top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የመጨረሰን ጣዕም የማያውቅ ለራሱ ክብር አይኖረውም (በሚስጥረ አደራው)

የመጨረሰን ጣዕም የማያውቅ ለራሱ ክብር አይኖረውም (በሚስጥረ አደራው)
የመጨረሰን ጣዕም የማያውቅ ለራሱ ክብር አይኖረውም (በሚስጥረ አደራው)

ይህንን አባባል ስሰማ የምር ደንግጫለሁ። “የመጨረስን ጣዕም ካላወቅክ፤ ለራስህ ክርብ አይኖርህም” ። በዛው ቅጽበት ጀምሬ የጨረስኩት ምንድን ነው ብዬ እራሴን ጠየቅኩኝ? የጀመርኳቸው ብዙ ነገሮች በህሊናዬ መጡ፤ የጨረስኳቸው ነገሮች ግን..…

ነገርን ጀምሮ መጨረስ የሚሰጠው ስሜት ልዩ ነው። ብዙ ጊዜ ግልጽ የሆነ የጥፋተኝነት ስሜት የሚሰማን ለሌሎች የገባነውን ቃል ማክበር ሲሳነን ነው። የጥፋተኝነት ስሜት ብቻም ሳይሆን እራስን ወቀሳ ውስጥም እንገባለን። ሆኖም ግን ይህ ስሜት ማንነታችን ላይ የሚያደርሰው ጥፋት አናሳ ነው። ትልቁ ጥፋት የሚመነጨው ለራሳችን የገባነውን ቃል ማክበር ሲሳነን ነው። ለራሳችን የገባነንውን ቃል ማክበር ሲያቅተን፤ አፍ አውጥተን እራሳችንን መውቀስ ባንችል እንኳን ለራሳችን ያለንን እምነትና አመለካከት በእጅጉ ይጎዳዋል። አብዛኛውን ጊዜ ይህ የገዛ ቃል ኪዳንን ካለማክበር የሚመጣው የጥፋተኝነት ስሜት የሚያደርስብን ጥፋት በገሃድ የሚታይ አይደለም። ልክ እንደ ትንሽ የኮርኒስ ቀዳዳ በቀን በቀን የሚያስገባው ዝናብ እምብዛም አይረብሽም። ከብዙ ጊዜ በኋላ ግን ቀዳዳው ይሰፋና አይምሮዋችን ሳይወድ በግዱ የችግሩን መኖር እንዲቀበል ያስገድደዋል።

ናትናዬል ብራንደን የተባለው ሳይኮሎጂስት “በራስ መተማመን ማለት እኛ  ስለእራሳችን የገነባነው ስም ነው” ይላል። የገነባነው ስም ሲል፤ በስራችን፤ በውሳኔዎቻችን እና በአመለካከቶቻችን ለረጅም ጊዜ ያስመሰገብነውን  ውጤት ነው። መልካም ስም የሚገነባው ሰው እንደተጠበቀው  መጠን ሆኖ ሲገኝ ነው።  ለምሳሌ አንድ ሰው ሁሌ እመጣለሁ እያለ ቢቀርብን፤ ከግዜ በኋላ ለዚህ  ሰው “ቃለ-አባይ” የሚል ስም መስጠታችን አይቀርም። በተደጋጋሚ እመጣለሁ እያለ ከቀረ፤ ከጊዜ በኋላ እኛም ቀጠሮው ቦታ መገኘት እናቆማለን። ምክንያቱም፤ በድግግሞሽ ማንነቱን ስላስተዋወቀን።

“Self-Esteem is the reputation we acquire with ourselves”- Nathaniel Branden 

እኛም ላይ የሚፈጸመው ከዚህ የተለየ አይደለም። ነገሮችን አደርጋለሁ እያልን ባላደረግን ቁጥር፤ እራሳችን እየቀጠርን በቀረን ቁጥር ከጊዜ በኋላ እኛ ለእራችን የምንገባው ቃል ዋጋ ያጣል። እምነት ማለት ይደረግልኛል ብሎ መጽናት ማለት ነው። በራስ መተማመን ለእኔ እንደሚገባኝ፤ እኛ እራስችን ላይ ያለን እምነት ነው። ምን ያህል ለእራሳችን ቃል እንገዛለን? ማንም ሰው በቃሉ የሚቆምን ሰው ይውዳልም ያከብራልም። ለቃሉ የሚታመን ሰው የተከበረና የተመሰገነ ነው። እኛም ለእራሳችን የምንገባውን ትንሽም ሆነ ትልቅ ቃል ባከበርን ቁጥር፤ ለእራሳችን ያለን ፍቅርም ሆነ ክብር እየጨመረ ይመጣል።

አብዛኛውን ጊዜ ከሌሎች ጋር የምንጋጨው በቃላቸው አልተገኙም፤ በጠበቅናቸው ቦታ አልቆሙም ብለን ነው። እኛ በእራሳችን መደሰት ሲያቅተን፤ ምናልባት ያጠፍነው ቃል ይኖር ይሆን ብለን አስበን እናውቃለን? የሰው ልጅ ባህሪ ይደንቃል፤ እራሳችንን ከማስደሰት ይልቅ ሌሎችን ለማስደሰት የምንጥረውን ያህል፤ ሌሎች ላይ ከምናሳርፈው ወቀሳ በላይ እራሳችን ላይ የምናሳርፈው ወቀሳ ይበልጣል። ያላስተዋነው አንድ ነገር ቢኖር፤ ሌሎች በቃላቸው አልተገኙም ብለን ይህን ያህል ከተከፋን፤ እኛ ለገዛ እራሳችን ቃለ-አባይ ስንሆን ምን ያህል ቅያሜ ውስጥ እንገባለን? ብዙ ሰዎች ከሌሎች ሰዎች በላይ እራሳቸው ላይ የመጨከን አቅም አላቸው። የእርባና ቢስነት ስሜት የዚህ የጭካኔ  አንዱ ውጤት ነው። እስከመቼ ነው የምታለለው ብሎ አንድ ቀን ውስጣችን ተስፋ ይቆርጥብናል። ነገ እደርስልሃለሁ ብለን ብንሞግተው እንኳን፤ ከዚህ በፊት መቶ ጊዜ የገባነው ቃል ነበርና አይሰማንም። ሌሎችን በከንቱ የቃላት ድርደራ አስረን ማቆየት እንደማይቻል ሁሉ፤ እኛም እራሳችንን በቃል ብቻ ያለድርጊት ልናከርመው አይቻለንም። ሰው በእራሱ እምነት ሲያጣ ከራሱ ይሸሻል…

ለእኔ የደስታ ትልቁ ንጥረ ነገር ሰላም ነው፤ የአይምሮ ሰላም! የአይምሮ ሰላም ደግሞ የመንፈስና የስጋ፤ የፍላጎትና የድርጊት፤ የእውነታና የፍርድ ሚዛንን የመጠበቅ ሃላፊነት አለበት። ለውስጣችን ሰላም ማጣት ብዙ ምክንያቶች ሊደረደሩ ቢችሉም፤ ያለጥርጥር ቃልን ካለማክበር የሚመነጩት ምክንያቶች አብዛኛዎቹ ናቸው። አንዳንዴ የሆነ ነገር ለማድረግ አስባችሁ በደስታ ጫፍ ከደረሳችሁ በኋላ፤ ጥቂት ጊዜ እንዳለፈ የደስታው ስሜት በርዶ የአለመቻል ስሜት ወሮዋችሁ አያውቅም? እኔ እንደሚመስለኝ እንዲህ የሚሰማን፤ ውስጣችን ከዚህ በፊት ያጠፈነውን ቃል ሲያስታውስ ነው።

በውህደት ሃሳብ ውስጥ የሚመላለስ ሰው፤ እራሱን ሌሎች ውስጥ በቀላሉ ያያል። በሌሎች ስሜቶች ውስጥ የገዛ እራሱን ስሜት ስለሚያስተውል፤ ለሌሎች በሚያዝነበት መጠን ለእራሱም ያዝናል። ይህንን ያልኩበት ምክንያት፤ ለሌሎች ሰዎች የገባነውን ቃል ባለማከበራችን የሚደርሰው መጥፎ ስሜት፤ የእራሳችንን ቃል ስናጥፍ ከሚፈጠረው ስሜት ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ ነው። እንደውም ባይበልጥ። ስለዚህ ለእራስ የገቡትን ቃል ማጠፍ እንደ ቀላል ነገር የምንወስደው አይደለም። ጥፋቱ ከምናስበው በላይ ነው።

ከላይ እንዳሰፈርኩት ስለእራሳችን የሚኖረን እምነት፤ ፍቅርና ክብር፤ በቃል አክባሪነታችን መጠን ይወሰናል። ጀምረን የምንጨርሳቸው ማንኛቸውም ተግባሮች የእምንት ጡቦች ናቸው። ከጊዜ ብዛት በነዚህ ጡቦች የሚገነባው ግንብ እኛን ከእራስችንም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጥርጣሬ ይከላከለናል። የመጨረስን ጣዕም ካላወቅን እውነትም ለራሳችን ክብርና እምነት አይኖረንም። የሚገርመው ነገር፤ ይህንን ስሜት ለማምጣት ትልቅ ነገር ጀምረን መጨረስ አይጠበቅብን.…ማንኛቸውም ጅማሬዎች ፍጻሚያቸው ወደዚህ ስሜት ያደርሰናል። ዋናው ነገር ለእራሳችን የምንገባቸውን ማንኛቸውንም ቃል ኪዳኖች በቁም ነገር መውሰዳችን እንዲሁም ሁሉንም ጅማሬዎች ከፍጻሜ እንዲደርሱ መጣራችን ነው። ሁላችንም ቃሉን የማያከብር ሰው አናከብርም…የገዛ እራሳችንን ጨምሮ። ቃል ተቀብሎ የማይደረግለት ደግሞ እንደተካደ ይሰማዋል …የገዛ እራሳችንን ጨምሮ።

35 views0 comments
bottom of page