የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

Aug 5, 20192 min

ንጉሥ መሆን! – ኤፍሬም ሥዩም

ንጉሥ መሆን! – ኤፍሬም ሥዩም

ምናልባት…
 

 
ከቤተ መንግስቱ በአፋ – ከዙፋኑ እግር
 
ድንኳን ጥሎ ለሚኖር – ከሜዳ ላይ ወድቆ ለሚያድር
 
የለት ስቃዩን – የማግኘት ርሃቡን
 
የማጣት እርካታውን – የድህነት ቀንበሩን
 
የጉስቅልናውን ስንክሳር – ንጉስ ይፈታል ብሎ ለሚያስብ
 
ለአንድ ትንሽ ምስኪን የድሃ ልብ፤
 
ንጉስ መሆን – ቀላል ነው
 
ያለ ጭንቅ ፣ ያለ ሃሳብ – በድሎት መኖር ነው።
 

 
ንጉስ መሆን ግን ይከብዳል …
 
ምናልባት ለመንገስ – መጋደል ይቀላል።
 
በአንድ ወቅት ንጉሱ …
 
ከንግስናው በፊት – የድሃ ልጅ ነበር
 
ምስኪን ብላቴና – ተጨቁኖ የሚኖር
 
የፍርድን መጓደል:
 
የድሃን መበደል፡
 
ይህን ሁሉ ያውቃል፤
 
ንጉስ መሆን ደግሞ…
 
እውቀትን ያስንቃል፤
 
ከሜዳ ላይ ወድቆ – መኖርን ያስመኛል።
 

ሌላው…
 
ከጠረፍ ላይ ሰፍሮ፡
 
ሚስት ልጁን ሩቅ ጥሎ፤
 
የርስቱን ድንበር … ወጥቶ ለሚጠብቅ፡
 
ላንድ ምስኪን ወጥቶአደር (ወታደር)፤
 
ንጉስ መሆን ምንም ነው፡
 
ተራ ትንሽ ቀላል ነገር፡
 
ፀሃይ ተከልሎ … በጥጋብ መሳከር።
 

 
ንጉስ መሆን ግን ይከብዳል፤
 
ምናልባት ለመንገስ – መጋደል ይቀላል።
 
ምክንያቱም ያ ንጉስ …
 
ከዘመናት በፊት – ድንበሩን ጠባቂ … በራሱ ጭፍራ ነው፤
 
ወይም
 
ያንድ ወታደር … የአብራኩ ክፋይ ነው።
 
ስለ ሀገር ፍቅር
 
ስለ ድንበር ክብር
 
ጥይት መታኮስም የሚቀለው ነበር።

ንጉስ ሲሆኑ ግን … ነገር ሁሉ ይለወጣል፤
 
የንጉስን ጭፍራ መሆንን ያስመኛል።
 
ምናልባት …
 
የሰማይን በረከት በመጠበቅ …
 
በውሃ እጦት ለሚሳቀቅ…
 
ላንድ ምስኪን አርሶአደር – ማዳበሪያ ላስጨነቀው፤
 
ማዳበሪያ ማግኘት ማለት…
 
በንጉሱ ፈቃድ … በቀጭን ትዕዛዝ … መምጣት የሚችል ነው።
 

የዛች ድሃ አገር … ንጉስ ገዢያቸው ግን፡
 
ስለ ገበሬዎች መፈክር አንስቷል
 
በስማቸው ምሏል
 
ራሱንም ሰጥቶ በብዙ ተጋድሏል።
 
ንጉስ ሲሆኑ ግን – ይህ ሁሉ ይቀራል
 
መሃላው በተራ – ከጉሮሮ ያንቃል
 
ጠልቶ የጣሉትን – ይቅርታ ያስብላል።
 
ለምን?
 
ከመንገስ … መጋደል … እጅጉን ይቀላል።
 

 
ሌላው …
 
ንጉስነትን ፈልጎ – ንጉሱን ለሚተች
 
አውቅልሃለሁ ለሚል – ለድሃ ተሟጋች
 
ንጉስ ይሁን እንጂ…
 
ለሁሉም ነገሮች – መፍትሔው ቀላል ነው
 
ንጉስ መሆን ነው የችግሮች መፍችያው።
 

 
የድንበር መከበር…
 
የገበሬው ችግር …
 
የፍርድ መጓደል …
 
የድሆች መበደል …
 
ባገሪቷ ያለው የስቃይ ስንክሳር…
 
መፈታት ይችላል – ባንዲት ምሽት ጀምበር።
 
ንጉስ ሲሆኑ ግን – ይህ ሁሉ ይጨንቃል፤
 
የንግስናው ዙፋን – ላፍ ዳገት ይሆናል።

    240
    0