top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የማይቆም ወንዝ ድንጋዩን ሰንጥቆ ያልፋል፤ በጉልበቱ ሳይሆን በጽናቱ!


የተፈጥሮ አድናቂ ከሆነን የወንዝን ውበት በህሊናችን ለመሳል ባልተቸገርን። ወንዝ ውብት ብቻም ሳይሆን ከሰው ልጅ ህይወት ጋርም ጥልቅ ግንኙነት አለው። ወንዝ የብዙ ስልጣኔዎች ምንጭ፤ የስነጽሁፎች መጠንሰሻ፤ የፍቅር መጎንጫ ሆኖ በየስነጽሁፉ ተከትቦ እናገኘዋለን። የሰው ልጅ ህይወት በወንዝ ተመስሎ ሲታይ የኑሮዋችን ፍሰት እንዴት እንደሆነ በሶስተኛ አይን ያስመለክተናል።

ስለወንዝ የተለያዩ ድንቅ አባባሎች ተነግረዋል። ለዛሬ መነቃቂያ የመረጥኩት “የማይቆም ወንዝ ድንጋዩን ሰንጥቆ ያልፋል” የሚልውን ነው። አስቡት ከድንጋይ እና ከውሃ የቱ ይጠነክራል? በውሃ የተቦረቦሩ ስንት የድንጋይ አለቶችን አይተናል? ውሃ በምን አቅሙ ድንጋይን ያህል ነገር በስቶ ያልፋል? እውነት ነው ውሃ ድንጋይን የመሰንጠቅ ሃይል አለው። ከድንጋዩ በርትቶ ወይም ከድንጋዩ በላይ ጉልበት ኖሮት ሳይሆን  ከድንጋዩ የበለጠ ጽናት ስላለው ብቻ ነው።

ህይወታችንም  ልከ እንደወንዝ ነው፤ በየመሃሉ የሚገጥሙን አለቶች እና ድንጋዩች ምንም እንኳን ሊታለፉ የማይችሉ ቢመስሉም ያለማቋረጥ ከተጋፈጥናቸው እና ጉዞዋችንን ካልገታን ግን እየተቦረቦሩ መንገድ ይከፍቱልናል። ብዙዏቻችን ግን የወንዙን  ያህል ጽናት የለንም  ፤ በትንሹም በትልቁም እንቅፋት ጉዞዋችንን እንገታለን። የስኬት ትልቁ ቁልፍ ያመንበትን ነገር ያለማቋረጥ መከወን ነው። ሁላችንም አላማ እና ግብ ሊኖረን ይችላል፤ ነገር ግን ጥቂቶች ብቻ ናቸው ግባቸውን አንግበው እረጅም መንገድ የሚጓዙት። እነሱም ጽናት ያላቸው ብርቱዎች ብቻ።

አብዛኛዎቻችን አንድ በር ሲዘጋብን ሁለተኛውን ለማንኳኳት እንፈራለን። በዚህ ምድር ላይ ያለተቃውሞ እና ውድቀት ያሰበበት ስፍራ የደረሰ አንድም ሰው የለም። አሁን ከፍ ብለው የምናያቸው ሰዎች ሲጀምሩ እንደሁላችንም ሰዎች ተራ ነበሩ። ዛሬ ብዙዎች የሚያጨበጭቡላቸው ሰዎች  ሀ ብለው ደረጃውን መውጣት ሲጀምሩ ከራሳቸው በቀር ያጨበጨበላቸው ሰው አልነበረም። አንድን ነገር ለመጀመር ትልቅ መሆን አይጠበቅብንም፤ ትልቅ ለመሆን ግን መጀመር መቻል ግዴታችን  ነው። የዛሬው ስራችን የብዙ ሰዎችን አይን አልሳበም ማለት የነገ ስራችንም እንደዛው ነው ማለት አይደለም። ህልማችን ለሌሎችም ሰዎች እንዲታያቸው መጠበቅ ትልቁ እንቅፋት ነው፤ አንዳንዴ የስኬትን ጎዳና ስትመርጥ ግብህ ለሌሎች አይታያቸውም። ሌሎችን ለማሳመን መጣሩ ጊዜህን እንዳያባክንብህ ተጠንቀቅ።

ከላይ እንዳልኩት ወንዝ ድንጋይን ያህል ነገር አልፎ መጓዝ የሚችለው ከድንጋዩ የበለጥ ጉልበት ኖሮት ሳይሆን፤ የማይበገር ጽናት ስላለው ነው። አዎ በመንገዳችን ብዙ አለቶች ይኖራሉ፤ ብዙ በሮች ይዘጉብናል ብዙ እንቅፋቶች ይፈጠራሉ። ምንም እንኳን የማይታለፉ ቢመስሉም፤ ተስፋ ባለመቁረጥ እና ጉዞን ባለማቆም የማይታለፍ ምንም እክል የለም።

ሌላ ጽናትን በተመለከተ የተረተ አንድ ተረት ላካፍላችሁ እና ጽሁፌን ልቋጭ። ሁለት ዝንቦች መውጫው ጠባብ የሆነ የወተት ጠርሙስ ውስጥ ይሰምጣሉ። አንደኛው ዝንብ ትንሽ ከተንፈራገጠ በኋላ መውጣት ሲያቅተው ተስፋ ቆርጦ ሰምጦ ሞተ።ሁለተኛው ዝንብ ግን ያለማቋረጥ ወተቱ ላይ ሲንፈራገጥ፤ ብዙ ከመንፈራገጡ የተነሳ ወተቱን ንጦ ወደቂቤነት ለወጠው። ቂቤው ላይ ቆሞም ከጠርሙሱ ለመወጣት ቻለ። ተረቱ ቀልድ ቢመስልም እወነታ አለው። ያለጽናት ስኬት የለም። ጽናት የሚፈተነው ደግሞ ምንም እንኳን የሚያበረታታን ብናጣም ጉዞዋችንን መቀጠል ስንችል ነው።

ያለጭብጨባ የሚጽፉ፤ ያለዝና የሚዘፍኑ፤ ያልደሞዝ የሚያገለግሉ፤ ያለሽልማት የሚለፉ ጽኑዏች ናቸው የነገ ስኬታማ ሰዎች። ዛሬ ያለንበት ቦታ የነገም ቦታችን ነው ማለት አይደለም፨ እናስታውስ አንድን ነገር ለመጀመር ትልቅ መሆን አይጠበቅብንም፤ ትልቅ ለመሆን ግን መጀመር መቻል ግዴታችን  ነው።


በሚስጥረ አደራው

85 views0 comments
bottom of page