top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

“የሰው ልጅ ከባዱን ጥላቻን ከተማረ፤ ቀላሉን ፍቅርንም መማር ይችላል…“ (በሚስጥረ አደራው)


“የሰው ልጅ  ከባዱን ጥላቻን ከተማረ፤ ቀላሉን ፍቅርንም መማር ይችላል…“ (በሚስጥረ አደራው)

መቼም አለማችን አሁን ያለችበት ደረጃ ከዚህ በፊት ደርሳ አታውቅም። በስልጣኔ በእውቀት እና በምርምር፤ ይህን ዘመን የሚያክለው ማን አለና? በተቃራኒው ደግሞ ፍቅር እና ሰላም ቦታቸውን እየለቀቁ በሁላችንም ህይወት ውስጥ ባዶ ስፍራ እያስቅሩ ሲሸሹ ይታያል። አለም የጠበበችን ያህል፤ ጦርነቱ እና ስቃዩ አንዳንዴ ዝም ብሎ ለሚያስተውለው ሰው ተስፋ ያስቆጥራል። ጥላቻን እንዲህ ከየት ለመድነው ያሰኛል፤ ሁላችንም የምድር እንግዶች ነን፤ ይዘነው የመጣንም ይዘነው የምንሄደውም ምንም ነገር የለም። ታዲያ ይሄ ሁሉ ግፊያና እና ግርግር ምንድን ነው?

እውነቱን ንገሪኝ ካላችሁኝ የምናደርጋቸውን ነገሮች ለምን እንደምናደርግ ብንጠይቅ፤ ለብዙ ነገሮች መልስ አናገኝም። ምክንያቱም ድርጊቶቻችን ከሰበብዓት የራቁ ስለሚሆኑ በቂ ምክንያት ለማግኘት ይቸግረናል። ከሰብዓዊነት የሚመነጩ ድርጊቶን ሲጀመር ለምን የሚል ጥያቄ አያስነሱም። ጥላቻችን፤ ግፋችን፤ በቀላችን ግን፤ ከተፈጥሮዋችን ውጪ እያደረገን ነው። ሰውነታችን ቀስ በቀስ እየደበዘዘ ነው፤ የብዙዎቻችን ነፍስ እየጠወለገች ነው፤ ማንም በጥላቻ እና በክፋት ያበበ እና ፍሬ ያፈራ ሰው የለምና።

እስቲ ሁላችንም ወደልጅነታችን ለደቂቃ በአይነ ህሊናችን እንመለስ፤ ከፍቅር በቀር፤ ከደስታ በቀር፤ ከሳቅ በቀር፤ ያለንን ከመካፈል በቀር፤ ምን በውስጣችን ነበር? ማንም ከበቀል ጋር አልተጸነሰም፤ ማንም ከጥላቻ ጋር እልተወለድም ። ልጅነታችን እውነተኛው ተፈጥሮዋችን የተንጸባረቀበት ዘመን ነው። እድሜያችን ሲጨምር ግን፤ በልጅነታች ቆሻሻ የነበረው ልብሳችን ጸድቶ፤ ንጹህ የነበረው ነፍሳችን አደፈች። በሰላም ያርፍ የነበረው ህሊናችን፤ ሰላሙን ነፈግነው።

ሞኝ አትበሉኝ እንጂ ሁሌ የማስበውን ነገር ልንገራችሁ። መሞታችንን ዘንግተነዋል……ዛሬ ወይም ነገ በማንኛውም ሰዓት ይህችንን አጉል የፎከርንባትን ምድር ልንሰናበታት እንደምንችል ጠፋን? መልካም ነገር ማድረግ ምን አልባት ለብዙዎቻችን ሊከብደን ይችላል፤ ግን ቢያስ ጥፋት ሳይሰሩ መሞት እንዴት ይከብደናል?

መልካም ለመስራት ሃይማኖተኛ መሆን አያስፈልገንም፤ ወይም መማር ወይም ልዪ መሆን አያስፈልገንም፤ ብቸኛው መመዛኛ ሰው መሆን ብቻ ነው። ሰው መሆን ብቻ!!! የነጻነት ታጋዩ ማርቲን ሉተር ኪንግ ደስ የሚል ንግግር ተናግሮ አልፏል “ጨለማን ጨለማ አያጠፋውም፤ ጨለማን ማጥፋት የሚችለው ብርሃን ብቻ ነው፤ ጥላቻንም ጥላቻ አያጠፋውም ጥላቻን ማጥፋት የሚችለው ፍቅር ብቻ ነው”

አብዛኛዎቻችን ጥላቻን በጥላቻ ለማጥፋት እንሞክራለን፤ የታሪክን ስህተት በበቀል ልናርመው እንጥራለን። ግን ያ ሞኝነት ነው፤ ማን ሲሳካለት አይተናል? ምን አልባት አንድ ሰው እንዲህ ቢያስብ ብዙሃኑ ካልተቀበለው ምን ዋጋ አለው ብለን ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ እንሰንፍ ይሆናል። ማህተመ ጋንዲ አንድ ሰው ነበር፤ ማርቲን ሉተር ኪንግ አንድ ሰው ነበር፤ ማንዴላ አንድ ሰው ነበር….አለምን ለመለወጥ ሳይሆን መጀመሪያ እራሳችንን ለመለመለውጥ እንሞክር።

ከታሪክ እንማር ጥላቻን በጥላቻ አናጠፍውም፤በፍጹም አያጠፋውም!!! የነጻነቱ ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ደስ የሚል ንግግር አላቸው

” ማንም ሰው ሌላውን ሰው በዘሩ እና በቆዳው ቀለም፤ ውይም በሃይማኖቱ እንዲጠላ ሆኖ አልተወለደም፤ ሰዎች መጥላትን ተምረውት ነው። የሰው ልጅ ጥላቻን ከተማረ፤ ፍቅርንም መማር ይችላል፤ እንደውም ፍቅር ለሰው ልጅ ተፈጥሮ ከጥላቻ ይልቅ ቅርብ ነው።”

ማናችንም ከዚህ ምድር ይዘነው የምንሄደው አንዲት ነገር የለም፤ ስለዚህ በጥላቻ ለምን ግዜያችንን እናጠፋለን፤ ይልቅ በፍቅር እና በስምምነት ብዙ ነገሮችን እንለውጥ። ጥላቻን ፈልገነውም ሆን ሳንፈልገው ተምረነው ይሆናል…….ፍቅርን መማር ግን ጥላቻን ከመማር በላይ ይቀላል እና ፊታችንን ወደ ፍቅር እንመልስ እላለው።


ሚስጥረ አደራው

49 views0 comments
bottom of page