top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

በበላህ ገብር... በሰማህ መስክር!

Updated: Apr 18


ከእለታት አንድ ቀን፤ በአንድ የተንጣለለ መስክ ላይ አንዲት  በግ ከነግልገሏ ሳር በመጋጥ ላይ ሳሉ፤ አንድ ግዙፍ ንስር-አሞራ በሰማይ እያንዣበበ፣ በተራበና በጎመዠ ስሜት፣ ከአሁን አሁን ወርጄ ልብላ እያለ ግዳይ - ሊጥል ያስብ ጀመር፡፡ጅው ብሎ በመውረድ ሊውጥ - ሊሰለቅጥ በሚልባት  የመጨረሻ ቅፅበት ላይ፤ ድንገት አንድ ሌላ የሱው ብጤ ግዙፍ ንስር መጣ፡፡

 በበጊቱና ግልገሏ አናት ላይም በስግብግብ ስሜት ያንዣብብ ገባ፡፡ ክፉኛ ቋምጧል፡፡ ሁለቱ አዳኝ ንስሮች ግዳይ ሊጥሉ  ባሰቡት  ምግብ ሳቢያ፣ ክንፋቸውን እያራገቡ ፍልሚያ ገጠሙ፡፡ ተቋሰሉ፡፡ ተዳሙ፡፡ አየሩ በንስር አሞሮች  ጩኸት ተሞላ፡፡ ሰማዩ  ታወከ፡፡ ይሄኔ በጊቱ ቀና ብላ ወደ ንስሮቹ ንፍቀ-ክበብ አስተዋለች፡፡ በተፈጠረው ሁኔታም እጅግ በመገረም ወደ ግልገሊቱ ዞራ፤ “አይገርምሽም ልጄ ሆይ? ከበቂያቸው በላይ የሆነ ይህን የሚያህል ሰፊ አድማሰ ሰማይና ህዋ ተንጣሎላቸው ሳለ፤ ሰማይና ህዋ ተንጣሎላቸው ሳለ፤ እኒህን መሳይ የተከበሩ ትላልቅ ወፎች እርስ በእርስ ሲናቆሩና ጦርነት ሲገጥሙ ሲታዩ አይገርምሽም?ፀልይላቸው ልጄ ሆይ! ከልብሽ ፀልይላቸው! ፈጣሪ ለእነዚህ ክንፋም ወንድሞችሽ ሰላም ያውርድላቸው ዘንድ ፀልይ!” ግልገሊቱም ከልቧ ፀለየች፡፡

ካህሊል ጂብራን ከፃፋቸው ተረቶች መካከል አንዱ ነው፡፡


***

ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ አሳሳቢ ነው፡፡የትግራይን ጦርነት ከስንት የህይወት መስዋዕትነት፣ የሥነልቡና ጉዳትና የሞራልና ኢኮኖሚ ድቀት በኋላ እንደምንም ተወጣነው  ስንል፣በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች አዲስ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ይፈራረቁብናል፡፡ ግጭቱና አለመረጋጋቱ ጋብ አለልን ስንል፣ 

ረሃቡና ድርቁ ይከሰትብናል፡፡


ረሃቡንና ድርቁን በመከራ ተሻገርነው ስንል፤ ዓይኑን ያፈጠጠ ሙስና ከራስጌ እስከ ግርጌ እንደ አራሙቻ ይወርረናል፡፡ ስለዚህም  እንፀልያለን! ከሙስናው ለመገላገል መመሪያ ሲወጣ፣ መመሪያው ራሱ ሙስና የተጠናወተው ሆኖ ይገኛል፡፡እቅዶች ይነደፋሉ፤ አይተገበሩም፡፡ ህግጋት ይደነገጋሉ፤ አይከበሩም፡፡ የህዝብ መብት ተንቋል፡፡ ፍትህ ቦታ ካጣ ሰንብቷል፡፡መመሪያዎች ይወጣሉ፡፡ መሪም፤ ተመሪም አያገኙም፡፡ይህን ሁኔታ ከአናት ለመቆጣጠር፣ ከወገቡ ለማጥበቅም ሆነ ከግርጌው አጭዶ ለማስተካከልና ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት  ከቶም አዳጋች የሆነ ይመስላል፡፡ ጉዳዩ ከ Policy in Crisis ወደ Crisis in policy ዘቅጧል፡፡(የችግር ጊዜ መመሪያ ከመሆን ወደ የመመሪያ ችግርነት ተለወጠ እንደ ማለት) አሊያም “ከድህነት ፍልስፍና ወደ ፍልስፍና  ድህነት” መዝቀጥ መሆኑ ነው፡፡ የስርዓተ-አልበኝነት መፈጠር ዓይነተኛው ስጋት ይሄኔ አንገቱን ብቅ ያደርጋል፡፡


ለዚህም እንፀልያለን! ሁኔታው ሁሉ ዛሬም መልስን Who guards the guards (ጠባቂዎቹንስ ማን ይጠብቃቸው፣ ተቆጣጣሪዎቹንስ ማን ይቆጣጠራቸው) እንድንል ይገፋፋናል፡፡ ለምድር ለሰማይ የከበደ ፍፁማዊ - ሥልጣን፣ ሙሉ ለሙሉ የሚያነቅዝ ሙስናን ይጋብዛል (Absolute Power corrupts absolutely) የሚባለው በዋዛ አይደለም፡፡ ሙስና፤  መሪዎች መካሪ ሲያጡ፣ አልሰማ ሲሉ፣ የራሳቸውን ድምፅ ብቻ እናዳምጥ ሲሉ፣ አለቃና ምንዝር እኩል ሲፋጠጡ፣ ፖለቲከኞች መቻቻል አቅቷቸው “ማን ከማን ያንሳል?” ሲባባሉ፣ የሚከሰት ነው፡፡ ማናለብኝ ማለት ሲዘወተር ነው፡፡ ህዝብ ሲረሳ ነው፡፡ ሀገር ከጉዳይ ሳትጣፍ ስትቀር ነው፡፡ በጠቅላላው ኃላፊነት ሲዘነጋ ነው። በተለይ ጉዳዩ በባለስልጣናት፣ በቢሮ ኃላፊዎች፣ በፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ካድሬዎች ላይ ተከስቶ ሲገኝ የብዙሃን ህዝብ ህልውና በእጅጉ ሊነካ ይችላል። መብት ይረገጣል፣ ፍትህ ርትዕ ይጎድላል። ይሄኔ ከአሳሳቢነት ወደ አደጋነት ይሸጋገራል። አደጋነቱም ማህበራዊ ምስቅልቅልን፣ ኢኮኖሚያዊ ድቀትንና ፖለቲካዊ መሰነጣጠቅን ያስከትላል። ወገናዊ ፍጅትን ያመጣል። ይኸው “አገራችን ወዴት እያሽቆለቆለች ይሆን?” የሚለው ጭንቀት፣ የየዕለት ጸሎት ወደሚጠይቅበት ደረጃ ይደርሳል። ስለዚህ እንፀልያለን! መሪዎች ሲወያዩና ሲገማገሙ፣ ሳያውቁ በስህተት አውቀው በድፍረት ለሰሯቸው የእምነት መዛባቶች፣ የአካሄድ መንጋደዶች ሁሉ ዛሬውኑ፣ ቶሎ ለማረም መዘጋጀታቸውን እንዲያሳዩ እንፀልያለን። እኔ ነኝ የበለጠ “ህዝባዊ”፣ “ዲሞክራሲያዊ”፣ “የፍትህ ተሟጋች” የሚልን ስሜት ሌላውም  (ተቃዋሚም)እንዳለው እንዲያስቡ እንዲከራከሩበትም እንጸልያለን።በአንድ ወገን የፖለቲካ ድርጅት አባል፣ በሌላ ወገን የመንግስት መዋቅር ወንበር ባለቤት ሲኮን፣ በሁለት ልብ የመተዳደርን ያህል ከባድ ነው። የፖለቲካ ድርጅት አባል ብቻ ሆኖ ደግሞ “የመንግስት መዋቅር ለእኔ ምኔ ነው”ሲባልም የራስ ደሴት፣ የራስ አምባ፣ የራስ ሀብት ቅርስ ማበጀት  ላይ  ብቻ  ማተኮር  ይሆናል። ማንኛውም ኃላፊ በመንግስት መዋቅር ላይ እስካለ ድረስ ለህግጋትና ለደንቦች ተገዢ፣ መመሪያዎችን ፈፃሚ፣  ሰብአዊ መብትን   አክባሪ መሆን አለበት። ማንም ከህግ በላይ ሊሆን አይገባውምና። 


ጥፋቶችና ህግ - የመጣስ ተግባራት  በተፈጸሙ   ጊዜም በወቅቱ እንዲታረሙና ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ መደረጉ እንጂ፣ “ያባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ” የሚለው  አያዋጣም። ያን የሚከተል ሰው “ትልቅ ዘራፊ ሲቀጣ አብረህ ተቀጣ!” የሚል  መርህ ለመቀበል ዝግጁ የሆነ ብቻ ነው።እዚህ ላይ መስተዋል ያለበት አንድ ጉዳይ፤ በማንም ሹም ላይ ችግር ቢፈጠር፣ ማንም ባለስልጣን በእኩይ ተግባሩ ቢጋለጥ “አለቃ  ሲነካ አሽከ ይነካል” የሚል አብረው የሚዘምሩ ወገኖች ቢኖሩ (ጥፋቱን ካልተጋሩ በቀር)፣ ሀገርንና ህዝብን ዋንኛ መመዘኛ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ማወቅ አለባቸው። አገር ውዝግብ ውስጥ ስትወድቅ የማይናድ የሚመስለው ይናዳል። ከድጡ ወደ ማጡ ይሄዳል። “ወጣ ወጣና  እንደ ሸንበቆ፣ ተንከባለለ እንደ ሙቀጫ” ያሰኛል።  ህዝብ መሪዎች ላይ እምነት ያጣል። ሰላም ሰላም የሚለው  ሁሉ  ትርምስና ሁከት ይሰማዋል። ይህም እንዳይሆን እንፀልያለን! ሙስና በስልጣን ፊት ለፊት በርም ይምጣ በፖለቲካው የጓሮ-በር፤ ዞሮ ዞሮ የአገርንና የህዝብን ገንዘብና በር፤ ዞሮ ዞሮ የአገርንና የህዝብን ገንዘብና ንብረት ለግል ጥቅም ማዋል ነው። ስለዚህም ህዝብ የፖለቲካ ባለስልጣኑንም ሆነ የመንግስት መዋቅር ሹሙን መጠየቁ፤ በዙሪያው የተገኘውንም “በበላህ ገብር፣ በሰማህ መስክር” ማለቱ  አይቀርም። 


ህዝብ የበደሉትን ይቅር ማለት  ያውቃልም፣ ይችልበታልም፤ ይማራልም። “ለሚያልፍ ቀን አንቀያየም” ከማለትም ይልቅ፤  “ሀጢአታችንን ያጸዳልን  ዘንድ በጊዜ ንሰሐ(ተውባ) እንግባ!” ማለትን ህብረተሰባችን ከተገነዘበ  ከተገነዘበ ውሎ አድሯል። ስለሆነም መስኩ ላይ ሆና ከምትጸልየው ግልገል ጋር  ሆኖ ለሀጥዓን ሁሉ ይፀልያል የነገሩትን የማይረሳ የለመኑትን የማይነሳ  መንግሥት ይሰጠውም ዘንድ አቤት ይላል። እያንዳንዱ ሰው  ክቡር ነው። አብረን እንጸልይ!!


(አዲስ አድማስ)

13 views0 comments
bottom of page