top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

በምዕራብ ጎጃም ጎንጂ ቆለላ ወረዳ ተመራማሪዎች በደቦ ጥቃት ሕይወታቸው አለፈ



በምዕራብ ጎጃም ዞን ጎንጂ ቆለላ ወረዳ ለምርምር የሄዱ ተመራማሪዎች ጥቅምት 13፣ 2011 ዓ.ም በተፈፀመባቸው የደቦ ጥቃት ሕይወታቸው አልፏል።

የጎንጂ ቆለላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ደመቀ መላኩ እንደተናገሩት ግለሰቦቹ ጥቃቱ በተፈፀመበት ቀን ጥዋት በአዲስዓለም የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ለተማሪዎች መረጃ ሰጥተው፤ ለጥናት የሚያስፈልገውን የምርምር ናሙና ሽንትና ሰገራ መሆኑን አስረድተው ከተመረጡ ልጆች ናሙናዎችን በመውሰድ ላይ ነበሩ።

ዕለቱም የአዲስ ዓለም ገበያ ቀን ሲሆን ት/ቤቱም በዚያው አቅራቢያ ይገኛል።

ዋና አስተዳዳሪ እንደሚናገሩት "በተሳሳተ መልኩ ልጆቻችን የጤና ክትባት እየተሰጣቸው ነው፣ እየተመረዙብን ነው፣ ሊገደሉብን ነው" በማለት ቁጥራቸው በርከት ያሉ ግለሰቦች ወደ ትምህርት ቤት አምርተዋል።

በወቅቱ የነበሩ የትምህርት ቤቱ ጥበቃዎችም ከቁጥጥራቸው ውጭ በመሆኑ በአካባቢው በነበሩ ጥቂት ፖሊሶች ታግዘው ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመወሰድ ላይ ሳሉ በወረዳው በሚገኝ አዲስ ዓለም የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት አቅራቢያ መናሃሪያ አካባቢ ጥቃቱ እንደደረሰባቸው አቶ ደመቀ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ዋና አስተዳዳሪው ስለ ግለሰቦቹ ማንነትም አስመልክቶ እንደገለፁት አንዱ ግለሰብ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሶስተኛው ዲግሪ ጥናት ወደ ቦታው ያመራ ሲሆን፣ ሌላኛው በሜጫ ወረዳ በሚገኝ ጤና ጣቢያ የሚሰራ የጤና መኮንን ናቸው።

የወረዳው የጤና ባለሙያም ጉዳት ደርሶበት በአካባቢው የጤና ተቋም ህክምና እየተደረገለት እንደሆነ አስተዳዳሪው ይናገራሉ።

የወረዳው የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ አንተነህ በላይ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ባህር ዳር ክትባት ሲሰጡ ሞቱ በሚል በተናፈሰ ወሬ ምክንያት መኪና መሰባበርና በሰዎችም ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውሰው አካባቢው ለባህርዳር ቅርብ በመሆኑ ይሄው መረጃ በመናፈሱ ጥቃቱ ሊፈፀም እንደቻለ ያስረዳሉ።

"ግለሰቦቹ ደብዳቤ ቢይዙም ወረዳውን አላሳወቁም" የሚሉት ኃላፊው ከሁለት ት/ቤት ናሙና ለመሰብሰብ ወረዳውን ጤና ፅ/ቤት እንደጠየቁና ደብዳቤ ተፅፎላቸው ቀጥታ ወደ ት/ቤት እንደሄዱ ይናገራሉ።

በድንጋይና በዱላ በደረሰባቸው አሰቃቂ ጥቃት ህይወታቸው ወዲያው ማለፉን ኃላፊው አስረድተዋል።

ጥቃቱ የተፈፀመው ከቀኑ 7፡30 ገደማ ሲሆን የፀጥታ ኃይሎች 10፡30 ገደማ ሁኔታውን ማረጋጋት እንደተቻለ ገልፀዋል።

ግለሰቦቹ የአካባቢው ተወላጆች በመሆናቸው ማህበረሰቡ ፀፀት እንደተሰማው ገልፀው "እጃችንን በእጃችን ቆረጥን፤ አገር የሚጠቅሙ ምሁራንን አጣን!" በሚል በድርጊቱ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን አጋልጦ መስጠት የጀመረውም ራሱ ህብረተሰቡ እንደሆነ ባለሙያው ይናገራሉ።

በተጨማሪም የአካባቢው ተወላጅ የሆኑና ቤተክርስቲያን ለማሰራት ድጋፍ እያደሩ የነበሩ ግለሰቦችም መኪናቸው የተመራማሪዎቹ ንብረት ነው በሚል ጥርጣሬ ጥቃት ቢሞከርባቸውም፤ በአካባቢው ይታወቁ ስለነበር ከጥቃት ሊድኑ እንደቻሉ የወረዳው አስተዳዳሪ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ መኪናቸውን እንደተቃጠለ ዋና አስተዳዳሪው ጨምረው ተናግረዋል።

በጥቃቱ እጃቸው አለበት የተባሉ 27 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው የማጣራት ስራው እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል።

BBC - Amharic


12 views0 comments
bottom of page