የመስቃን ቤተ ጉራጌ ታሪካዊ አመጣጥ
በአምባሳደር ድንበሩ አለሙ (ጎጎት ከሚለው መፅሃፍ የተወሰደ
በመጀመሪያ ስለ መስቃን ህዘብ ታሪካዊ አመጣጥ ከመመልከታችን በፊት ስለ ህዝቡ አሰፋፈርና ስለ አካባቢው መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ ማወቅ አስፈላጊ ነው። የመስቃን ህዝብ በጉራጌ ዞን ከሚገኙ አስራ አንድ ወረዳዎች መካከል አንዱ በሆነው በመስቃን ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን የሚዋሰነውም በሰሜን ሶዶ በደቡብ ስልጤ በምእራብ ሰባት ቤት ጉራጌና በምስራቅ ከማረቆ ጋር ነው።
የመስቃን ህዝብ ካለው የህዘብ ብዛትና ከሰፈረበት ይዞታ አኳያ የወረዳው መጠሪያ ስም ለመሆን የቻለ ሲሆን ህዝቡ ተራራማ ከሆነው የመስቃን ደጋና ወይና ደጋ ክፍል አንስቶ የወረዳው ርእሰ ከተማ የሆነችው ቡታጅራን ጨምሮ እስከ ቆላማው የወረዳው ድንበር ድረስ ሰፍሮ ይገኛል። በተጨማሪም የመስቃን ቤተ ጉራጌ አባላት በአጎራባች ወረዳዎችና በደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በከንባታ አለባ ጠንባሮ በሲዳማና በጌዲኦ ዞኖች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል በመቂ አከባቢና በሃገሪቷ በሆነችው በአዲስ አበባ ከተማ ውስት ተሰራጭተው ኑሮአቸውን መስርተው የገኛሉ።
የመስቃን ቤተ ጉራጌ አመጣጥ
የመስቃን ህዝብ ታሪካዊ አመጣጥን በተመለከተ እስከዛሬ ድረስ በሃገር ውስጥም ሆነ በውጪ ሃገር የታሪክ ምሁራን በኩል የተካሄደ ጥናት ካለመኖሩ ባሻገር የጉራጌን ህዝብ ታሪክ ለመጻፍ የተነሱ የታሪክ ምሁራን ባሰባሰቧቸው የታሪክ መዘክሮች የጻፉት ነገር ቢኖር በጣም አናሳ በሆነ ሁኔታ የጉራጌ ብሄረሰብ አካል መሆኑንና የጉራጌ ብሄረሰብ የዘር ግንድ ከሆኑት ሰዎች ጋር ወደ ዛሬው የጉራጌ ምድር መምጣታቸውን የሚጠቁም መጠነኛ ፍንጭ የሚሰጥ ሆኖ እናገኘዋለን።
በዚህ ምክንያት የህዘቡን ማንነት የሚገልጽ ጥናት ባለመካሄዱ በተጨማሪም ወደ ሰነድነት የተሸጋገረ የቆየ ታሪኩን የሚዘግብ ጽሁፍ ባለመኖሩ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ስለህዝቡ ታሪክ ባህልና ገድል በቂ ግንዛቤ ለመጨበጥ የተቸገረ መሆኑ አሌ የማይባል ሀቅ ነው። ሆኖም ባንድ ታሪክ ወቅት የሚገኝ ህብረተሰብ በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ ይሁን እንጂ የትኛውም ህዝብ የራሱ የሆነ ታሪክ ባህልና ቋንቋ ያለው ስለመሆኑ የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይሆንም ።
በመሆኑም ከዚህ መሰረታዊ ጉዳይ በመነሳት የመስቃን ህዝብ የማንነት መግለጫ የሆነው ታሪኩና ባህሉን ለማጥናት ከላይ በተገለጸው ነባራዊ ሁኔታ አስቸጋሪ ቢሆንም ባሁኑ ጊዜ በህይወት ያሉ የማህበረሰቡ ተወላጆ የሆኑ አዛውንቶች ባፈ ታሪከ የሚናገሩትን መረጃ በማሰባሰብና አንዳንድ መጽሃፍቶች ስለ መስቃን ህዘብ ከሚሰጡት መጠነኛ ፍንጭ ጋር በተገናዘበ መልኩ የተሟላ ባይሆንም መጠነኛ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ የመስቃን ህዝብ የረጅም ዘመን ታሪክን ከዚህ ቀጥሎ ለማየት እንሞክራለን።
በመጀመሪያ ደረጃ የመስቃን ህዝብ መስቃን የሚለው መጠሪያ ስያሜ ያገኘው በመካከለኛው ዘመን መባቻ ላይ ቢዳራ በሚባለው ቀበሌ ተገንብቶ የነበረውና በሗላም በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ባህመድ ግራኝ የፈረሰው መስቀለ እየሱስ ከሚባለው ቤተክርስቲያን ስም የተወሰደ ለመሆኑ የመስክ ጉብኝት በተደረገበት ወቅት ለጥናቱ ተባባሪ የሆኑ አዛውንቶች ገልጸዋል። በተጨማሪም ስሙንት(ስምንት) ሰንጋ መስቃን በመባል የሚታወቁት አከባቢዎች ደግሞ የጠቀር፣ ሚካኢሎ፣ ውሪብ፣ አቦራት፣ እም (እናት) መስቃን ፣ እምቦር (ፈረዝአገኝ) ፣ የተቦን እና ጎይባን ናቸው።
ወደ ተነሳንበት ርእሰ ጉዳይ ስንመለስ የዛሬው የመስቃን ህዝብ በተሰበሰበው መረጃ መሰረት በስሩ 62 (ስልሳ ሁለት) ጎሳዎችን ያቀፈ ነው።
የእነዚህ ጎሳዎች ታሪካዊ አመጣጥን ስንመለከት በተለያየ ወቅት ከተለያ አቅጣጫ በተለያ ምክንያት የመጡ ሲሆን ከነባርና ቀድመው ከመጡ ጎሳዎች ጋር በስምምነትና በግጭት እየተቀለቀሉ እየተዋሃዱ በረጅም ጊዜ የታሪክ ሂደት የዛሬውን የመስቃን ቤተ ጉራጌ በመባል የሚታወቀውን ህዝብ ለመመስረት ችሏል።
1. እናት መስቃን
-
ቦንጂ
-
አልወድሽ
-
ማሬኖ
-
ወሬቦ
-
ድላባ
-
ሊላቶ
-
ሰጦ
-
ፋጌ
-
ተራሞ
-
በጋሞ
-
ሰቡቴ
-
አውራሪ
-
ጅገና
2. እምቦር
-
ስናኖ
-
ኦዳ
-
ኢንዴ
-
ቃሶ
-
ኤሉ
3. ዲራማ
-
ሞንኢሎ
4. ፈረዝአገኝ
-
ሱሚየ
-
ንቡወ
-
ጋሎ
5. ግዴይ
-
ዋተራ
-
ገሬኖ
-
ጃርሶ
6. ውሪብ
-
ቸሮ
-
ሱነከሌ
-
ቦሰኖ
-
ጎዳና
-
ገሬኖ
-
ጃርሶ
7. ሚካኢሎ
-
ሚካኢሎ
8. የጠቀር
-
አረቢዳስ
-
ጃተኒ
-
ቅምቦት
-
ወጎ
-
ከሳዬ
9. የተቦን
-
ዳረጎት
-
አስፎ
-
ገድፍ
-
አማኖ
-
ወሶ
-
ግድርወ
-
ራያ
-
ዋቆ
-
ኤቤኝ
-
መንደል
-
ጅርመከር
10. ጐይባን
-
ሸዋ
-
ጨዋ
-
አትርዱ
-
ወይንጉስ
-
ወልዶ
-
ሁልየ
-
አርቦ
-
ደዋዲን
-
ዳሞ
-
ሼህ መረዲን(ማሬኖ)
-
ባሮ
-
ጉምባር