top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ጭንቅት - ዘጠና በመቶው ቅዠት (በሚስጥረ አደራው)


ማን እንዳለው ባላውቅም ይህንን አባባል ከህይወት መመሪያዎቼ እንደ አንዱ አድርጌ ብወስደው እመኛለው። አባባሉ ይህ ነው “ህይወትን የምትወድ ከሆነ ጊዜህን አታባክን፤ ምክንያቱም ህይወት የተሰራችው ከጊዜ ነውና።” ይላል። እውነት ነው፤ ህይወት ከጊዜ ጡብ የሚገነባ ትልቅ ግንብ ማለት ነው። ጊዜውን የሚቆጥብ ሰው ትልቅ የህይወት ግንብ ለመገንባት የሚያስችለው ብዙ ጦቦች ይኖሩታል። ጊዜውን የማይጠቀም ሰው ግን ህይወቱን የሚገነባበት በቂ ጡብ ሳይኖረው፤ በጊዜያዊ ጎጆ ተጠልሎ ዘመኑን ይሳልፋል።

የጊዜን ዋጋ ብዙዎቻችን እስካላጣነው ድረስ አናውቀውም። ሲጀመር ጊዜ ብለን ስናስብ ፤ የአመታት ክምችት እንጂ ደቂቃ እና ቀናቶች የሚቆጠሩ አይመስለንም። ለዚህ ነው የጊዜ ኪሳራ ሲደርስብን፤ ሳናውቀው በትልቁ የምንከስረው። ለምሳሌ አንድ ሰው አንድ ኩንታል ጤፍ በጀርባው ተሸክሞ እረጅም ጉዞ እየተጓዘ ነው እንበል። ይህ ዘንቢል ከስሩ ትንሽ ቀዳዳ አለው። በዚህ ቀዳዳ በጣም አነስተኛ ጤፍ ይፈሳል። ይህ ሰው ምንም እንኳን ቀዳዳውን ቢያየውም፤ በዛች ቀዳዳ የሚፈሰው ጤፍ አይጎዳኝም በማለት ጉዞውን ይቀጥላል። እረጅም ከተጓዘ በኋላ ጀርባው እየቀለለ ሲመጣ ይታወቀዋል ፤ ምንም እንኳን ቀዳዳው ትንሽ ቢሆንም፤ ማፍሰሱን አያቆምምና። በስተመጨረሻ እረጅም ጉዞውን ሲጨርስ ምን አልባት ባዶ ቀረጢት ብቻ ተሸክሞ ሊደርስ ይችላል።

የጊዜም ነገር ከዚህ አይለይም፤ በየቀኑ የምናባክናቸው ደቂቃ እና ሰዓታቶች፤ ልክ በትንሹ የቀረጢት ቀዳዳ እንደሚፈሰው ጤፍ ናቸው። ትንሽ፤ ነገር ግን በጊዜ ብዛት ባዶ የሚያስቀር ኪሳራ። ብዙዎቻችን ጊዜያችንን የምናባክንበት የተለያዩ ምክንያቶች አሉን። አንድ ሁላችንንም የሚያጋራ እና ቀናችንን በሰመመን እንድናሳልፍ የሚያደርገን ዋነኛው ምክንያት ግን “ጭንቀት” ነው።

ኸርል ናይቲንጌይል ጭንቀትን በሚገባ እንዲህ ሲል ገልጾታል “ሰባት ከተሞችን የሚሸፍን ትነት( በየመስታወቱ ነጭ ሆኖ የሚታየው እንፋሎት)፤ ቢጠራቀም አንድ የብርጭቆ ውሃ አይሞላም፤ የሰው ልጅም ጭንቀት ከዚህ ጋር በጣም ይመሳሰላል።” ይህንን ያለበት ምክንያት የጭንቀትን እውነተኛ መልክ ለማየት እንድንችል በማሰብ ነው። ጭንቀት አብዛኛውን ጊዜ በውሸት ላይ የተመሰረተ፤ በምናልባት ውስጥ የተቀነባበረ ፈጠራ ነው። ብዙዎቻችን ጊዜያችንን የምናባክነው እና ዛሬያችንን ሳንኖርበት የምናሳልፈው፤ ገና ጊዜው ደርሶ እውን ያልሆነውን ነገር በምናባችን ለመሳል ስለምንሞክር ነው።

እርግጥ ነው እድሚያችን ሲጨምር ጭንቀታችንም እየቀነሰ ይመጣል። ምክንያቱም ያሳለፍነው የህይወት ልምድ፤ የተጨነቅንባቸው ነገሮች እውን ሳይሆኑ ሲቀሩ አልያም፤ ጭንቀታችን ለተራ ነገሮች የተገበረ ከንቱ መስዋትነት መሆኑ ስለሚያሳየን ነው። እራሳችንን ከጭንቀት ለማላቀቅ እና ዛሬን ለመኖር ግዴታ እስክናረጅ መጠበቅ የለብንም። አይምሮዋችንን በአግባቡ መጠቀም ከቻልን፤ ጭንቀታችንንም በትክክለኛው መነጸር ማየት እንችላለን። ጭንቀታችንን በትክክለኛው አይምሮ ስንዳኘው፤ ብርጭቆ እንዳማይሞላው ነገር ግን ዙሪያችንን መሸፈን እንደሚችለው ትነት (እንፋሎት) ይሆንብናል።

በጣም ያስገረመኝን እና አስተሳሰቤን ዞር እንዳደርግ ያስገደደኝ ሌላኛው መረጃ ይህ ነው። የሰዎችን ጭንቀት እንደ ኸር ናይቲንጌል አባባል በዚህ መልኩ ከፋፍሎ መረዳት ይቻላል።

-ጭራሽ እውን ላልሆኑ ነገሮች የምንጨነቀው የጭንቀት መጠን- 40 በመቶ

-ላለፉ እና ለውጥ ማምጣት ለማንችልባቸው ነገሮች የምንጨነቀው የጭንቀት መጠን- 30 በመቶ

-ስለጤንነታችን ያለአግባቡ የምንጨነቀው የጭንቀት መጠን- 12 በመቶ

-በረባው ባልረባው በሃዘኔታ የምንጨነቀው የጭንቀት መጠን- 10 በመቶ

-ተገቢ እና ትክክለኛ ጭንቀት- 8 በመቶ

እናም ከጭንቀታችን ሁሉ ዘጠና ሁለቱ በመቶ ለውጥ ለማናመጣባቸው ነገሮች የምንጨነቀው የጭንቀት መጠን ነው። ከላይ እንዳሰፈርኩት ህይወት የተሰራችው ከጊዜ ነው፤ ጊዜውን የማይወድ እና በአግባቡ የማይጠቀም ሰው ህይወቱን እየገንባ አይደለም። ጊዜ ደግሞ የሴኮንድ፤ የደቂቃ ፤ የሰዓታት እንዲሁም የቀናት ድምር ነው። በጭነቅት እና በሃዘን የምናሳልፋቸው ሰዓታት እና ቀናቶች፤ ከህይወታችን ግንብ እየፈረሱ የሚወድቁ ጡቦች ማለት ናቸው። ዘጠና በመቶውን የሚሸፍኑትን ያለአግባብ የምንጨነቅባቸውን ነገሮች ለይተን ማውቅ ከቻልን፤ ጊዜያችንን ምን ያህል በአግባቡ እንጠቀምበት ነበር። ከምንም በላይ በከንቱ የሚያልፉ ቀናቶች አይኖሩንም። ዛሬን መኖር ስንጀምር ደግሞ፤ ከደስታ ጋር ይበልጥ እንተዋወቃለን፤ ምክንያቱም ደስታ ከዛሬ እርቃ አታውቅምና።


40 views0 comments
bottom of page