top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

" ከፍተኛ የሆነ እንግልት በቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታል እየደረሰብን ነው" ይላሉ ታካሚዎች !!


“ህክምና ከበር ይጀምራል ይላሉ ታማሚዎች”

እግር ጥሎዎት ወይም ችግር ደርሶብዎት ወደ ህክምና ማዕከል ከሄዱ ከበር ጀምሮ የሚደረግልዎት እንክብካቤና መስተንግዶ የህክምናው አንዱ አካል ነው። ዶክተሩ ዘንድ እስኪደርሱ ድረስ ከበር የሚቀብለዎት የጥበቃ ሰራተኛ እና የካርድ ክፍል አቀባበል ህመምዎን የሚያባበብሱ ወይም የሚያሽር ነው የሚሆነው። ቅን እና ለሙያው ታማኝ የጥበቃ ሰራተኛ እና የካርድ ክፍል ከገጠምዎት በሚሰጥዎት መልካም መስተንግዶ ዶክተሩ ዘንድ ሳይደርሱ ከህመምዎ መፈወስ ይጀምራሉ። በተመሳሳይ የሚፈለገውን እንክብካቤ ከበር ጅምሮ ካልተገኘ ህመሙን የሚያባብስ ነው የሚሆነው። በቡታጅራ የአጠቃለይ ሆስፒታል ለታካሚዎች የሚያደርጉት መስተንግዶ ምን ይመስላል ? በጋራ በመሆን እንቃኘው ፡-


ተገልጋይ - 1

የቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታል ለረጅም ጊዜ ለህክምና መጥቻለሁ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበላሸ ነው የሄደው ። አሰራር ካርድ ክፍል ሄደህ ረጅም ሰአት ትቆማለህ ። እንደገና ህክምና ክፍል ሄደህ ሀኪሙ አይመጣም እንደዛው ትጉላላለህ ።ሀኪሙ ገብቶ ተመርምረህ እንኳን ወደ ላብራቶሪ ቢልክህ የሌላ ሰው የምርመራ ውጤት ሊሰጡህ ይችላሉ ። ጠዋት ወጥተህ ካርድ አውጥተህ የማግስቱ ላትታከም ትችላለህ ። ወዲያውኑ ታክሞ የሚሄድም ታካሚ ታያለህ ። ይህን ችግር ያመጣው የተቋሙ ከደረጃ መውረዱን ያመለክታል ። ከ2000 ዓ.ም ተሸላሚ ሆስፒታል መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ተገልጋይ ሁሉ በእኩል መታየት አለበት ። ተገልጋይ ዛሬ ነው ለህክምና የመጣሁት የገጠመኝ ነገር ከጥበቃ ጀምረህ ስርአት የለም ማለት ትችላለህ ። ጥበቃዎች የሚያውቁት ሰው ከመጣ ተጣድፈው ጣልቃ በመግባት ካርድ ያወጣሉ ። በጣም የታመመ ሰው ከሆነ ችግር የለውም ያለኝ ሀሳብ ይኸው ነው ።


ተገልጋይ - 2

እኔ ልጅ አሞብኝ ነው ። የመጣሁት ጠዋት ነው የመጣሁት አሁን አራት ሰአት ነው ። አልገቡም አንድ የመንግስት ተቋም እስከ 2:30 የስራ ሰአት መሆኑን ነው የሚገባኝ እንደ ህክምና ደግሞ ሰአት መኖር አልነበረበትም ። ጊዜ የማይሰጡ በሽታዎች ስለሚኖሩ ይኸው እንደምናየው በጣም ብዙ ሰው ነው ያለው ። ዛሬ ሰኞ ነው ተገልጋይ ሊበዛ ይችላል ።

አንድ የህክምና ተቋም የማያቋርጥ ስራ መስራት እያለበት እንግልቱ ለምን እንደሚያስፈልግ አልገባኝም ። እኔ በግሌ በተቋሙ የሚሰሩ ሀላፊዎችን በስራ ላይ አለመገኘት ይህን የተገልጋይ እንግልት እንደሚፈጠር ይሰማኛል ። የተቋም ሀላፊ የሆነ ሰው ተገልጋዩን በሙሉ ይህን በከፊል ምን ችግር አለ ብሎ መጠየቅ ይኖርበታል ባይ ነኝ ።


ተገልጋይ -3

እኔ ከሩቅ ነው የመጣሁት በነበርኩበት ቦታ በጤና ጣቢያ ደረጃ ህክምና ወስጃለሁ ። ለተሻለ ህክምና ወደ ቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታል ተገኝቻለሁ ። መስተንግዶቸው በጣም ዝቅተኛ ሆኖ ነው ያገኘሁት ። እኔ ማንበብ አልችልም ወስዶ የሚያሳይህ ሰው የለም ።ተቋምንም ተቋም የሚያሰኘው በውስጡ የሚሰራው አገልግሎቶች ያማረ አካሄድ ይዘው ሲጓዙ ነው ። አብዛኛው ሰው ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን ተጠቃሚ ነው ። ሳይ እነሱም ይንገላታሉ ። እኔ የመጣሁት ከዛ በፊት በነበረው ታሪክ ነው ።ዛሬ ግን ታሪኩ መበላሸት የለበትም ። አሁንም ጊዜው ገና ነው ። የነበረ ታሪኩ መመለስ ይችላል ባይ ነኝ ።


የመጨረሻው ጥያቄ ያቀረብንላቸው ተገልጋይም እንዲህ ይሉናል፦

የመጣሁት ከጦራ ስልጤ ዞን ነው ። የመጣሁትም እህቴ ታማብኝ እህቴን ለማሳከም ነው ። እንደ ቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታል ባለሁበት ቦታ በጣም ጥሩ የሆነና የተሸለመ መሆኑ ሰምቻለሁ ። ስመጣ ግን የገጠመኝ የመረጃ አያያዝ በጣም ቸልተኛነት አለ ። የሌላን ሰው የምርመራ ውጤት ቀይሮ እስከመስጠት የገጠመኝ ። ሌላው ደግሞ እዛ ሂዱ እዚህ ሂዱ የሚባለው ነገር ንባብ ለማይችሉ የሚያሳዩ ባለሙያዎች ቢኖሩ ባይ ነኝ ። ይህንን የአገልግሎት ቅሬታ ተኝተው ባሉት ህክምና የሚወስዱት አዋቂና ህፃናትን መገልገያ ቦታ ገብቶ MMN ለመቃኘት ሞክሮ ነበር ። ግን የቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ወደ ጉራጌ ዞን ለስብሰባ ስላመሩ የተወከሉት አካላት ለማነጋገር ስንጠይቅ ከዚህ በፊት ሆስፒታላችን የሚያጠለሹ ነገሮች በማህበራዊ ሚዲያ ተለቆብናል ። አሁን ገብታችሁ መጠየቅ አትችሉም ብለው መልሰውናል ።


ውድ አንባብያን የመንግስት ተቋም የዜጎች መገልገያ እንጂ እንግልትና በደል የሚደርስበት ቦታ መሆን የለበትም። እንግልት አድራሽ የሆነ መንግስት ተቋምን በተመለከተ በደሎቹን ወይ ቅርታዎቹን ለህዝብና ለሚመለከተው የመንግስት አካል በማሳወቅ ችግሩ ይቀረፍ ዘንድ ተግተን እንሰራለን። የቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታልን በተመለከተ አብዛኛው ቅሬታ የቀረበው በመገልገያ ተቋም ሆኖ የጠየቅናቸው ቅሬታ አቅራቢዎች ከሁሉም የህክምና መስጫ ክፍሎች ሲሆን ጉዳያቸው ከካርድ ክፍል ፣ ከድንገተኛ የእናቶች ቀጠሮ መከታተያ የተያያዘ መሆኑን ለማስገንዘብ እንወዳለን።


ሻኪር አህመድ

መስቃን ሚድያ ኔትዎረክ ቡታጅራ

119 views0 comments
bottom of page