top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

"የቅናትና ምቀኝት ትንታኔ ይዘት" (በሳዲቅ አህመድ ኡስማን)



(ውድ አንባብያን ይህ የሳዲቅ አህመድ ኡስማን ከዓመታት በፊት ከተሰሩት ቀደምት ስራዎች ውስጥ አንዱ ነው)


ቅናት ፡- ልሎች ያሉበትን የኑሮ ሁኔታ በመመልከት ልዩ የሆነ የክፋት ወይም የደግ ስሜት በህሊና ላይ መጫር ነው።


ጥሩ ቅናት ፡- ቅናት ያደረበት ግለሰብ ወይም ቡድን የሌላውን ስኬት በአርያነት በመከተል ሌላው ከደረሰበት ለመድረስ

እራሱን በተስፋ ሃይል አንፆ ጠንክሮ ይሰራና አላማን ከግብ ያደርሳል።


መጥፎ ቅናት፡- የማድረግ የብቃት ወኔ ይነሳና በስንኩል አስተሳሰብ ክፋትን ያስመነጫል በተጨማሪም ሌላውን ለመጉዳት ወይም በሌላው ላይ ለማሴር ይገፋፋል። ይህን መሰሉ ቅናት ደረጃው ያደገ ስለሆነ ምቀኝት ይባላል።


የምቀኝነት መንስሄና ሂደት

በኑሮ ውስጥ ያካበቱት እውቀት፣ መንፈሳዊና ግብረገባዊ ብቃት፣ ክብር፣ ዝና፣ አበይት የምቀኝነት መንስሄዎች ናቸው።


ምቀኝነት የሥነ-ልቡና ክስረት

ይህ እኩይ ምግባር የውስጥ ስሜትን በአያሌው ይወርስና ተመቅኚውን ግለሰብ ያሰቃየዋል፣ ያብከነክነዋል፣ ፊቱን እያኮሳተረ እና ደም ስሩ እየተገታተረ ሁለንተናው ይታወካል። የሚመቀኘው ግለሰብ ስለራሱ ማሰቡን ይቀንስና አእምሮውን በሌላ ሰው የለት ተለት ሁኔታ ይሞላል። አምራች (productive) ዜጋ መሆኑ ይቀንሳል:: በዚያም ሳቢያ የበታችነት ስሜት ይጠናወተዋል! በራስ መተማመን (Self Confidence) ያጣል፡፡

በራስ መተማመኑን እራሱ በራሱ ነፍጎ የበታችነት የተሰማው ግለሰብ (ቡድን) እራሱን በሞራል ለማጎልበትና ከሌሎች ለመድረስ ክፋት የተሞላበትን ውድድር ይተገብራል:: የዚህም ውድድር ባህሪ ምቀኝነት ይሆንና “ምቀኛ” ያስብላል።

ከላይ በተጠቀሰው ፍልሚያ ውስጥ ምቀኛው ይጨነቃል፣ ይደነግጣል እንዲሁም ይሰቃያል። ይህ… ስቃይ ሁለንተናውን ተቆጣጥሮ ለትካዜ ዳርጎ፣ ተስፋን ነፍጎ፣ በፍራቻና በሃዘን ያብሰለስላል። ደስታ ይጠፋል ተመቅኚው ይታመማል፣ ይከስራል፣ የበታች ይሆናል።

“ምቀኝነት ሰውን የሚጨርስ ተላላፊና ኃይለኛ በሽታ ቢሆንም ቅሉ ሌላ ሰውን የማይገድለው ከሁሉ አስቀድሞ ምቀኛውን ስለሚገለው ነው!”

የምቀኝነት አበይት ባህርያት

ጥላቻ (ባላንጣነት)፡-

ሌላ ግለሰብ፣ ቡድን፣ ማህበር፣ ብሄር፣ ዜጋ ወዘተ መልካምን እንዲያገኙ፣ እንዲሳካላቸው፣ እንዲያልፍላቸው፣ እንዲያድጉ፣ እንዲበለጽጉ፣ በእጅጉ ባለመፈለግ ውስጣዊ ቁርሾ ጭሮ የሌሎችን ጥላቻ በህሊና መፍጠር፡፡


የበላይነት ታላቅ ስሜት፡-

አለመሰልጠን በእጅጉ መፈለግ፤ በተቻለ መጠን በንግግርም፣ በተግባርም፣ በኑሮም ወዘተ የበላይ ለመሆን ብቻ መጣር፡፡ ሌሎች መልካምን ሲያገኙ በጥረት ሲበልጡ መከፋት፡፡


መገረም፣ መደንገጥ፣ ማመካኘት (Excuse)፡-

ሌሎች የተሻለ ሲያገኙ እንዴት? ብሎ መደንገጥ። በጥያቄና በመላምት መብሰልሰል፡፡ ለምሳሌ ሰርቆ ይሆናል፣ ሕገወጥ ሥራ እየሰራ ሊሆን ይችላል፣ ከባለፀጋ ተጠግቶ ቢሆንስ፣ ትምሀርቱን ኮርጆ አልፎ ቢሆንስ የሚል ምክንያቶች (Excuse) መደርደር።


ፍርሃት ስግብግበነት፡-

ሌሎች ካደጉና መልካምን ከተጎናፀፉ ለእኔ ምንም አይተርፍልኝም ብሎ በገና ገና መጨነቅ፣ በምድር ያለው ሲሳይ ፀጋ በሙሉ ያልቅ ይመስል በመፍራት፣ የስራ የእውቀት የእድገት ዘርፎች ሚስጢር በማድረግ መስገብገብ።


ሃይልና ክብር መሻት ፡-

በተቻለ መጠን ሌላውን በማንቋሸሽ እራስን ከፍ ከፍ ማድረግ። የሌሎችን ስኬት እንደ ተራ መመልከት፣ የበላዩንም የበታቹንም ለመናቅ መሞከር።


ክፍ ተግባርና ንፉግ ልብ ፡-

ሌሎች ደስተና ሲሆኑ ሰላም ሲኖራቸው አለመውደድ፣ ብጥብጥን መፍጠር፣ ሰዎች ሲበጣበጡ መደሰት፣ ከራስ በስተቀር አለም በመከራ በችግር ስትሆን አትኮሮት አለመቸር፣ እራስ ወዳድ ሆኖ ስለ እራስ ወዳድነት መስበክ።


ከተራ ባህርያት መቆራኘት፡-

ከሚገባው ባለይ ማፌዝ፣ ማጥላላት ልሎችን ማቃለል፣ የሚታወቀውንም የማይታወቀውንም ማማት፣ ተንኮልን ተመክቶ ግብዝ መሆን፣ በቀልድ፣ በፀብ፣ በእዩኝ እዩኝ እና በነገር ሌሎችን ማወክ።

አትኩሮት ለምቀኝነት

ምቀኛ ሁሌ የሚመለከተው የበላዩን ሳይሆን፣ የበላዩ የበታቹን የሚመቀኝበት መኖሩ አሌ የማይባል ነው። ለምሳሌ ሐብታም ድሃው እንዳያልፍለት፣ የተማረ ካለ ያልተማረው እንዳይማር፣ በሙያው ፕሮፍሽናል ካለ አማተሩ ፕሮፌሽናል እንዳይሆን ወዘተ…

የምቀኝነት አበይት ባህርያት በሚለው ለደካማ ንዑስ አርእስት ስር የተጠቀሱት ባህርያት በሰው ልጆች የኑሮ ሂደት የሚኖሩ መሆናቸው የማይካድ ሲሆን የባህርያቱ መብዛትና ማነስ የግለሰቡን ጥራት ስለሚወስኑት የሚችሉትን ያህል ከእራስዎ ላይ ቀርፈው ሊጥሏቸው ይጣሩ።

የዚህን ጥናታዊ ፅሁፍ መረጃ ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህ ምቀኝት የሚለው ጠንቅና በሽታ የተጠናወትዎ መስሎ ከተሰማዎ ልብ ይበሉና ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን አንኳር የመፍትሄ እርምጃዎችን ይተግብሩ።

ለምቀኝነት ከንቱ ስሜት የጥረት መድሃኒት

  • ቢመቀኙ በፍፅም ልላው እንዳያድ የማድረግ አቅም የለዎትም። ይህ ችሎታ የፈጣሪ ብቻ ነው። እርሶ የሚመቀኙት ሰው አምላክ በሰጠው ሲሳይ ሲደሰት እርሶ ለምን በጭንቀት ይብሰለሰላሉ?

  • ምቀኝነትን እራሶ በራሶ ይፃረሩት፣ ህሊናዎን ለጥሩ ሥነ-ምግባር ያነሳሱት። ህሊናዎ አንድን ሰው ለመጉዳት ካሰበ ለዚያ ግለሰብ መልካም ያድርጉለት፤ በዝናው ከቀኑ ያድንቁት። ምቀኝነት ግለሰቡን እንዲሸሹት ከገፋፋዎ ይቅረቡት ስለምን ካሉ “ልቦናዎ ድርጊትን ይከተላልና”፡፡

  • እራሶን በራሶ ያፅናኑ። እኔ ለግዜው የለኝም ይህ ግለሰብ ግን ያደገው በዕድሉ ወይም ያላሰለሰ ጥረት አድርጎ ወይም ከሁሉም በላይ አምላክ ረድቶት ነው እኔም ለወደፊቱ አገኛለሁ ይበሉ።

  • የማደግን ምስጢር ይገንዘቡ ለምሳሌ ሌላው በለጠኝ ካሉ ልምዱን እንዲካፍልዎት ይጠይቁት! ከጠየቁት ያውቃሉ። ከተመቀኙ ግን እራሶን ይጎዳሉ፡፡

  • እራስን አይዋሹ! “እራስን መዋሽት ከውሽቶች ሁሉ የከፋ ውሽት ነውና”። ለደካማ ጎኖ ምክንያት አይደርድሩ። “መታረም ሲቻል ማመካኘት (Excuse) ማብዛት የኋልዮሽ የሚያስኬድ ነውና”፡፡ ስህተቶትን አብጠርጥሮ የማወቅ ልምድን ያካብቱ፣ ስህተቶትን ይመኑ፣ የሚያርሞትንም ያመስግኑ፡፡

  • ምቀኝነቶ ይፋ ከወጣና ቅያሜ ከተፈጠረ ይቅርታን ይጠይቁ። ክፉ በደግ ይገራልና! ይቅርታን የማይጠይቅ አንደበት ዘለቄታዊ ሰላም ከህልውናው ጋር አብራ ልትገኝ (Coexis) ልታረግ አትችልም፡ ምቀኝነት ሰላምን ማጣት ስለሆነ ሰላምን በይቅርታ ማግኘት የሚቻል ከሆነ የይቅርታን ታላቅ ዋጋ ይገንዘቡ፡፡

  • ምቀኝነት የሚሉት በሽታ በጣም ጎጂ መሆኑን ይገንዘቡና ለውጥን ግዜ ሳያባክኑ ይጀምሩ! ለውጥ የብሩህ ተስፋ እሽት ነውና።

ልብ ያለው ልብ ይበል

ሳዲቅ አህመድ ኡስማን

117 views0 comments
bottom of page