top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ነብስ-ያወቀ ውሻና ነብስ-ያላወቀ ሰው

ከዕለታት አንድ ቀን፤ ነብስ-ያወቀ ውሻ፣ አንዲት መሸታ ቤት፣ ግሮሠሪ ገብቶ፤ ነብስ-ያላወቀ ሰው፣ሲመሽት አግኝቶ እንደ ሰዉ “ሃይሃይ!፣ “ፒስ ነው” “ኩል ነው!” - ሳይል፤ በወግ እጅ ነስቶ እንዳገሩ ባህል፣ ሰላምታውን ሰጥቶ፣ በውሻ ትህትና ጂን አዞ ቁጭ አለ-በረዶና ሎሚ፣ ባናቱ አረገና፡፡ ሰውዬው አንድ እግሩን፣ በሌላ ወንበር ላይ፣ አሻግሮ ቸክሎ በዚህኛው ጐኑ፤ ባለጌ ወንበር ላይ፣ ባለጌ እግሩን ሰቅሎ ቡችላ ቀለበት፣ የእጅ-አምባር ሠንሠለት…፣ በክፍት ሸሚዙ የሚታይ ሀብል ወረት እንዲያው በጥቅሉ፣ መስሎ ሱቅ ወርቅ ቤት .. በእጁ እሚሽከረከር፣ መኪና-ቁልፍ ዓይነት … ደሞ ጨምሮበት ይዞ ኮራ ብሎ፣ ብልጭልጭ ሱፍ ለብሷል … በጅንን-ዕይታ፤ ውሻውን ያየዋል፡፡ ውሻ ጂን ሲጠጣ፣ አይቶ አያውቅምና በቅጡ ገርሞታል!! ውሻውን ሊጠይቅ ገና ዐይኑን ሲያቀና “ምነው ተገርመሀል? ግርያለህ መስለሀል?” አለው ውሻው ቀድሞ፤ “ውሻ ግሮሠሪ ገብቶ ሲጠጣ ሳይ … እንዴት አልገረም?” አለ ሰው ተደሞ፤ ውሻ በውሻኛ ፈገግ-ለቀቅ ብሎ፣ … ድምፁንም፣ ጂኑንም፤ በውል አጣጥሞ “ከብዙ ግብዝ ሰው፣ ቅን ውሻ እንደ ሚሻል፣ ሳይህነው የገባኝ በድህነትህ ላይ፤ በአንጐልክም፣ በሰውህም-መዘነጥህ ገርሞኝ ማንኛውም ፍጡር፣ ከአካላቱ ይልቅ፣ ጌጣ-ጌጡ በዝቶ፣ የበቅሎ መጣምር፣ ግላስ ሲመስልብኝ ሰው የጌጥ ዕቃነው ስንጥቅጥቅ መስተዋት ቁሳቁስ ነው አልኩኝ!” ሰውዬው ገረመው፤ “እንዲህ ልትል የቻልክ፣ እንዴት ብታየኝ ነው?” አለና ጠየቀው “እኔማ ያየሁህ፣ በውሻ አተያይ ነው፡፡ ቆይ አንዴ ታገሠኝ፣ ከአፍታ በኋላ ደግሞ እንገናኛ አለው በሬዲዮው በ “ኤፍ-ኤም”ኛ!!” መናገር ሊቀጥል ውሻ በውሻኛ ጂኑን ጠጣ ጠጣ … አፍ-አፉንላስ ላስ … የዝናብ መጥረጊያ እንዳለው መኪና ግራ ቀኙን ዳሰስ ሊፕስቲክ አውጥቶ ከንፈሩን ተም-ተም፣ ላይ-ታቹንላግ-ላግ፣ እንደ ሴት-ቄንጠኛ … “ሰዎች ስትባሉ፣ እሩጫ አበዛችሁ እኛንም ጨምሯል፣ አጉልህ ይወታችሁ … እኔም እንደናንተ፣ እንዳቅሜ ሮጣለሁ ትንሽ እጠጣና፣ ፀጉርቤት እሄዳለሁ ፀጉሬን አሳጥሬ፣ እስተካከላለሁ ብታምንም ባታምንም፣ ቀለም መቀባባት … ሂውማን ሄይር ምናምን … በጣም እጠላለሁ፡፡ ከዛሠርግ አለብኝ፣ ከመንጋ አጃቢ ጋር፣ ገና እጃጃላለሁ፡፡ አበሻ ሲገበዝ፣ ላንድቀን ሲሞሸር፣በምፀት አያለሁ፡፡ የነገ ፍቺውን፣ ዛሬ ሲያመቻቸው፣ እታዘበዋለሁ! የውሰት ቬሎውን፣ የውሰት ጌጥ-ወርቁን፣ የውሰት ደስታውን … ሽንጣም ሊመዚኑን … ሲመዝን አያለሁ!! ሰውዬው በግርምት እንዲህ ሲል ጠየቀ፡- “አንተ ለመሆኑ የፈረንጅ ውሻ ነህ፤ የአበሻ ውሻነህ?” “ማይ ጋድ!” አለ ውሻ፣ “በተማረ” ልሣን፣ በፃድቅ ውሻኛ፡፡ “ውሾች እንደ እናንተ እንደ ነጭ-አምልኮች “ፈረንጅ” “አበሽ” ብለው፤ ውሻን አይፈርጁም፤

አንዱን ዘርከሌላው አያበላልጡም፡፡ ይልቅ ልጠይቅህ፣ አንድ ተረት መሳይ፣ አላችሁ አባባል “ውሾን ያነሳ ሰው ውሾን ይሁን” የሚል ይህ እንዴት ተባለ፣ ከየት መጣ ይሄ ቃል?”… ሰውዬው መለሰ፤ “ከዕለታት አንድ ቀን፣ ርሀብ የመታቸው፣ አንድ ልጅና አባት ማሣቸው ሲቃጠል በድንገተኛ እሳት፡፡ አይተው እንደልማድ፤ ለማምለጥ ያልቻለ አንድውሻ አብሮ ሲነድ፤ “ተጠብሷል! እንብላው! ምንይለናል?” ብለው ከጠኔ ሊድኑ በሉት ተስገብግበው፡፡ ግን እንስማማ አሉ ለማንም ላይነግሩ በውል ተማማሉ፡- ውሾን ያነሳ ሰው፣ውሾን ይሁን አሉ”፡፡ ውሻው እየጠጣ፣ ከትከት ብሎጮኸ፤ ሳቀ፣ በውሻኛ “ሰዎች ስትባሉ፣ አያልቅም ጉዳችሁ … ከበላችሁ ወዲያ፣ ህግ ማውጣትማ፣ ታቁበታላችሁ!! ለነውር ሥራችሁ፣ ለመሶቡ ግጣም፣ ታበጃጃላችሁ! የሰውልጅ ይሄው ነው፣ ውሻን ቅርጥፍ አርጐ ከበላ በኋላ ውሾን ያነሳ ሰው ውሾን ይሁን የሚል ያመጣል መሀላ” አለውሻ ሆዬ፣ ጂኑን አወራርዶ፤ ምፀት ማስታገሻ፤ “ሌላም ልጠይቅህ-‘ውሻምን አገባት፣ የምትገባው እርሻ’ የሚልም አላችሁ፣ ትርጉሙ ምንድነው፣ የቃሉ መነሻ?” “ይሄ እንኳ ዘይቤነው - ሰው አለጉዳዩ ገብቶ ሲዘባርቅ ወይም አለሙያው፣ በማያውቀው ጦር ውስጥ፣ ላይተኩስ ሲባርቅ ወይም አላገሩ፣ አለወንዙ ገብቶ፣ አጉል ሲምቦጫረቅ ይህተረት ይወሳል፣ ልኩን ለማሳወቅ!” …. ከትከት ብሎ ሳቀ፣ ውሻው ሞቅ እያለው “ቅኔውና ኅብሩ፤ ስላቁ እዚህ ጋነው - ገቢሩ የሰው ነው፣ምሳሌው ውሻነው ሰው አይረባም ያልኩህ፣ ይሄን ጨምሬ ነው!” “ና ድገመኝ!” አለ፣ አሳለፊጠራ፤ በቅን ውሻነቱ፣ ጨምቶ እየኮራ!! “ደሞም እንደ ውሻ ጭራህን አትቁላ” ሲሉ ሰምቻለሁ “የእኛኑ ጭራ ነው፤ ሌላ ጭራ አላችሁ?!” ሰውዬው ከቢራው ጥቂት ተጐንጭቶ (ያው ጭራ እንደ መቁላት ጥቂት ተወራጭቶ) “ጭራ ወይም ጅራት፣ መንፈስ ነው፣ምላስ ነው የሐሞተ-ቢስ ሁሉ፣ የዥዋዥዌ ክር፣ የእጅ-መንሻ ድርድር የአድር-ባይ፣ ቅቤ አንጓች፣ ተብትቦ ያሠረው! ቱሻ ወፍቾ ነው -”… አለና ነገረው፡፡ “አይ የሰው ልጅማለት፣ ይገርመኛል ከቶ ጭራውን ይቆላል፣ በውሻ አመካኝቶ!” አለና ሎሚውን ጅኑ ውስጥ ጨማምቆ፣ ጨልጦ ተነሳ፡፡ ሰውዬው ቢራውን ጥቂት አጣጣመ “አንድ ነገር ብቻ ልጠይቅህ እስቲ - ከመሄድህ በፊት፤ ዕውነት ውሻ ማነው?” ውሻው በውሻኛ እንዲህ ሲል ፈፀመ፡- “ውሻ ማነው አልከኝ? … ውውው ዋዋዋ! ዎዎዎ፣ ዋዋዋ!” ብሎ በሆህኛ … “ውሻማ ራሴ ነኝ!! እኔ ሞትኩ የምለው የሰው ልጅ ለመሆን የሞከርኩ እለት ነው! ለምን አትለኝም? አየህ እዚህ እኛ አገር፣ ውሻና ሰው እኩል፣ ሲመሽት ቢገኝም ሰውኮ እሚኖረው፣ በ “ሚስ-ኮል” ብቻ ነው፤ ሀብታሙ እሚኮራው፣ በባንክ ብድር ነው፤ አገሩ እሚሸልል፣ ባለም ባንክ ስፖንሰር፣ ነብሱን አሲዞ ነው፤ ዜጋውአለሁ የሚል፣ለየነብስ አባቱ፣ኑዛዜ ሰጥቶነው፤ ታዲያ እኔ ወዳጄ፤ ሰው ልሁን የምለው፣ ምን ልሁን ብዬ ነው?! አንተም የምትሞተው ውሻ መሆን ላትችል፣ ውሻ ነኝ ካልክ ነው! ቦታ አልቀይርህም! ራስክን ችለህ ቁም-ማንነት የራስነው

(ራሳቸውን ለመሆን ላሰቡ) ታህሣሥ፤ 20006 ዓ.ም

ከአዲስ አድማስ ድረ ገጽ የተወሰደ

39 views0 comments
bottom of page