top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

“መስቃን በተቋም ይመራ”

Updated: Jan 29



በ2019 እ.አ.አ የመስቃን ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ አመራሮች፣ ባለሃበቶች እና ዳያስፖራዎች ቡታጅራ ከተማ አድርገውት በነበረው ወሳኝ ስብሰባ በቀረበው ጽነሰ መሰረት በትኩረት ከተወያዩ በዃላ ወስነው፣  መርቀው አደራውንም ለተወላጆች አስተላልፈው እና አስረክበው ነበር። በወቅቱ ካልተሳሳትኩ ስብሰባው የጠሩት አምባሳደር ድንበሩ አለሙ እና ሌሎች ቀደምት አመራሮች ነበሩ። ተሰብሳቢዎቹ በሙሉ በሚባል መልኩ መስቃን በተቋም ይመራ የሚለውን ጽንሰ ሃሳብን በሙሉ ድምጽ በመደገፍና በመወሰን እንዲሁም በባህሉ እና ወጉ መሰረት አዘጋጆቹን መርቀው አደራውን ለሚመለከተው ሁሉ ማስተላለፋቸውን ከአምባሰደር ድንበሩ ጋር በግል ባደረግናቸው የቴልፎን ውይይቶች እንዲሁም በጋራ ባደረግናቸው የበይነ መረብ ስብሳበዎች (መካከለኛው ምስራቅ እና አለም አቀፍ የመስቃን ተወላጆች ያካተተ) በተደጋጋሚ ሲገለጽ ሰምቻለሁ። በተጨማሪም በእለቱ በቡታጅራ ከተማ ስብሰባውን ተካፍለው የነበሩ በሪያድ ሳዑዲ አረቢያ የመስቃን ልማት ማህበር ተወካይ እንዲሁም አባል የሆኑ ወንድሞቻችን ይህኑኑ አረጋግጠዋል።

ሽማግሌዎቻችን አደራውን ባስተላለፉት መሰረት ስራዎች ተጀምረው የነበሩ ቢሆንም በተፈለገው መልኩ ካለመፍጠኑ ባሻገር በዕለቱ በልዩ ሁኔታ የተጠሩ እና ስብሰባው ተካፍለው የነበሩት ተወላጆች ውሳኔ ላገኘው ጉዳይ እና ያንን አደራ ተቀብለው ከግብ ለማድረስ ይተጉ ለነበሩት ለቅን አሳቢያዎቹ ቀደምት አመራሮች ጀርባቸውን ሰጥተው እንደነበር ጉዳዩን የሚያውቀው ሁሉ በትዝብት መዝገብ አስፍሯቸዋል።

የተነሳሁበት ጉዳይ ለወቀሳ አይደልም። ማን ለአካባቢው ሰራ? እንዲሁም አብሮነት በሚያዳብር መልኩ ማን ምን አከናወነ? ለሚለው ህዝቡና እና ስራው እራሱ ያውቀዋል። በተጨማሪም ደህና ወይም መልካም የዘራ ባለ ብዙ ደህና እና ባለ ብዙ መልካም ባለቤት እንደሚሆን እሙን ነው። መጥፎ ዘርቶ ግን ደህና ወይም መልካም ምርት የሰበሰበ ከቶውን አይኖርም። ለምን ቢባል የመጥፎ ዘር ውጤቱ መጥፎ ብቻ ነውና። በእርግጥ እነዚያ በጀርባ መስጠት ስማቸው የሚነሳው በመስቃን ማህበረሰብ ላይ መጥፎ ያስባሉ እንዲሁም መጥፎ ይሰራሉ ለማለት ባያስደፍርም ግዙፍና ሰፊ የሆነ እንዲሁም ለማህበረሰብ በሚጠቅም ጉዳይ ላይ እነርሱ ስላልጀመሩት በቻ አለመሳተፍ ወይም አለማገዝ በራሱ ወደ መጥፎ ይወስዳልና እንጠንቀቅ ለማለት ያህል ነው።

የተባለው ተቋም ከምን ደረሰ? የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆን… ይሆናል። ጉዳዩ ብዙ አወያይ ስለሆነ እና ሰለሚሆን ለዛሬው እንዲተው ይሁን።  

የአመታቱ የመስቃን ማህበረሰብ ጥረት መና ሆኖ አልቀረም። በተፈለገው እና በታቀደው መልኩ ምስራቅ ጉራጌ ዞን ተመስርቷል። ለአመታት በመስቃን ማህበረሰብ ላይ ተጣበቀው ጥሪቱን ሲነጥቁ፣ ምርቱን ሲያደርቁ እና ትውልዱን ሲያመክኑ የነበሩት መዠገሮች በመስቃን ህዝብ የአመታት ያላታከተ ዱዓ እና ትግል ላይመለሱ ከላዩ ላይ ተነስተዋል። 

ትላንት በውስን አመራሮች ተወሰኖ የነበረው ተቆርቋሪነት ዛሬ ላይ ከውስኖች አንገራጋሪዎች፣ ወላዋዮች እና ሆድ አደሮች በቀር አብዛኛው አመራር ወይም ተሿሚ ቀፍድዶት ከነበረው የፍርሃት ቆፈን ተላቅቆ ውክልናውን በተገቢው ሁኔታ እየተወጣ እና ድምጽ ከፍ አድርጎ እያሰማ ይገኛል። በተጨማሪም በጣም ውስን የነበረው የመስቃን ተወላጆች የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ የሶሻል ሚድያ ተሳትፎ ዛሬ ላይ ሺዎቹ እየተሳተፉበት፣ በባህሩ እየዋኙበት እና እየቀዘፉበት ይገኛሉ።

የቀረ ጉዳይ ቢኖር ህጻናቶች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ መወሰን እና ግብአቱን ማዘጋጀት ብቻ ነው። ማህበረሰብ ልጆቼን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ላስተምር ብሎ ቢጠይቅ ወይም ቢፈልግ ከልካልይ ይኖራልን? ህገ መንግስቱስ ይከለክላልን?

 

ቪዲዮን ያደረሰን ወንድም ሸመሱ ጀማል ነው። የተመሰገነ ይሁን።


ኢዱና አህመድ ኡስማን

መስቃን ሚድያ ኔትዎርክ  

32 views0 comments
bottom of page