top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

“ውሉ የጠፋው ድውር” (በእሙ ኢሳን)


ዛሬ… ዛሬ ለመኖር ዘር አልባ መሆን ሳይሻል አይቀርም። ያለበለዚያ… ልክ እንደ እንሰሳ በዘር… በዘር ተከፋፍለን አንበሳ… ካንበሳ አህያም… ካህያ ጋር መኖር ብቻ ሊኖርበት ነው ። እንደሰው ስናስብ ደግሞ የምንግባባት ቋንቋ አለን። ታዲያ የመግባቢያው ቋንቋው ካለን ለምን አንዳችን ካንዳችን አልተረዳዳንም ? ለመኖር በክልል ታጥረን እዚህ… ማዶ ያለው ሰው ከወድያኛው ማዶ ካለው የጎሪጥ እየተያየ አለመተማመን በሰፈነበት በዚህ ዘመን ውሉን የሚያገኝልን አይናማ እና ብልሃተኛ ያስፈልገናል። ሃገራችን በታመመችበት ወቅት ዶክተር አስፈልጓት ኖሮ ለህመሟ ፈውስ ይሆናት ዘንድ ተማጽና ኖሮ… ሃኪም አገኘች ታዲያ የተገኘው ሃኪም ጊዜያው ማስታገሻ እንጂ ፈውስ አላስገኘላትም። ግን… አሁምን ቢሆን ውሉ ስለጠፋ እንጂ የድውሩ ውል ቢገኝ ኖሮ ከማስታገሻነት ወደ ፈውስ ታመራ ነበር ። ግና ለዶክተሩ ሌላ አይናማ ሃኪም ያስፈልገዋል ህመሟን የሚያሳየው ወይም የሚያግዘው “በሽታውን የደበቀ መድሃኒት አይገኝለትም” አይደል የሚባለው። ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ለዶክተሩ ህመማችንን እና የሆዳችንን መንገር ይጠበቅብናል። ሆድ ለሆድ ከተገናኘን እና አይናማው ዶክተር ህመማችንን ካየልን እና ከተገለጸለት መፈወሱ ለሃኪሙ ቀላል ነው የሚሆነው።

“በዝሆኖች ጥል የሚጎዳው ሳሩ ነው” እንደሚባለው በየክልሉ በጎሳ ሰበብ በሚፈጠረው ችግር የሚጎዳው እድሜ ልኩን ሲሰራና ሲደክም የሚነኖረው ለፍቶ አዳሪው ወገኔ ነው። ጀርመናዊው ናዚ በኢትዮጵያ ዳግም የተወለደ ወይም የተከሰተ ይመስል በዘር መጠፋፈቱ እስከ መቼ ይቀጥል ይሆን? መፍትሄውስ ምን ሊሆን ይችላል? በክልላችሁ እንደፈለጋችሁ ሁኑ ተብለን ብንተው እንኳን ከወትሮ የተለየ የምናገኘው ምንም አይኖርም። ምናልባት የእኔነቱ ልክፍት እየገነነ ይመጣና ከዚያም ያ.. እኔነት ከብሄር ወደ ጎሳ ከእዚያም ወደ ቤተ ዘመድና ቤተሰብ ይወርድና የማይቀረው መገፋፋትና መተላለቅ በአንድ ብሄር ውስጥ ሊከሰት ይችላል። በአለም ታሪክ ከአንድ ብሄር ብቻ ስለተፈጠሩና ያ… ብሄር በአንድ አካባቢ ስለታጠረ ብቻ ሰላም አይሰፍንም። ብልጽግናም አይኖርም። ሰላምና ብልጽግናን ልንጎናጸፍ የምንችለው ሰላምን በሚሹ እና ብልጽግና ባህላቸው ባደረጉ ግለሰቦች ፍላጎት እና ጥረት እንጂ በዘር እና በክልል አይደለም። ለዚሁ ማነጻጸሪያ ይሆነን ዘንድ ጎረቤታችን የሆነችው ሶማልያ አንድ ብሄርና እምነት ያላት ሃገር ብትሆንም የሶማልያ ህዝቦች ሰላም ከራቃቸው እነሆ አመታትን አስቆጥረዋል። ሌላኛው ደግሞ ትላንት ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተከሰተው የተቃውሞና የድጋፍ ሰልፎችን ብንመለከት የአንድ ብሄርን መበትና ፍላጎት ለማስጠበቅ በቆሙ ቡድኖች መካከል የተከሰተ አለመግባባት ነበር። ጎበዝ… እኔነቱን የፈለከውን ያህል ብታከረውና ብታንረውም እንኳን በአንተ ክብ ውስጥ ትሽከረከራለህ እንጂ ሌላው ክብ ውስጥ ገብተህ እንደ ክብህ እንዳሻ ልትሆን አይቻልህም። ለምን ቢባል ሲጀምር እኔነትን መርጠሃልና። አዎን.. ሌላኛው ክብ ለሌላው ልክ እንዳንተው እንዳሻው መሆኛ ሲሆን የምትግባቡበት ቋንቋም አይኖራችሁም። ለምን…? “ለምን ማለት ጥሩ ነው”። አንተ በእራስህን ቋንቋ ስታወራ እርሱም በቋንቋው ከራሱ ሰዎች ጋር ይግባባል። አንተ እኔነትህ አክረኸው ከራሴ ቋንቋ ውጪ አልናገርም እንዲሁም አልሰማም ካልክ መግባባት የሚለው ቃል ዋጋ ቢስ ነው የሚሆነው። ወይም ለመግባባት ሌላ ሶስተኛ ቋንቋ ሊያስፈልጋችሁ ነው። ምንልባት እኔና እኛ ማለት ስትጀምር በተጨማሪም ሌላውን እንደ እራስህ ማየትና ማክበር ስትጀምር ሁሉም ነገር ገር… በገር ይሆናል። ታዲያ ይሀ የሚሆነው ከሻህ ብቻ ነው። የማትሻ ከሆነ ግን እኔም… እኔ ነኝ።

ወገኖቼ ሆይ… በህግ እንደተደነገገው ከሆነ ኢትዮጵያዊው ሁሉ በየትኛውም ክልል ንበረት አፍርቶ መኖር ይችላል ይላል። ታዲያ ህግ አስፈጻሚዎችና አስከባሪዎች የታሉ ? የሌላው ብሄር ተወላጅ ወደ ሌላ ክልል ሄዶ ንበረት ካፈራ በላቡ ጥሮ እና ግሮ ቢሆን እንጂ እዚያ ክልል በመሄዱ ብቻ ከሰማይ የወረደለት መና አልነበረም! አይኖርምም። እዚያ በመሄድ ያፈራቸው ንበረቶች ከክልሉ የታፈሱ አይደሉም ብዙ መስዋትነት የተከፈለበት እንጂ!!


ማስተዋሉን ይስጣችሁ !


እሙ ኢሳን

ሪያድ ሳውዲ አረቢያ

55 views0 comments
bottom of page