top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

“ምናባዊው የዘጠኙ ጉራጌዎች አብሮነት” (በኢዱና አህመድ ኡስማን)


“ምናባዊው የዘጠኙ ጉራጌዎች አብሮነት”

እነርሱ እንደሚሉት ወይም “ቤተ ጉራጌ” ብለው እንደሚጠሩት እኛ ቤተ ጉራጌውያን አንድነት እና አብሮነት አለን ወይም አንድ ነን የሚለው ቃል ወይም አባባል ሲጠቀስና ሲሰማ የሚስተዋለው ከሶሻል ሚድያው ብቻ ነው። የአንድነት መሰረቱ ምንድ ነው ወደ ሚለው ከተመጣ ደግሞ ለአመታት ሲደረግ የነበረው የጉራጌውያን የአብሮነት ዲስኩር ምርቱ ገለባ ነው የሚሆነው።

እስቲ ምላሽ ወዳልተገኘለት ጥያቄ ልግባ፡-

1. ቤተ ጉራጌ የሚለው ስያሜ ከየትና እንዴት መጣ ?

2. የሰባት ቤት ጉራጌ ማህበረሰብ “ጉራጌ” የሚለውን ስያሜ ለማግኘት ለምን ሰባት መሆን አስፈለገው?

እላይ ለተጠቀሱት ነጥቦች የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ምላሽ ይኖራቸዋል ብዬ አስባለሁ! እጠብቃለሁም።


የጉራጌ ማህበረሰብ ጉራጌ ብቻ ተብሎ ያልተጠራበት ምክንያት ወይም “ቤተ” የሚለው ተቀጽላ የተካተተበት ምክንያት ግልጽ ባይሆንም ለአሁኑ ለጉራጌውያን መሰነጣጠቅ በር ከፋች እንደሆነ አመላካች ነው ብዬ አምናለሁ። አሁን ያለንበት ነባረዊ ሁኔታ ካስተዋልን የሰባት ጉራጌ የመንግስት አመራሮች የስልጣን ስግብግብነት እና የስልጣን ጥም መንስኤው “ሰባት ነን” ከሚለው የመነጨ ነው ባይ ነኝ። ታዲያ… ይህ ሰማይ የነካውን የሰባት ቤት ጉራጌን የመንግሰት አመራሮች የስልጣን ጥምን ለማረጋገጥ ከዞን ጅምሮ እስከ ፌደራል ያሉ መዋቅሮች መበርበሩ የግድ ይላቹሃል።

የመስቃን ቤተ ጉራጌ እና የሶዶ ቤተ ጉራጌ እንደ ጉራጌ አካል በእኩል የስልጣን እርክንን ይጋራሉ? ለሚለው ሶዶ ቤተ ጉራጌ በከፊል ከዞን ጀምሮ እስከ ፌደራል ባሉ እርክን ውስጥ የሚገኙ ሲሆን የመስቃን ቤተ ጉራጌ ግን ወልቂጤ ከተማው የሚገኘው የዞን መዋቅር ውስጥ በጣም ውስኑ የሆኑ የቤተ መስቃን ተወላጆ አመራሮች በዞን ደራጃ ላለው የስልጣን እርከን ቢደርሱም ጉራጌ ዞን ውስጥ በሚተበተበው ወጥመድ ምክንያት ይፈረጁና ከሃላፊነት እንዲነሱ ይደረጋል። በጣም የሚገርመው ደግሞው በተነሳው ሃላፊ ምትክ ሌላ የቤ መስቃን ተወላጅ ይተካና ምንልባት አንድ አመት እንዲሰራ ነው እድል የሚሰጠው። እርሱም ልክ እንደ ቀድሞው ወንድሙ ተመሳሳይ እጣ ይገጥመዋል። እናንት... የሚመለከታችሁ ሁሉ! ልብ እንድታደርጉ የምሻው ጉዳይ ቢኖር የቤተ መስቃኑ ተወላጅ የመጨረሻው የስልጣን እድገት ወይም እርከን እስከ ዞን ድረስ ብቻ መሆኑን ነው። ሌላው ደግሞ የቋንቋ አጠቃቀምን እና ከዞን እስከ ክልል ያሉትን ትላልቅ የስልጣን እርከኖችን በተመለከተ አንዳንድ የዋሆች ወይም የመርካቶ ሰዎች ምን ችግር አለው? ሁሉም ጉራጌ ሲሉ ተስተውለዋል። እነርሱ... ፍጽም የዋህ በመመስል ለሚሰነዝሩት ሃሳብ እንደ እነርሱው የዋህ በመምሰል “ ትክክል እንደሆኑና ሁሉም ጉራጌ እንደሆነ ነገር ግን ዞኑን መስቃን ያስተዳድር እንዲሁም የመስቃንኛን ቋንቋ ሁሉም ጉራጌዎች በእኩል ስለሚረዱት ልጆቻችሁ እና ልጆቻችን የመስቃንኛ ቋንቋን እንዲማሩት ይሁን” የሚል ምላሽ ሲሰጣቸው ጉራጌነትህን ይክዱታል። ለእነርሱ ጉራጌ ማለት ሰባት ቤት ነው። በተጨማሪም ትክክለኛው የጉራጌ ቋንቋ ብለው የሚያስቡት የሰባት ቤተ ጉራጌ ቋንቋን ብቻ ነው። በጣም… ግር የሚለው ደግሞ የትኛው የሰባት ቤተ ቋንቋ የሚለው ጥያቄ ሲመጣ የሰባቱ አንድ አለመሆን ፍንትው ብሎ ይታያል። ሰባት ቤት ጉራጌውያን ሰባት ይሁኑ እንጂ አንድ ናቸውን ተብሎ ቢጠየቅ “አንድ ለመሆን ሰባት ለመሆን አስፈለገ” የሚለው ምላሽ ሊሰጥ እንደሚችል ምንም ጥርጥር አይኖረውም። የሰባቱ አንድ አለመሆንን በተመለከተ እንደ መስቃን ልማት ማህበር የሪያድ የሳውዲ አረቢያ ቅርንጫፍ በምናደርጋቸው ልማታዊ እንቅስቃሴዎች የሰባት ቤት ጉራጌውያን ቀደምት ባለስልጣናት ለስራ ጉዳይ እዚህ ሪያድ በመጡበት ወቅት ከወረዳ ጀምሮ እስከ ፌደራል ባለው የሃለፊነት እርከን ውስጥ እንደ ትግራዩ “የአድዋ ተወላጅ” ከሰባት ቤቶች ውስጥ ተመራጭ ቤተሰቦች እንዳሉና እርሳቸውም በከፍተኛ ተጽእኖ ስር ሆነው ላሉበት ደረጃ መድረሳቸውን አሳውቀውን ነበር። ከሰባት ቤት ውስጥ ማን ነው ለስልጣን ተመራጭ የሆነው ቤተሰብ ለሚለው ወደ ፊት እንደ አስፈላጊነቱ እንመጣበታለን።

የጉራጌ ታሪክና በጉረጌነት ዙሪያ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ አላስኬደ ያሉትን ወይም ሌላውን እየጎዱት ያሉትን ጉዳዮችና ሂደቶችን ነቅሶ ለማውጣት በሚሞከርበት ጊዜ ለሰዉ የሚመስለው የአንድ አለመሆን አባዜ የመጠናወት ወይም እኩይነት አይነት ነው። እንደ ግሌ ከሆነ አንድ ነን የሚለው ባያስማማኝም ችግራችን በመቅረፍ አንድ ለመሆን ወይም በአንድነት ለመጓዛ ተስማምተን እየጣርን ነው የሚለው ይመቻል። ነገር ግን እነ ማን ናቸው አንድ ለመሆን እየጣሩ ያሉት ወደ ሚለው ሲመጣ ሶሻል ሚድያ ላይ የሚራኮቱት ብቻ ሆነው ይገኛሉ። ለአንድነት የሚደረጉ ትላልቅ ስራዎች እና አንዳንድ ስራዎች ዝግጅት ወይም ድግስ አዘጋጅተን ለግብዣ በሚጠሩ የተወሰኑ የማህበረሰብ ክፍል ግለሰቦችና ውስን አመራሮች ብቻ የሚወሰን እና የሚለካ አይደለም። የጉራጌውያን ጉዳይ ከፕሮፐጋዳ ስራ በላይ ወይም የገዘፈ ከሆነ ሰነባብቷል። የጉራጌውያን የጥምረት ጉዳይ ፕሮፐጋንዳ አያቃናውም። ይህን ሰራን ወይም አደረግን ተብሎ በሚለጠፍ ፎቶ በተጨማሪም ራስ እና እግር በሌለው ወሬ ብቻ የጉራጌውያን የጥምረት ሁኔታ የሚለካ መሆን የለበትም። አንደኛ የአንደኛውን እና ሌላኛ የእዛኛውን ጉዳይ በእኩል መረዳትና ማክበር አለበት። ያኔ! ነው አንድን ነን ወይም እየሆንን ነው ለማለት የሚቻለን። ወደ መደምደሚያው ስመጣ አንድነት የስልጣት ጥማት በተጠናወታቸው ፖለቲከኞች ቢሮ እና በሶሻል ሚድያ በሚረጭ ጊዜ ያለፈበት የፕሮፐጋንዳ ስልት ሳይሆን ፍጽሙ ጥልቅ በሆነ ወንድማማችነት ተመስርቶ ከእታች ጀምሮ ሲስራ ነው እውን ሊሆን የሚችለው። በእላይ ደረጃ ብቻ ከሆነ መሸዋወድ እና መሸነጋገል ይበዛበታል ። ወይም "እከክልኝ ልከክልህ" አይነት ነው።

ወዳጄ ሆይ አንድነቱን የምትሻ ከሆነ...ፖለቲከኛውን ከሃይማኖት አባት እና የሃገር ሽማግሌዎች እንለየው! ያኔ... መንገዱ ፍትው ብሎ ይታየናል። ነገር ግን ማን ነው ፖለቲከኛ ያልሆነው ተብሎ ቢጠየቅ... እኔ እንጃ! ይሆናል መልሴ...


የተነሳሁበት ርዕስ “ምናባዊው የዘጠኙ ጉራጌዎች አብሮነት’ የሚል ሲሆን አብረን ነን ለሚለው? አዎን… እንደ ሰውና እንደ… ኢትዮጵያዊ አብረን ነው ያለነው። ነገር ግን እውነታው ወይም እንደ ጉራጌውያን ነባራዊ ሁኔታ ከሆነ ዘጠኝ ስንሆን የማንስማማ እና አጋጣሚውን ካገኘን የምንጎዳዳ አይነት ነን። ታዲያ… ከጉራጌውያን መካከል ምናልባት በቁጭት “እኔ ሌላውን የጉራጌ አካል አልጎዳሁም ወይም አልጎዳም” የሚል ከተገኘ ይህ ግለሰብ ለፈጣሪው ቃል የተገዛ ፍጹም ቅን ሰው ነው ማለት ነው። ወይም በተከፈተው ቦይ ብቻ የሚሄድ እና እይታው የተጋረደበት ጭሰኛ ብቻ ነው ሊሆን ነው የሚችለው። ለምን ቢባል? ቅን ሰው ያው ቅን ነው። ሁሌም ቢሆን የሚታየው መልካም ሲሆን ጭሰኛው ግን “የጎባጣ አሽከር አጎንብሶ ይሄዳል” እንደሚባለው ጭሱ እይታውን ስለሚጋርደው ከጌቶቹ አመልካከት ከማራመድ ፣ ከሚሰጠው ተስፋ እና ከሚተላለፍለት ትዝዛዛት ውጪ የሚታየው ምንም አይኖርም። ከማሳረጌ በፊት “ ስለ ዘጠኙ ጉራጌዎች” እነ ማን ናቸው? ለሚለው ዛሬ ላይ ሆናችሁ የጉራጌውያን ፍላጎትን በጥለቀት መዳሰስ ስትጀምሩ ከዘጠኞቹ ባሻገር አስረኛውን የጉራጌ አካል ጭምር ታገኙታላችሁ።

ቸር እንሰንበት!

ኢዱና አህመድ

ሪያድ ሳውዲ አረቢያ

74 views1 comment
bottom of page