top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የሚያነበው ሳያለቅስ የማያነበው ለምን ያለቅሳል?(በሚስጥረ አደራው)


የሚያነበው ሳያለቅስ የማያነበው ለምን ያለቅሳል?(በሚስጥረ አደራው)

ጽሁፉን የሚያነበውና ታሪኩ የተጻፈለት ሰው ስለ አንድ ጽሁፍ እኩል ስሜት ሊኖራቸው አይችልም። ሰሞኑን አንድ ትምህርት ላይ ይህ ታሪክ ከጆሮዬ ዘለቀ። በአንድ ከተማ ውስጥ አንድ ብቸኛ ማንበብ የሚችል ሰው ነበረ። ይህ ሰው ከእርሱ ሌላ የሚያነብ ሰው በከተማው ባለመኖሩ ከፍተኛ ኩራት ይሰማው ነበር። ኩራት ብቻም ሳይሆን ደብዳቤ እንዲነበብላቸው ወደ እርሱ የሚመጡ ሰዎችን ይንቅ ነበር። ከእለታት አንድ ቀን አንድ ሰው ደብዳቤ ይላክለትና እንዲነበብለት ወደዚህ ሰው ብቅ ይላል። ሰውየው ደብዳቤውን በንቀት ከተቀበለው በኋላ ማንበብ ይጀምራል።

የጽሁፉ አጋማሽ ላይ ባለደብዳቤው ማለቀስ ጀመረ። ይሄኔ አንባቢው በብስጭት “በለቅሶህ አቋረጥከኝ” ብሎ ጮኸበት። ባለደብዳቤው ያለቀሰበት ምክንያት፤ ደብዳቤው የአባቱን ሞት ስለሚያረዳ ነበር። የአንባቢውን መቆጣት አይቶ ባለደብዳቤው እንዲህ ሲል መለሰለት “የምታነብልኝ ደብዳቤ የአባቴን ሞት የሚያረዳ ነው፤ ለዚህ ነው የማለቅሰው” አለው። ይሄኔ በትዕቢት የተወጠረው አንባቢ “ የማነበው እኮ እኔ ነኝ፤ አንተ ማንበብ አትችል? የሚያነበው ሳያለቅስ የሚነበብለት ለምን ያለቅሳል?” አለው። ምስኪኑም ሰው “የምታነበው አንተ ነህ፤ የሞተው ግን አባቴ ነው” ሲል መለሰለት።

ይህ ታሪክ ብዙ መልዕክት አለው። የሚያነቡ ብዙ ስዎች አሉ፤ የሚያነቡት ታሪክ ግን ከእነርሱ ህይወት ጋር ምንም ቁርኝት የለውም። በአንጻሩ እነርሱን የሚመለከት ጽሁፍ የተጻፈላቸው ማንበብ ግን የማይችሉ ብዙ ሰዎች አሉ። ሁለቱን ሰዎች የሚያጋራው ጽሁፉ ብቻ ስለሆነ አንዳቸው የአንዳቸውን ስሜት መረዳት አይችሉም። በንባብ ደረጃ ብዙዎቻችን ሊቅ ነን። ነገር ግን በምናነበው ነገር ውስጥ እኛን የሚመለከት ነገር ከሌለ ንባባችን ቃላት ከማለብለብ የዘለለ አይሆንም።

ሰዎች ስለ ሌሎች አላማ ይመክራሉ፤ ይናገራሉ፤ ይተቻሉ፤ አላማው ቢሞት የሚያለቅሰው ግን አላሚው ነው። ሰዎች ስለሌሎች እምነት ይወቅሳሉ፤ ይሞግታሉ፤ ይጋፋሉ፤ ከፈጣሪው ሲጣላ የሚያነባው ግን ባለ እምነቱ ነው። ሰዎች ስለሌሎች ህልም ትርጉም ይሰጣሉ፤ ፍቺ ያቀርባሉ፤ ይተነብያሉ፤ በህልሙ ውስጥ በቅዠት የሚታመሰው ግን ባለ ህልሙ ነው። ይህ ሰዎችን ለመውቀስ ያነሳሁት ነጥብ አይደለም። የሚያሳስበኝ እኛ ማንበብ ስለቻልን ብቻ የባለታሪኩን ስሜት ባለመረዳት ስሜታቸውን እንኳን እንዳይገልጹ መከልከላችን ነው።

ጠንቋይ አላማው የሌላውን ሰው እጣ ፋንታ መተንበይ ነው እንጂ፤ የሚተነበይለትን ሰው ስሜት መጠበቅ ላይ አይደለም። የጠንቋይ ገበያ የሚደራው የሰውን ስሜት በመጠበቅ ላይ ሳይሆን፤ የሚመስለውን በመናገር ላይ ብቻ ነው።እዚህ አለም ላይ የብዙዎቻች እውቀት የሚተገበረው በዚህ በጠንቋዩ መንገድ ነው። ስለሰው እንተነብያለን፤ የምንተነብየው ነገር ግን ለሚሰማው ሰው ምን ማለት እንደሆነ መረዳት አንችልም። የብዙ ሰዎችን ታሪክ ስናነብ፤ ማንበባችን ላይ ነው እንጂ በጽሁፉ ውስጥ ያሉት ገጸባህሪያት በእውነትም የሚነበብለት ሰው አካል መሆናቸውን አንረዳም።

ብዙ ታሪኮች እና ህልሞች ለንባብ አደባባይ ወጥተዋል። የሚያነቧቸው ባለታሪኮቹ አይደሉምና የሚሰነዘሩት አስተያየቶችና አመለካከቶች ከባለታሪኮቹ ስሜት ጋር የሚሄዱ አይደሉም። በምናነባቸው ታሪኮች ውስጥ ለባለታሪኩ ክብር እስካልሰጠን ድረስ፤ ንባባችን ከላይ እንደሰፈረው ትዕቢተኛ አንባቢ ስሜት አልባ ንባብ ይሆናል። ቁምነገራችን ማንበብ መቻላችን የሆነ ቀን፤ታሪኩን እንጂ ባለታሪኩን ማየት አንችልም። ታሪክ ያለ ባለታሪኩ ክብደት የለውም። ሰው ሁሉ ባለታሪክ ነው፤ ተንቀሳቃሽ መጽሃፍ። ታሪኩን ከሰውየው ስናወጣ ለትችትና ለወቀሳ ድፍረት እናገኛለን። ከምንም በላይ ሰዎችን ከታሪካቸው ስንነጥል፤ ደስታና ሃዘናቸው፤ አላማና ግባቸው፤ ህልምና ውጥናቸው፤ ተስፋና ፍርሃታቸው፤ ባጠቃላይ ስሜታቸውን በሙሉ ለመረዳት ይከብደናል። ልክ ከላይ እንደሰፈረው አንባቢ ማንበባቻን ላይ እንጂ ትኩረታችን፤ የባለታሪኩ ስሜት ላይ አይሆንም።

አለም ሁሌም በአንባቢውና በባለታሪኩ የተሞላች ናት። በሚኖረውና በአስተያየት ሰጭው፤ በባለህልሙና በህልም ፈችው፤ በአካሚውና በታካሚው መካከል የስሜት መጋራት መፍጠር ከባድ ነው። እንደው ታሪኩ እይታ ስለፈጠረብኝ የጻፍኩት እንጂ ምንም የመፍትሄ ሃሳብ የለኝም። እኔም እራሴ የችግሩ አካል ስለሆንኩኝ። እውነቱን ለመናገር ችግርም ላይሆን ይችላል፤ ግን ልብ ልንለው የሚገባን ሃሳብ ይመስለኛል። ቢያንስ የሌሎች ስሜት ላለመጉዳት እንድንጠነቅቅ ይረዳናል። በአንድ ወቅት አንድ ሰው የነገረኝ አባባል ትዝ አለኝ። ይህ ሰው ” there are a lot of things I don’t know, so I dwell in that a lot this days, you will be amazed by the power of “ I don’t know”” ብሎኝ ነበር። “ብዙ የማላውቃቸው ነገሮች አሉና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አይምሮዬ የሚያርፈው “አላውቅም” በሚለው ሃሳብ ላይ ነው። የአለማወቅ ሃይል በጣም ታላቅ ነው” ማለቱ ነበር። “አውቃለው” ከሚል ተራራ የሚወረወር ጦር ሁሌም የአንድ ሰውን አይን ይጎዳል።

እኔም ጽሁፌን የማጠናቅቀው በዚህ ነው፤ መፍትሄውን አላውቅም። እንደሚገባኝ ከሆነ ግን የምናየው፤ የምንሰማው፤ የምናንበው ታሪክ የሚነካን፤ እኛ ታሪኩ ውስጥ ባለን ድርሻ መጠን ብቻ ስለሆነ…ሁሌም ለአስተያየት፤ ለወቀሳና ለፍርድ ባንቸኩልና ባንደፍር መልካም ነው።

ሚስጥረ አደራው

48 views0 comments
bottom of page