top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

"ከኮፍያው በስተጀርባ" (በሳዲቅ አህመድ)

Updated: May 30, 2020


እርሳቸው የሐይማኖት አስተማሪ ብቻ አልነበሩም።ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ አሰራርን ጭምር የተካኑ ቢሆኑ እንጂ።ማን ናቸው? ከምድረ-ጉራጌ በእግር ተጉዘው ወደ ዳና-ወሎ በመዝለቅ የእውቀት (የኢልም) ካባን ደርበው የተመለሱት ሼህ ኢሳ አልቃጥባሬ።

ዘመኑ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ዜግነትን የተካዱበት ነበር።ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሳይሆን «በኢትዮጵያ የሚገኙ እስላሞች» የሚለው ፊውዳላዊ አጠራር ዛሬም ከትውልድ ህሊና መውጣት ያልቻለ የትላንት ስንክሳር ነው። አግላይ የሆነው ተረት ዛሬም በሗላቀሮች ዘንድ ይደሰኮራል። «የእሳላም አገሩ መካ የአሞራ አገሩ ዋርካ» የሚለው ምናባዊ ትርክት ዛሬም የዋሁን ጠልፎ በአስተሳሰብ የሚቀፈድድ ችካል እንደሆነ ነው።


•የሁሉም ያልነበረችው ኢትዮጵያ


መሳፍንቱና መኳንንቱ የሚንፏለሉባት አዲስ አበባ የሙስሊሞችን ተሳትፎ የማትሻ ነበረች።ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ምጥቀትን የተካኑት ሼህ ኢሳ በብልሃታቸው እስከ ቤተ መንግስት ዘልቀው በመግባት የlobbying (የማግባባት) ስራ የሚሰሩ ነበሩ።እንደ ሐይማኖት መሪ ከመኳንንቱ እና መሳፍንቱ ጋር ዘና ብለው የሚቀመጡ ሳይሆን ብድግ ብለው ማስተናገድ የማይገዳቸው ሁለገብ ሰው እንደነበሩ ይነገራል።በዘመኑ እቃ የሚሸከም ሰው «ውራጌ...ውራጌ» ተብሎ ይጠራ እንደነበር የሚናገሩት ቀደምት አባቶች በሼህ ኢሳ ጥረት ከጉራጌ ወደ «ኩሊ...ኩሊ»ነት መቀየሩን ይናገራሉ።


የዜግነት መብት በተገፈፈባትና ሶስት የሙስሊም አመት በዓሎችን ማክበር በተከለከለባት ኢትዮጵያ ውስጥ በአዲስ አበባ፣ቃጥባሬ፣ቡታጅራ፣እንሴኖ እና ቆሼ በተባሉት ቦታዎች የራሳቸውን ማእከላትን ወይም መስጊዶችን በመገንባት በስራቸው ብዙ አስተማሪዎችንና ተማሪዎችን በማካተት በወቅቱ በገዢዎች ተነጥቆ ሊወሰድ የነበረውን እምነት በማቆየቱ ረገድ ታላቅ ስራን ሰርተዋል ሼህ ኢሳ።የሼህ ኢሳ ተከታዮች በዛሬው አጠራር ህብረ-ብሔራዊነትን የተላበሱ ነበሩ።ሰባቱ የጉራጌ ማእዘኖች፣ቀቤናዎች፣መስቃኖች፣ሶዶዎች፣ወለኔዎች፣ስልጤዎች፣ማረቆዎች፣ኦሮሞዎችና ሌሎችንም አዋህደው መምራት የቻሉ ድንቅ ሰው መሆናቸው ይታወሳል።


•የታላቅ ራእዮች ባለቤት የነበሩት ሼህ ኢሳ


ሼህ ኢሳ ወጣቱ ሐይማኖትን መማር ብቻ ሳይሆን ሁለተናዊ በሆኑ የአገር ጉዳዮች ላይ ተሳታፊ እንዲሆን አድርገዋል።ወጣቱ በውትድርና ውስጥ ኢንዲገባና በሒደት ወታደራዊ ስልጣንን እንዲቆናጠጥ መክረዋል።ወጣቱ ቀስት መወርወርን፣ዋና መዋኘትን፣ነጻ ትግል ማድረግን፣መንጃ ፈቃድ ማውጣት፣በመንግስት ስራ ውስጥ መግባትና ወደ ተለያዩ ቦታዎች ተንቀሳቅሶ በንግስድ ይሰማራ ዘንድ ስልጠና ይሰጡ የነበሩ ድንቅ ሰው ናቸው።ልዩ ኮፍያ ለምን?


የሼህ ኢሳ ድምቀት (popularity) በመሳፍንቱና መኳንንቱ ዘንድ ቅናትን ፈጠረ።በመቶዎች የሚቆጠሩ ደረሳዎችን (የቆሎ ተማሪዎችን) አስከትለው ወደ አዲሳበባ በሚገቡት ሼህ ኢሳ ላይ ትንኮሳ ተጀመረ።በንጉሱ ዘመን የነበረው ወዋቅራዊ አሰራር የእሳላም ኮፍያ የሚለብሱ ሰዎች ላይ በጭቆናው ላይ ድርብርብ ጭቆናን ይጭንባቸው ጀመር።በዚህ ፈታኝ ወቅት ነበር ሼህ ኢሳ የራስቸውን የእስላም ኮፍያ በመፍጠር ተከታዮቻቸውን ማስለበስ የጀመሩት።አረንጓዴ፣ቢጫ፣ቀይ ቀላማት ጥለት ላይ ተጨማሪ ሁለት ቀለማትን በመጨመር «የቃጥባሬ» ተከታዮች መለያ አደረጉት። ሶስቱ ቀለማት የአገር ሰንደቅ አላማን ሲወክሉ ጥለቶቹ አምስት መደረጋቸው ደግሞ አምስት የእስልምና ማእዘናትና በቀን አምስት ግዜ የሚሰገዱትን ሰላቶች ለማመላከት እንደሆነ የድሜ ባለጸጋዎች ያስረዳሉ።


ሙስሊሞችን በመተናኮስና ሙስሊም ጠልነትን (Islamophobia)ን በአገዛዙ ውስጥ በማስረጽ ይሰሩ የነበሩት የዘውድ አማካሪዎች በነርሱ አጠራር የ«ቃልቻው» አካሔድ ስጋት ሆነባቸው።የሼህ ኢሳ ተከታዮች በአዲስ አበባም ሆነ በመላው ሸዋ በአዲስ የእስላም ኮፍያ ደምቀው መታየት ጀመሩ።አንዳንድ ባለስልጣናት ኮፍያው እንዳይለበስ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥሉ።ጉዳዩ ንጉሱ ዘንድ ደረሰ።የሼህ ኢሳ ተቀናቃኞች ቅሬታቸውን ያሰማሉ።በፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ላይ ምጡቅ የነበሩት ሼህ ኢሳ «ንጉስ ሆይ!...ንጉስ በህይወት እያለ ሰንደቅ-አለማ ዝቅ ይላልን?» ብለው ጥያቄ ያቀርባሉ።በርግጥም ታዋቂ ሰዎች ሲሞቱ፣በአገር ላይ ሐዘን ሲደርስ፣የአገሪቷ መሪ ወይም ንጉስ ሲሞት ሰንደቅ አላማ ዝቅ ተደርጎ ይውለበለባል። የሼህ ኢሳ ጥያቄ ምትሃታዊ ነበር። ንጉሱ ከመፍቀድ በስተቀር አማራጭ አልነበራቸውም።ይህ በዚያ ዘመን የተስተዋለ አይነተኛ የሰላማዊ ትግል እሴት ነው።


በዚያ ዘመን ይህንን ኮፍያ መልበስ ስልጡን የሚያስብል እንደነበር የታሪክ አዋቂዎች ያስረዳሉ።በግዜ ሒደት ውስጥ ኮፊያውን ከባእድ አምልኮ ጋር ለማጣመር የሚሰማው ትርክት ላይ አበይት የሆኑ ታሪካዊ እይታዎችን በማቅረብ ሚዛናዊነት ሊኖር እንደሚገባ ማሳየቱ ተገቢ ነው።ይህ ኮፍያ አንዳንዶች እንደሚያሳዩት የአንድ ቡድን ሙሪድነት (ተከታይነት) መገለጫ ብቻ ሳይሆን «በኢትዮጵያ የሚገኙ እስላሞች» ወይም «የእስላም አገሩ መካ የአሞራ አገሩ ዋርካ» እያለ የዜግነት መብትን የነጠቀውን ፊውዳላዊ አገዛዝ «የለም አገሪቷ የሁላችንም ናት» እየለ የሞገተ የማንንነት ሰንደቅ ነው።በዚህ አጋጣሚ ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች እንደዜጋ መቆጠር የጀመሩት የንጉሱ አገዛዝ ከተገረሰሰ በሗላ መሆኑን ልብ ይሏል።


•አገርን የመጠበቅ ሐላፊነት በንጉሱ ሽሽት


በጣሊያን ወረራ ወቅት ንጉሱ አገር ጥለው ሲወጡ ሼህ ኢሳ አልቃጥባሬ የራሳቸውን አገር ጠባቂ ግብረ-ሐይል አዋቀሩ።ወታደራዊ ስልጠናና ማእረግ አስፈላጊ መሆኑን ያስተማሩት ሼህ ኢሳ ልጃቸው ሱልጣን ለሻለቃነት ማእረግ እንዲደርሱ አድርገዋል።የንግሱ አገዛዝ ከሻለቃነት በላይ ባይፈቅድላቸውም በሻለቃ ሱልጣን የጎበዝ አለቃነት የሚመራው ጦር ቦረና ሔዶ አገሩን በመጠበቁ ረገድ የነበረው ተጋድሎ የላቀ ነበር።ጦሩ ምስጋናና ሽልማትን አላገኘም።አጼ-ሐይለስላሴ በሼህ ኢሳ አልቃጥባሬ ስም የተጭበረበረ (forged) ደብዳቤ በመጻፍ በጦሩ ውስጥ ወከባ ከፈጠሩ በሗላ ልክ በእርበኛው በላይ ዘለቀ ላይ የፈጸሙትን አይነት ክህደት ፈጸሙ።የሻለቃ ሱልጣን አገር ወዳድ ጦር በቁም እስር እንዲቀጣ ተደረገ።በዚህም ሳቢያ ብዙዎቹ በሲዳማ ውስጥ ኑሮአቸውን እንዲመሰረቱ ተገደዋል።በተለምዶ አራዳ በመባል በሚታወቀው አካባቢ ይርጋአለም ከተማ ውስጥ «መስቃን ሰፈር» የሚባለው ቦታ የቁም እስረኞችና ራስ ደስታን ተከትለው የሔዱ ሰዎች የመሰረቱት እንደሆነ ይነገራል።«ሼሁዬ የነፍስ አባት ይሁኑኝ» የሚል የሚሰልም ሰው እስኪበዛ ድረስ ሼህ ኢሳ ወደ የአሁኑ የአማራ ክልል ተልከው በንጉሱ መታሰራቸውም የሚዘነጋ አይደለም።


•ተያያዥነት ያለው የግል ታሪክ


ኢትዮጵያ የሁሉ ትሆን ዘንድ ራእያቸውን ካሰረጹባቸው ወጣቶች መካከል የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ወላጅ አባት ይገኝበታል።ከደረሳነት (የቆሎ ተማሪነት) ህይወትም ባሻገር በሼህ ኢሳ ራእይ መሰረት ሾፌር ለመሆን ወደ አዲስ አበባ ያቀናው አህመድ ተክለሐይማኖት (በርበሬ ተራ) አካባቢ ሻይ ቤት በመክፈት መንጃ ፈቃድ የሚባል ድግሪውን ለመጨበጥ ለአመታት ጥሯል።ፈተናዎችንበተደጋጋሚ የመውድቅበት ሚስጥር አልተከሰተለትም።ተስፋ ቆርጦ አዳሚቱሉ በመሔድ ያለመንጃ ፈቃድ የትራከተር ሾፌር ሆኖ ይቀጠራል።ለጋብቻ ወደ ቡታጅራ ያቀናና የጫጉላ ግዜውን እንደጨረሰ ባለቤቱን ይዞ ወደ ወደ ሲዳማ/ይርጋ አለም ያቀናል።የአርበኛነት ማእረጋቸውን በንጉሱ የተነጠቁት የሩቅ ዘመዱ በሙስሊም ስም መንጃ ፈቃድ እንዳያወጣ ይመክሩታል።ምክሩንም ሰምቶ «ክንፈገብርኤል ቀጸላ» በሚል ስም ሲፈተን በአንድ ሙከራ ፈተናውን ያልፋና የወቅቱን 1ኛ ደረጃ መንጃ ፈቃድ ይወስዳል።ልክ የንጉሱ አገዛዝ ሲወድቅ በዘመነ ደርግ «አህመድ ኡስማን ሐቢብ» በሚል አውነተኛ ስሙ የ2ኛ ደረጃ መንጃ ፈቃዱን ወስዷል።


በንጉሱ ዘመን የመንግስት ስራን ለመቀጠር ሐይማኖትን ወይም ስምን እንዲቀይሩ የተገደዱ ብዙ ናቸው።አንዳንዶቹ ሐይማኖትን መቀየር ብቻ ሳይሆን በጋብቻ ከስርዓቱ አራማጆች ጋር እንዲቀየጡ ተደርገዋል።በዚህም መሰረት ማንንነታቸውን እንዲመናመን ሆኗል።ማንነታቸውም ቢመናመንም ልጆቻቸው የከፍተኛ ደረጃ ትምርትን፣የውጭ አገር የትምርት እድልን በማገኘት በዘመነ ሐይለስላሴም ሆነ በዘመነ ደርግ ካልያም በህወሃት/ኢሃዴግ ቁልፍ ቦታዎችን ለመጨበጥ በቅተዋል።ጨቋኝ በነበረው የትምርት ስርዓት ውስጥ በኢዶችና በመውሊድ ፈተና እንዲሰጥ እያደረገ ሙስሊም ተማሪዎች ላይ ይደርስ የበረውን አይረሳም።በስርዓተ ትምርቱ ውስጥ የነበረው ግፍ ለንጉሱ አገር በቀሉ የለውጥ ጅማሮ አለብላቢት ሲሆንባቸው ጋብ ማለቱ ተስተውሏል።ቀደም ሲል የትምርት እድልን ተነፍገው በእገር ድንበር አቋርጠው ከሱዳን ወደ ግብጽ የደረሱ አገር ወዳዶች ትምርታቸውን ከአገር ውጪ በማጠናቀቅ ወደ አገር በመመለስ የጨቆኟቸውን ንጉስና አገርን ያገለገሉበት እውነታን ልብ ይሏል።በዚህ አጋጣሚ ቀልጣፋው ሼህ ኢሳ «የዟሊሞችን ቋንቋ ተማሩ» ወይም «የነዚያ ጨቋኞችን ቋንቋ ተማሩ» በሚል እሳቤ በድብቅ ቄስን በመቅጠር ማንበብና መጻፍ እንዲማሩ ካደረጓቸው ታዳጊ ወጣቶች መካከል የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ወላጅ አባት አንዱ ነው።


•ኮፍያው የትግል መለዮ ነበር


ኮፍያው ኢትዮጵያዊ ዜግነትን ለመቀዳጀት በተደረገው ትንቅንቅ ውስጥ «የትግል መለዮ» ነበር።ለምሳሌ ባለንበት ክ/ዘመን ስብሰባዎች ወይም አመት በዓሎች ለሰላማዊ ትግል ፍጆታ ሲውሉ ይታያል።ተመሳሳይ በሆነ መልኩ በሼህ ኢሳ አልቃጥባሬ እዝ ስር ሳምታዊና ወርሃዊ ስብሰባዎች ይካሔዱ ነበር።ስብሰባዎቹም ኢስነኢንና ሊቃህ በመባል ይታወቃሉ።በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚሳተፉባቸው ስብሰባዎች (ኢጅቲማአዎች) ሐይማኖታዊ እሴትን በማስረጽ፣አዳዲስ ስነ-ጽሁፋዊ ስራዎችን በመንዙማ መልክ በማቅረብ ውዳሴ የሚደራባቸው ብቻ ሳይሆኑ ጭቆናን ለመከላከል ማህበረሰባዊ መስተጻምር የሚዳብርባቸው ነበሩ።እነዚህን ነባር ተሞክሮዎች ስራፈትነት የሚደራባቸው ብቻ አድርጎ በክፉ ጎናቸው ለማሳየት ከመጣር ይልቅ እንደምን ከ21ኛው ክፍለ ዘመን እውነታዎች ጋር አጣምሮ ወጣቱ ከምርታማናነት (productivity) ሳይወጣ ማህበራዊ ትስስሩን ለበጎ ነገር መጠቀም ይቻላል? የሚለው ችላ ሊባል የማይገባ ጥያቄ ነው።


ለማጠቃለል ዛሬ ፌዴራሊዝም በሚል እሳቤ ክልሎችና ዞኖች የቀለም ወይም የአርማን መለዮ እንደሚያደርጉት ሁሉ በቀድሞ አጠራር የተወሰኑ የሸዋ ሰዎች የሸዋዉን ፖለቲካዊና ፊውዳላዊ ቅምጥል (elite) በብልሃትና በሰላማዊ መንገድ ለመሞገት የተጠቀሙበት የአገር ፍቅር ተምሳሊት እንጂ ዛሬ እንደሚነገረው ኮፍያው የአንድ አንጃ መገለጫ ብቻ አይደለም።ከኮፍያው በስተጀርባ ትግል አለ።ከኮፍያው በስተጀርባ መስዋእትነት አለ።ከኮፍያው በስተደርባ ስልጡንነት ነበር።ከኮፍያው በስተጀርባ የነበሩ አስተዳደራዊ ጭቆናዎችን በራስ ጫንቃ ላይ ተሸክሞ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለን ህይወት የመስጠት ራእይ አለ። ዛሬ ምእራቡ አለም በሆሊውድ ልቦለዳዊ ትርክትና አዲስ ማንነትን በብቃት ሲያሰርጽ «የራስ ያሉት የራስ» ነው እንደሚባለው ትውልዱ «ራስ-ጠል» ከመሆን ታቅቦ ከአባቶቹ ጥረት ጠቃሚውን በመውስድ ጎጂና ዘመንን የማይዋጁትን ለታሪክ መዘክርነት በማስቀመጥ የተሻለ ህይወትን ለቀጣዩ ትውልድ ሊሰጥ ግድ ይለዋል።የድሮዎቹ የተታቻላቸውን አድርገዋል።እነሱ ሩጫቸውን ጨርሰዋል።በሩጫው የዱላ ቅብብል ትንፋሽ እስኪያጥራቸው ሩጠው ዱላውን ለአባቶቻችን አቀብለዋል።አባቶቻችን ዱላውን ለእኛ ሰጥተዋል።እኛስ ምን እያደረግንነው? በእርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ አስተዳደራዊ በደል ተቀርፏልን?


ልብ ያለው ልብ ይበል!


ማሳሰቢያ

ሌሎች ያሏቸውን የማንነት መለዮዎችና የትግል ሒደቶች በአልባሳት ለማሳየት እንደሚጥሩት ሁሉ ይህም የህዝቦች ማንነትና የትግል ውጤት ነው።መሰል የማንነትና የትግል መገለጫዎችን የዘመኑን ፖለቲካዊ ሐረጎችን በመጠቀም ለመፈረጅና ለማሸማቀቅ የሚደረግ ጥረት ካለ በቁጥር አናሳ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ልክ እንደ ቀደምት የገዥ መደቦች ደፍጥጦ በራስ ስር ለማስገባትና ለመጨፍለቅ ከሚደረግ ጥረት ተለይቶ አይታይም።

172 views0 comments
bottom of page