም ይወርዳል ። አንዱ ስልጣን ላይ ሲወጣ አንዱ ከስልጣን ሲወርድ የኔ ጉዳይ አስራሁለት አመት )12) ሞላው ። በፊት የነበሩ ባለ ስልጣናት ለልጆቼ እንዲሰማቸው ፅፈውልኛል። የተፃፈው ደብዳቤ በእጄ ይገኛል ። ፍትህ አጣሁ ። እነዚህንም በቁጥር የጠቀስኳቸው ልጆች ለመኖር በሚከብድ ሁኔታ አብረውኝ ይኖራሉ ብለዋል ።

በመቀጠል አቶ ሁሴን ሳይድ ይባላሉ ። አድራሻቸው ቡታጅራ ከተማ በ03 ቀበሌ ቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታል በስተጀርባ ናቸው ። ሰፊ የሆነ በይዞታቸው ስር የነበረ የእርሻ መሬት የነበረ ሲሆን ሆስፒታሉ በተሰራበት ግዜ ወደ አንድ (1) ሄክታር ከግማሽ ለልማት እንዲውል ወላጅ እናታቸው በውዴታ ግዴታ ሰጥተዋል ። በጊዜው የነበሩ አመራሮች ለልጆች የሚውለው የመሬቱ ምትክ ሳይሰጡን የሚመጣው ባለስልጣን እንዲሰጠን እና ተተኪውን ቦታ አለመውሰዳችን በፁሁፍ ጭምር በመግለፅ ደብዳቤ ሰጥተውናል ። በተጨማሪም ጉራጌ ዞን ከተማ ልማት ፅ/ቤት ድረስ በመሄድ ደብዳቤ አፅፈን መጥተናል ። ግን ተፈፃሚ አልሆነም ። የማይፈፀምበት ምክንያት እኛም አላወቅንም በጊዜው እናቴ በደረሰብን ክህደት እና በደል በመደናፈጧ እና በመታመሟ ከጊዜ በኋላ ህይወቷ አልፏል ። እኔ ሆስፒታሉ ከተሰራ ጀምሮ እስከ ዛሬ ማዘጋጃ ቤት እመላለሳለሁ ። መፍትሔ የለም ። ምላሽ የለም ። ሁሉም መርዳት የሚፈልገው ሀብታም ነው ። ድሃ በመሆኔ ፍትህን በገንዘብ መግዛት አልቻልኩም ። ስለጠየከኝ አመሰግናለሉ በማለት ሳግ በተናነቀው ደምጽ ወቀሳቸውን ቋጭተዋል።

ሌላኛውም ባለ ጉዳይ ሀሳባቸው ቀጠሎ ። ወይዘሮ ወለላ ዶቦ ይባላሉ ። አድራሻ 01 ቀበሌ ነው ። ቡታጅራ ማዘጋጃ ቤት ሙሉ 15 አመት ተመላልሻለሁ ። መልስ አይሰጡም ። ቦታው ከቡታጀራ ፈትህ መስጅድ ዝቅ ብሎ የሚገኝ የእርሻ መሬት የነበረ ሲሆን መንግሥት ለኮንዶሚኒየም ልማት ፈልጎታል ተብዬ የእርሻ ስራውን አቋርጬ እንደዚሁ አለሁኝ። ብዙ ቤተሰብ አለብኝ ። ስድስት (6) ወንድ ልጅ አራት(4) ሴት ልጆች አሉብኝ ። ልጆቼ ወደ ሳውዲ አረቢያ ለስራ ሄደው የነበር ሲሆን በ2005 ዓ.ም በተነሳው ረብሻ ንብረት ገንዘባቸውን በመጣል ከሳውዲ አረቢያ ተመለሰው ሀገር ገብተዋል ። አብዛኛዎቹ ከራሴ ጋር ነው የሚኖሩት። የቡታጅራ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሰው መርጦ ምላሽ የሚሰጥ ተቋም ነው ። መሾም እንዳለ ሁሉ መሻርንም መርሳት የለብንም ይላሉ ። ሌላኛውና የመጨረሻው ባለጉዳይ አቶ አወል ናስር ይባላሉ ። ቀበሌ 01 በአሁን ሰአት ዋልታ ጀርባ በመባል የሚጠራው አካባቢ ነዋሪ ሲሆን በ2000 ዓ .ም በከተማ ቦታ የወጣ የመሬት ሊዝ አዋጅ ለማስፈፀም እንደማንኛውም ህብረተሰብ በእርሻ መሬታችን ጨረታ ወጥቶ ቢሆን አይሰማኝም ። በግምት ለአንድ ባለ ሀብት ከነ ባለቤቱ የእናቴ ይዞታ የሆነውን መሬት 400 ካ.ሜ አሸንፈዋል በማለት የቡታጅራ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ለመሰለው ሰው ችግር ፈቺ ላልመሰለው ሰው ችግር አምጪ ሆኖ ቀጥሏል ። የመንግስት ተቋማዊ ለውጥ ያልተቀበለ መስሪያ ቤት ቢኖር የቡታጅራ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም ። የቡታጅራ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ለሀብታም ብቻ ነው የሚያስተናግደው በማለት በምሬት ተናግረዋል ።

የመስቃን ሚድያ ኔትወርክ በአካባቢያቸው መብታቸውን ተነፍገው የሚኖሩት ሰዎች ወደ ተቋሙ የሚመጡ ባለጉዳዮች ከሰባት (7) አመት በላይ የተንከራተቱ መሆኑን አንባቢዎቻችን ግንዛቤ ውስጥ ብታስገቡልን እና ከየቀበሌው ጉዳያቸው ለረጅም ጊዜ እየተንከባለለ እዚህ የደረሰ መሆኑን ጭመር እናአሳስባለን።


ሻኪር አህመድ

መስቃን ሚድያ ኔትወርክ ቡታጅራ

 

ማሳሰቢያ

ውድ አንባብያን እላይ የተጠቀሱት ባለጉዳዮች ጉዳያቸው ከምን አግባብ እንዳለተፈጸመላቸው የሚመለከተው የመንግስት አካል የሚያውቀው ስለ መሆኑን ምንም ጥርጥር የለንም። የመንግስት አካል ህዝብን በእኩል ግልጋሎት የሚሰጥ እንዳለ ሁሉ በተቃራኒው ለጥቅም የተገዛ እንዲሁም ግልጋሎት ፈልጎ ለሚመጣው ባለጉዳይን በቸልተኝነት እና በቅጡ ማስተናገድ ባለመቻላቸው በርካታ ባለጉዳዮች ጩኸታቸው ሰሚ አጥቶ በገዛ ሃገራቸው ሁለተኛ ዜጋ ሆነው የኖሩበት የ27 አመቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። እላይ በስም የተጠቀሱት አቤቱታ አቅራቢዎች ወቀሳቸው ትክክል አይደለም የሚል እምነት የለንም። እንዲሁም የቀረበው አቤቱታ ፍጹም ትክክል ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ባንደርስም ተገልጋይ እንደ ግለሰብ ከፍላጎቱ አንጻር የሚያቀርበው ወቀሳ ትክክለ ነው ባይ ነን። ነገር ግን የሚመለከተው ግለጋሎት ሰጪ አካል ለዜጎች በእኩል ግልጋሎት መስጠት ስላለበት ከግለሰቦቹ ጉዳይ ጋር ተያያዥ የሆነው የህግ አግባብ ምን ይመስላል የሚለው በአፋጣኝ ምላሽ ይሰጥበታል የሚል ተስፋ አለን። ሌላው… ጉዳዩን በማየቱ ሂደት ውስጥ በሁለቱም ወገኖች መካከል ሊኖሩ የሚችሉ እውነታዎች ተገልጸው ለጠያቂ ምላሽ የሚሰጥበትና የተወቃሽ ስም የሚታደስበትና የሚካስበት ሁኔታ ሊከሰት ይችል ይሆናል የሚል እምነት አለን። ቸር እንሰንብት


መስቃን ሚድያ ኔትወርክ

ዝግጅት ክፍል

80 views0 comments
bottom of page