የመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

Dec 17, 20191 min

የሼህ ሁሴን ጅብሪል ግጥሞች (ክፍል - 16)

128. ዘመን ተበላሽቶ ወደቅ ወደቅ ሲል

ነጭ ከባሕር መጥቶ ይስላሉ ሲል

ተፈሪ የዚያን ቀን ይሆናል ትል

ሜዳ ላይ ይወድቃል ሳያገኝ ጅልል::

129. አላህን ሰደብኩት ማን አለው ጠበቃ

ምን ሥፍራ ኖሮት ነው ለራሱ የሚበቃ

በዱኒያ እንደሆነ ይበልጣል የእኔ ዕቃ

ቃልቻ ይመስክር አላህ ካለው ዕቃ::

137. አውራ በሬ ታርዶ አንበሳ ሲያለቅስ

ሐበሻ የዚያን ቀን ትሆናለች ኩስ

ሽታዋ የሚያስከፋ የምታስነጥስ

የዚያን ዕለት ይወድቃል እስላምና ቄስ

የዚያን ቀን ያስፈራል አገር እንዳይፈርስ::

138. እኛ አፈር በገባን በአንድ መቶ ዓመት

ተፈሪ ዓይኑን ታሞ ይገባል መሬት

ማር የላሰ ሁሉ ይቀምሳል እሬት

የበላውም አይቀር ሽቅብ ሲያስተፉት

ካለው ይገድሉታል ለገዘብ ስስት::

139. ሸዋ እባቡን ሳይዝ ምስጢሩን በዝብዞ

ድርቡሽ አገር ገባ የሰውን ላብ ይዞ

እባብ ልቡ አይገኝ መጣ መርዙን ይዞ

ዓለሙ ላይ ተፋው ያገሩን ጅብ ሰዶ

አብሮ የሚበላ አንጀትን በዝብዞ::

140. ሷሊህና ቃሲም አብደላህና ዙበኗር

በወልቃይት ብቅ አሉ ትግሬ ሲበረበር

ኩታበር ገራዶ ትሆናለች ጠጠር

ጎጃም ትጠፋለች ሳትውል ሳታድር

ብዙ ሰው ይጠፋል ያውም ከባላገር::

141. አሥመራ ተወግቶ ወልቃይት መርዙን ተፋ

ሽሬና መቀሌ ይሆናል የከፋ

እንቅልፍ እንዳይወስድህ እርብ ሳይጠፋ

ይመስላል ላየው ሰው ቂያማ የተደፋ

እርብ ስንቱን ጣለው ጠብቆ ወረፋ::

142. ጋይንት ንፋስ መውጫ ድራና ፎገራ

እርብ ላይ ሞልቶ ሲዘፍን ሲያጎራ

ነጋዴው ይጮሃል መቀሌና አሥመራ

ምን ይበጀው ይሆን ጅልጋና ፎገራ?

ሸዋ ደፈረሰ እህሊን ሳይዘራ::

143. መግዛቱን ይገዛል የዮሐንስ ዘር

ወዲያው ለጥቂት ቀን ይላል ፈንጨርጨር

ተፈሪን ጥላ አርጎ ሲያሳድድ ሲቀብር

ቢያዝ ደግ ነበር አገሩን ሳይቀብር

በቀር ሸዋ አይረጋም አትጠራጠር::

144. ሐበሻ ተፈሪን ይዘው ከቀበሩ

አሥመራ በሞላ ይታጠራል በሩ

መቼም ላስተዋለው ብዙ ነው ነገሩ

እኔ እገሌ አልልም ብዙ ነው ምሥጢሩ

በጫካ አካባቢ መች ቀረ ነገሩ::

    380
    1