top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ግምትና መላ ምት - ክፍል ሁለት (በኢዱና አህመድ ኡስማን)


eduna ahmed ousman
ግምትና መላ ምት - ክፍል ሁለት (በኢዱና አህመድ ኡስማን)

ግምትና መላ ምት በወዳጃሞች፣ በተጓዳኞችን፣ በቤተ ዘመድ፣ መሃል ቅራኔና ጥላቻን አንግሶ እሰከ መለያየት የተደረሰባቸው ክስተቶች በርካቶች ናቸው። በተጨማሪም ቅራኔና ጥላቻው ሰማይ ነክቶ የተጎዳዱና የተላለቁም እንደዚሁ በርካቶች ናቸው። በግምትና መላ ምት የሃሳብ መነሻነት የተሰሩና ሊሰሩ የሚችሉ በርካታ ክስተቶችና ጉዳዮች ቢኖሩም በእዚህ ጽሁፍ ለማጉላት የተሞከረው የግምት እና መላምት መጥፎ ጎኑን ብቻ ነው።

“ሌባ ፊት ለፊት የተቀመጠን አያይም” እንደሚባለው በሰው ልጅ የማህበራዊም ይሁን ግለሰባዊ ክስተቶች ውስጥ ፊት ለፊት ከተከሰቱት ጉዳዮች ይልቅ ምን ተከስቷል፣ ምን ሊከሰት ይችላል ወይም ሌላው ወገን ምን እያሰበ እንደሆን ለማወቅ በሚደረግ ከራስ ጋር ጸብ ውድ ጊዜና ሃይል ሲባክን ይስተዋላል። በአግባቡ ለተጠቀመበት “ጥርጣሬ በራሱ መልካም እና ጣፋጭ ነው”። ነገር ግን በመልካም ተጠራጥሮ መልካም የሰራ በምድርም ይሁን በሰማይ አትራፊ ሲሆን በመጥፎ የተነሳው ደግሞ ቁሳዊ እና መንፈሳዊ የምድር ኪሳራውን እንደ ሰው ዘር የማወቅ ሃይል ባይኖረንም የሰማዩን ኪሳራ በተመለከተ ግን በሁሉም መጽሃፎች ላይ በመጠቀሱ ሊከስር እንደሚችል ወይም የከሰረ ስለ መሆኑን ቅንጣት ያህል ጥርጣሬ አይኖረንም።

በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ሌላው ሰው የሚያስበውን እና ያሰበውን የማወቅ ሃይል የተቸረው የሰው ልጅ የለም። ነብያት ቢሆኑም እንኳን ከሃያሉ ፈጣሪ ከሚደረግላቸው እገዛ ውጪ የተለየ ሃይል አልነበራቸው። ታዲያ ይህ ምንን ያመለክታል የምናስበውና ከሰው እይታ ውጪ የምንፈጽማቸው ተግባራትን ከፈጣሪ በቀር ሊያውቅ የሚችል እንደሌለ ነው።

ከፍጡራኖች መካከል መላዕክት ከፈጣሪ በተቸራቸው ሃይል ከተፈጠርን ጀምሮ ያለውን በጎና እኩይ ተግባራችንን የሚከታተሉ ወይም የሚመዘግቡ አሉ። ሰይጣንና ግብር አበሮቹ ደግሞ ስጋ ለበስ ባለመሆናቸው ከሰው ልጅ በተለየ ሁኔታ ወይም በተለይ አቅም በሰው ልጅ የምድር ህይወት ወይም ኑሮ ውስጥ ቁርኝት አላቸው። ታዲያ እነዚሁ ሰይጣንና ግብር አበሮቹ የሰው ልጅ ከተፈጠረ ጀምሮ ባለው እንቅስቃሴ ውስጥ አብረውን የሚኖሩ ከመሆናቸው ባሻገር እንቅስቃሴያችንን የማወቅና የማየት እድል ሊኖራቸው ይችላል። ቢሆንም የሰው ልጅ ልክ በሃይማኖት አስተምሮት ላይ እንደተጠቀሰው እርኩስ መናፍሳትን ከእራሱ የማራቅ አቅም የተቸረው ቢሆንም በመጽሃፎቹ የተጠቀሰውን ያልተገበረው እርሱ ያለበት ቦታ ቢገኙም የሚያስበውን ግን የማወቅ አቅም ወይም ሃይል ይኖራቸዋል የሚል ግምት አይኖርም።

ወደ መደምደሚያ ስንመጣ ከፍጡራኖች መካከል ስጋ ለበሱ ሰው ከጎኑ ያለውን የሰው ልጅ ወይም ርቆ የሚገኝን የሰው ልጅ የሚያስበውን ወይም ከመጋረጃ በስተጀርባ ያለውን ሌላው የሰው ልጅ የሚፈጽማቸውን ተግባራት በራሱ ብቻ የማወቅ ሃይል የለውም። ከሰው ልጅ ውጪ ያሉት ሌሎች ፍጡራን ቢሆኑ እንኳን ከተፈጠሩበት አላማ ጋር ተዛማጅ ከሆነ እንቅስቃሴ ወይም ተግባር ውጪ የማወቅ ሃይል የላቸውም። ወዳጄ ሆይ… አንተ የተፈጠርክበት አላማ ሃያሉን ፈጣሪን ለመገዛት እና ለመገዛት ብቻ ነው። የሰው ልጅ የሚያስበውን እንዲሁም ተሸሽጎ የሚፈጽመውን ተግባራት ወይም ከስተት ያለ ምንም ግርዶሽ እና ክልከላ ሃይሉ ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው። ጎበዝ… ከእኩይ ግምት እና መላ ምት ርቀህ ህይወትህ የሰመረ ይሆን ዘንድ እምነትህን በፈጣሪህ ላይ በመጣል በሰላም እና በበጎ ተግባር ምራው። ለምን ቢባል የተሸሸገውን ወይም የማይታየውን የማወቅ ሃይል ወይም አቅም ላንተ አልተሰጠምና።

ግምትና መላ ምት ልክ ገደል አፋፍ ላይ እንደመቆም አይነት ማለት ነው። መልካም ግምትህ እና መላ ምትህ ግቡን የመታ ከሆነ ከስኬቱ ማማ ላይ የሚያፈናጥጥህ ሲሆን ግቡን ካልመታ ግን እጣ ፈንታህ ከገደሉ መፈጥፈጥ ነው የሚሆነው። በመልካም ለመልካም መጠራጠር ለሰው ልጅ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። በመልካም ለመልካም ተጠራጥሮ እራስን ከመጥፎ መጠበቅ እና በመልካም ለመልካም ተጠራጥሮ ቤሰተብንና ማህበረሰብን ከመጥፎና ከጉዳት መጠበቅ ደህና እና ሰላማዊ አካሄድ ነው።

ለአቅመ ሄዋን የደረሰች እንስት ከእኩለ ለሊት በዃላ ከእቤት ወጥታ ለብቻዋ በምታደርገው እንቅስቃሴ ምን ሊደርስባት ይችላል በሚል ግምትና መላ ምት ተጠቅሞ እርሷ ላይ ሊደርስባት ከሚችል ከመጥፎ ድርጊት መከላከሉ መልካም ሲሆን ለአቅመ ሄዋን የደረሰች ናትና ጉዳቱን ሊያደርስ የነበረው እከሌ ነው ወይም ከጎረቤት ያለው ነው ብሎ ማለቱ ደግ ያልሆነ ከራስ ጋር የሚደረግ ጸብ ነው። ከሁሉም የከፋና እብደት የሚሆነው ደግሞ “አንተ ነህ” ብለን ያለን እለት ነው። በእዚህ ምድር ላይ ፍረጃን ያህል የሚጎዳና የሚያስከፋ እንዲሁም መጥፎ ተግባር የለም።

የሰው ዘር ከተፈጠረ ጀምሮ የአዳምና የሄዋን ዘር አንድ አይነት ፍላጎት፣ አመለካከትና አካሄድ ያልነበራቸው ሲሆን ዛሬ ላይ ግን ከፋብሪካ በአንድ አይነት የተፈበረኩ በሚመስል አይነት እና ክፋት ወይም መጥፎ ሃሳብ ለሰው ልጅ የተቸረው ይመስል ከሊቅ እስከ ደቂቅ ደረጃው ቢለያይ እንጂ በግምትና መላ ምት ልክፍት ያልተለከፈ ወይም ያልታመመ የለም። ሁሉም በሚባል መልኩ ተጠቂ ቢሆኑም በተማረው እና አዋቂ ነኝ ብሎ እራሱን በቆለለው ይብሳል። አንዳንዴ ተማርኩ ብሎ ወረቀቶች የደረደረው በመገመቱ ወይም በመጠርጠሩ ብቻ የመማሩ ወይም የማወቁ ትልቁ ደረጃ እንደሆነ አድርጎ እራሱን ከፍ በማድረግ ያያል።

ይቀጥላል።


በኢዱና አህመድ ኡስማን

ሪያድ ሳኡዲ አረቢያ

92 views0 comments
bottom of page