top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

"የህዳሴ ግድብ ሙሊትና ለከት ያጣው የግብጽ ስግብግብነት" (በሳዲቅ አህመድ ኡስማን)

ብጽ «ናስር» የተባለውን ታላቁን ሰው ሰራሽ ሐይቅና አስዋን ግድብን ከ50 አመታት በፊት ስትሞላ ለምን የውሃ እጥረት አልገጠማትም? የህዳሴው ግድብ በታቀደለት የግዜ ሰሌዳ ቢሞላ ችግሩ ምንድን ነው?አንዳንድመረጃዎችን በማገላበጥ ለከት ያጣውን የግብጽ ስግብግብነት እንቃኝ።

• ግብጽ የእርሻ ምርቶች ኤክስፖርትና የኢትዮጵያ ድርቅ ኢትዮጵያ 85% ህዝቧ አርሶ አደር የሆነው ኢትዮጵያ ህዝቦቿን መመገብ ባልቻለችበት መልኩ ግብጽ ባላት አፈር ላይ አባይ የሚመርቅላትን ለም አፈር ትጠቀማለች።የራሷን ህዝብ ከመመገብ አልፋ ባለፈው አመት ብቻ 4.6 ሚሊዮን ቶን ፍራፍሬ፣አታክልትና ጥራጥሬዎችን ወደ ሌሎች አገራት ልካለች ሲሉ የእርሻ ሚኒስቴሩ ኢዘዲን አቡ ሰተይት ተናግረዋል።ግብጽ በአመት ከ 2.2 ቢለየን ዶላር በላይ ወደ ውጭ ከምትልካቸው የእርሻ ውጤቶች ገቢ እንዳላት አልየውም የተባለው ጋዜጣዋ ዘግቧል።  ግብጽ ከራሷ ተርፏት የእርሻ ውጤቶችን ኤክስፖርት ማድረጓ ችግር ባይኖረውም በኢትዮጵያ ላይ የምታሳየው ስግብግብነትን መቀበል የሚችል ህሊና የለም።በተለያዩ ግዜያት የአየር መዛባት እየገጠማት ለድርቅ የምትጋለጠው ኢትዮጵያ እራሷን አብልጽጋ ስታበቃ በምግብ አቅርቦት ለወደፊት ከተረጅነት ልትወጣ ግድ ይላታል።ለምሳሌ ከ2007-2008 ኢትዮጵያን ያጠቃው El Niño የተባለው የአየር መዛባት 10 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ለርሃብ አደጋ ማጋለጹን ቢቢሲ በሚያዚያ 3/2008 ካወጣው ዘገባ መረዳት ይቻላል። • የግብጽ ሰው ሰራሽ የናስር ሐይቅና ታላቁ የአስዋን ግድብ ግብጽ ካላት የቆዳ ስፋት ውስጥ 90% የሚሆነው ህዝብ በአባይ ወንዝ አቅራቢያ አንደሚኖር መረጃዎች ያሳያሉ።ይህም አብዛኛው ሰው የሰፈረው በ3.5% የአገሪቱ ይዞታ ላይ መሆኑን ጠቋሚ ነው።አፈራቹን ተሸክሞ ያመጣልኝ «አባይን ለብቻዬ» ለማለት የሚቃጣት ግብጽ የህዳሴ ግድብን የህልውና ጉዳይ ነው ብላ የቃላት ጦርነት ከበሮን መደለቋን ቀጥላለች። አባይን ገድቦ በመጠቀሙ ረገድ ግን መሪዎቿ የተዘናጉ አልነበሩም። የግብጽ አብዮታዊ መሪ ጀማል አብዱል ናሲር በስማቸው የተሰየመውን «ናስር» ሰው ሰራሽ ሐይቅን በአባይ ወንዝ ሙሊት ሰርተዋል። ሐይቁ አለማችን ውስጥ ካሉ ትልቅ ሰው ሰራሽ ሐይቆች ጎራ የሚመደብ ነው።በአማካይ 25 ሚትር (83 ጫማ) ጥልቀት ያለው ይኸው ሐይቅ ጥልቀቱ እስከ 130 ሜትር (430 ጫማ)  ይደርሳል።ጠቅላላ እርዝማኔው 550 ኪሎ ሜትር ሲሆን 83% የሚሆነው የሐይቁ አካል ግብጽ ውስጥ ያለ ሲሆን የተቀረው ደግሞ በሱዳን የኑቢያን መንደሮች ውስጥ የሚገኝ ነው።ይህ ሰው ሰራሽ ሐይቅ 5.97 ትሪሊየን cubic ጫማ ውሃን መያዝ የሚችል ሲሆን ለአስዋን ግድብ የውሃ ሙሊት የዋለና በመጠባበቂያነትም የሚያገለግል ነው።ጀማል አብድልናሲር፣አንዋረል ሳዳትና ሑስኒ ሙባረክ፣ዶ/ር መሐመድ ሙርሲና ጄኔራል አብዱልፈታህ አልሲሲ የተባሉት የግብጽ መሪዎች በአብዮት መሰላላል ላይ ቢወጡና ቢወርዱም በአባይ ላይ ያላቸው አቋም አልተቀያየረም። ግብጽ ከፍተኛ የወዛደር ሐይልን ተጠቅማ በእንግሊዝ መሐንዲሶች ቀመር በሩሲያ ገንቢዎች ጥረት በአንድ ቢለየን ዶላር የአስዋንን ግድብ ገንብታለች።ኢትዮጵያ በአብዮት መባቻና ማግስት ፍዳዋን ስታይ ግብጽ ማንንም ሳታስፈቅድ በአስዋን አካባቢ የነበሩትን 90ሺ አርሶ አደሮችን አፈናቅላ የአስዋንን ግድብ ገንብታ አጠናቃለች።ግድቡን በ1970 (እኤአ) ስትጨርስ ፕሬዝዳንት አንዋረ አሳዳት እንዳስመረቁት መረጃዎች ያሳያሉ።አስዋን 111 ሜትር (364 ጫማ) ርዝመት ያለው ሲሆን የውሃ ሙሊት ቁመናው 3830 ሜትር (12562 ጫማ) ነው።ዛሬ የአስዋን ግድብ ላይ ያሉት 12 ተርባይኖች 10 ቢሊየን ኪሎ ዋት የኤሌክትሪክ ሰዓታትን በአመት እንደሚያመነጩ በብሪታኒካ ሰነድ ላይ ሰፍሯል። የአስዋን ግድብ ግብጽን ክፉ ከሆኑት የርሃብና የድርቅ አደጋዎች የታደገ የግብጽ ምጣኔ-ሐብት የጀርባ አጥንት ነው። • ግብጽ የምትወረውራቸው የተንኮል ወጥመዶች ግብጽ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ የአረብ ሊግን እርዳታ ጠይቃለች።የአፍሪካ ህብረት ያግዛት ዘንድ ጥራለች።የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት እሮሮ አሰምታለች።የአሜሪካን አማላጅነትና ጫና ፈጣሪነትን ተጠቅማለች።በአለም ባንክ ኢትዮጵያን ወጥራ ይዛለች።በሚዲያ የውሸትና የፕሮፓጋንዳ መርዟን ረጭታለች።የጦርነት ከበሮን ደልቃለች።የኢትዮጵያን አጎራባች አገራት በዲፕሎማሲያዊ ሙስና በኢትዮጵያ ላይ  ለማስነሳት ጥራለች።በአገር ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባትና ኢትዮጵያን ለማወክ እየሞከረች ነው። አሁን ደግሞ ሙሊቱን ለማዘግየትና ለማክሸፍ እያሴረች ነው። • በአንድ እራስ ሁለት ምላስ  የህዳሴ ግድብ ሙሊት በግብጽ የእርሻ፣የኤሌክትሪክና የውሃ አቅርቦት ላይ ጫና የሚያሳድር ከሆነ ታላቁን «ናስር» የተባለውን ሰው ሰራሽ ሐይቅ በሞላችበት ወቅት ለምን ችግር አልገጠማትም? ሰው ሰራሽ ሐይቁን ጨርሳ አስዋን ግድብን ስትሞላ የውሃ እጥረት ለምን አልገጠማትም?መልሱ በ‹አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል› ስሌት እኔ ከሁሉም የተፋሰሱ አገራት በላይ ብጠቀምበትም የአባይ ቀዳሚ ባለቤት የሆነችዋ ኢትዮጵያ ድርሽ እንዳትልበት የሚል ለከት ያጣ ስግብግብነት ነው።ግብጽ የስግብግብነት ጥሟን ለማርካት የተንኮል ወጥመዶቿን ብትዘረጋም ኢትዮጵያ በሉዓላዊ ግዛቷ ስር መሰረተ ልማትን ለማሳካት የሚያግዳት ተገዳዳሪ ሐይል ከመጣ ሉዓላዊነትን ከመዳፈር ተለይቶ የማይታይ መሆኑን ልብ ይሏል።

ልብ ያለው ልብ ይበል!

ሳዲቅ አህመድ ኡስማን

16 views0 comments
bottom of page