የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ
Oct 5, 20191 min
105. ቋንቋቸው ተብታባ ዲናቸው እስላም ነው
አገራቸው ቆላ ልብሳቸው ግልድም ነው
ጦራቸው ክፉ ነው አፈር የሚያስቅም
እኒህ ለሐበሻ መርዝ ናቸው ሹ(ስ)ም?
ከኒህ ጋር መጣላት የለውም ጥቅም::
106. በአሥመራ ወያኔ ከመጣ ችግር
መጀመሪያ አሥመራ ትሆናለች ቀብር
አክሱም ትጠፋለች በአንድ ቀን ጀንበር
ግሼን ላሊበላ ትሆናለች ቀብር
ሁሉም ይሸፍታል ሴት እናኳን ሳይቀር::
107. ስንት እጃኢብ ያያል በዱኒያ የቆየ?
እኛ ባንደርስበት የልጅ ልጅ ጉድ አየ
ጥበብ እንዳይለምድ አሻቅቦ እያየ
የነጮችን ሥራ ብልግናን ገበየ
(አባቷም ዝም አለ ፈርጇን እያየ)::
108. የሳዳቶች ቀለብ ቀንበጥ ሳትረክስ
አላፊው ሳይቅማት ሳትበሰብስ
ትንባሆ ሳይቅማት ተሸጣ ሳትረክስ
ተው አታበላሻት ወንድሜ እየቃምክ አልቅስ
አላህ እንዲያለብስህ ሸማና ቀሚስ::
109. ይሰማኝ እንደሆን ፉቅራን ልምከረው
ለሴት ጫት መቃሙን መትፋቱን ይተው
መብራት አጥፉ እያለ ሰው እንዳያየው
እኔም ዝም አልልም ዲኑን ሲያረክሰው
እንኳን አላህ ጠልቶት ደስ አይልም ለሰው::
110. ብዙ ጉድ አየሁኝ መጅሊስ ተጠርቼ
ቱፍታ ልትመታ ጅስሟን ገልጣ አይቼ
ጸጉሯንና ጡቷን ሲይዟት አይቼ
እራቅ ብዬ ቃምኩኝ እንዳልነካት በእጄ
ሰው ነገረኛ ነው ሐሜቱን ፈርቼ::
111. ጠጅ ጠጣ ይለኛል ሲሩን ሳያውቀው
እኔ ለጠጣሁት ምን ቅናት ያዘው
አላህ ሲይስተው እንጅ ለሰው ብዬ አልተው
ንገሩት ቃልቻን ኋላ እንዳያመው
እንደ መምሬ ጉርሙ ሳላበላሸው::
112. አምስት ወቅት ሶላት ስገድ ብንለው
መርቅኛለሁ አለኝ እዩት ይህን ሰው
ጫቱን ዋጀብ አርጎ ዲኑን ሊያጠፋው
ጫቱን እየበላ ቢሰግድ ምነው?
እኔም ዝም አልልም ዲኑን ሲያረክሰው::
113. ሶላት ካልሰገደ አብሮኝ እንዳይቅም
ሐድራ ያበላሻል የለውም ጥቅም
አይሰግድም ከመባል ሞት አይሻልም
አላህ አይለቀውም እስከ ዘለዓላም
ነገሬ ካልገባው ይጠይቅ ዓሊም::
114. የመተማን ትተን የሐውሳን እናውጋ
ሦስት ቀን ጨልሞ በአራተኛው ነጋ
ለዕለት ታግሎ ነበር ሐውሳ እንዳይወጋ
ስሙ የታወቀ ትልቅ ባለጸጋ
ሳይያዝ ያመልጣል ሐውሳ ግን ተወጋ::
115. ነገሩ እማይገባ የተወላገደ
በአሥመራ በትግሬ ሄዶ እየነደደ
እንዴት ያለ እሳት ከሸዋ ነደደ
ቢያጠፉት እምቢ አለ እየተዛመደ::
116. አንበሳ እግሩን ታሞ ደም ሲያለቃቅስ
ማማው ምስጥ በልቶት ይሆናል ብስብስ
ወደቅ ወደቅ ይላል ወፉን ሊያጨርስ
የዚያን ቀን አሳማ ይሆናል ንጉሥ
ሺምጦ የሚበላ ሰው የሚያስለቅስ::