top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ኢስላምን ለማሻሻል የፈረንሳዩ የማክሮን መንግስት የጀመረው አብዮት እስከ የት? ( በሳዲቅ አህመድ ኡስማን)

Updated: Oct 31, 2020



የማክሮንና የኤድሮጋን ፍጥጫ!


መንግስትና የሐይማኖት ተቋማት መለያየት አለባቸው፤አገሪቱ የምትመራዉ በሴኩላሪዝም ነው፤ሐይማኖት የግል ምርጫ ነው የሚለው ፍልስፍና የፈረንሳይ ብሔራዊ ኩራት ነው።የራሷን ብሔራዊ ኩራት በሚጻረር መልኩ በ1980ዎቹ የሒጃብ አብዮት የጀመረችዋ ፈረንሳይ የነብዩ መሐመድ (ሰአወ) የካርቱን ምስልን የመሳል መብት ለዜጎቼ አስከብራለሁ ብላ ቆርጣ ተነስታለች።ጉዳዩ አለም ላይ ባሉ ሙስሊሞች ዘንድ ሐይማኖትን ማራከስ ተደርጎ ቢቆጠርም ፈረንሳይ ይህንን ማገድ አልችልም ብላ ቆርጣለች።ከካርቱን ጋር ተያይዞ በሚነሱ ግጭቶችና በሚፈጠሩ ጥቃቶች ሰለባ የሆኑ ግለሰቦችን ብሔራዊ ጀግና በማድረግ ዜጎቿንና አለምን ለማሰለፍ ብትጥርም እምብዛም ውጤት አላመጣላትም።


የፈረንሳይ ኢምፓየር ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በሗላ ሽንፈት ገጠመው።ጃፓን፣እንግሊዝ፣ዩናይትድ እስቴስና ጀርመን የፈረንሳይን ቦታ ተረክበው በቀድሞ የፈረንሳይ ግዛቶች ላይ ልእቅናቸውን ማሳየት ጀመሩ። ፈረንሳይ በመዳፏ ስር ከቀረችዋ አልጄሪያ እንድትወጣ በ1954 ህዝባዊ ንቅናቄ ተጀመረ።የአልጄሪያ ነጻ አውጪ ግንባር ተወለደ።አልጄሪያውያን በቁርጠኝነት ተዋጉ።አልጄሪያውያን የፈረንሳይን የቅኝ ገዢ ሐይል በመስዋእት ድባቅ መቱና በ1962 ነጻነታቸውን አወጁ።ፈረንሳይ ከሁለተኛው አለም ጦርነት በሗላ ከገጠማት አስተዳደራዊ መኮማተር ብሎም የቁስና የስነ-ልቦና ቀውስ ሳትላቀቅ አልጄሪያውያን ውርደትን አከናነቧት።ይህ ውርደት የሰው ልጆችን መብት አክባሪ ናቸው በሚባሉት ፈረንሳውያን ዘንድ የሚዋጥ አልሆነም።አሸናፊዎቹ አልጄሪያውያን ሙስሊሞች በመሆናቸው «ሙስሊም-ጠልነት» ከሽንፈቱ መልስ ተጠነሰሰ።ካቶሊኮች፣ሙስሊሞች፣አይሁዳውያንና ፕሮቲስታንቶች ሐይማኖትን የግል አርገው በሚኖሩባት ፈረንሳይ ውስጥ ስልታዊና አስተዳደራዊ «ሙስሊም-ጠልነት» በ21ኛው ክ/ዘመን ከፓሪሱ ማማ በላይ ገዝፎ የሚታይ እውነታ ሆነ።


ፈረንሳይ በውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት (FDI) የምጣኔ ሐብታቸውን ካጠነከሩ አገራት ተርታ የምትመደብ ናት።በአለም ላይ ጠንካራ ኢኮኖሚ አላቸው ተብለው ከተመዘገቡት 10 አገራት መካከል በሰባተኛነት ደረጃ ተቀምጣለች። ፈረንሳይ በአለም ላይ በጣሙን የምትጎበኝ የአውሮፓው ማህበረሰብ አካል ናት።በአውሮፓ ውስጥ ካሉት አገራት መካከል በእርሻ አምራችነት በቁንጮነት የተቀመጠችዋ ፈረንሳይ ከአለም ላይ ስድስተኛዋ የእርሻ ምርት አምራች ናት።ክዩናይትድ እስቴትስ በመቀጠል ሁለተኛው የእርሻ ውጤቶችን ላኪ አገር መሆኗን ኢንቨስቶፒዲያ ዘግቦታል።


በምእራብአውሮፓ ውስጥ በመልከአ-ምድራዊ አቀማመጥ ለንግድና ለቱሪዝም የተደላደለችዋ ፈረንሳይ የውጭ ኩባንያዎችን ስቦ ሊያመጣ የሚችል ምቹ ህጎች እንዳሏት ዘገባዎች ያመላክታሉ።የፈረንሳይ የምጣኔ ሐብት ጠንካራ ቢሆንም የአገሪቱ ዲሞክራሲ የሚያበቅላቸው መሪዎች በውጭና በአገር ውስጥ ፖሊሲያቸው ደካማ ናቸው የሚል ትችት ይቀርብባቸዋል።ከፍተኛ የቀረጥ ክፍያ መኖሩ፣የዜጎች እኩልነት አለመከበርና የወዛደር ደሞዝ መናር ለፈረንሳይ የምጣኔ ሐብት መላቅ እንቅፋት የሆኑ እውነታዎች ናቸው።


ቱሪዝምና የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት ምርኩዝ የሆኑት የፈረንሳይ ምጣኔ ሐብት አገር በቀል በሆኑ ተተናኳሽ ባለስልጥናትና ጋዜጦች መሰናክል ይሆኑበታል የሚል ስጋት አለ። በተለይ የዘረኛነት ወሬን የሚያናፍሱ ጋዜጦች ህዝባዊ መረጋጋት እንዳይኖር አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው።የፈረንሳይ የህዝብ ብዛት 67 ሚሊዮን ተጠግቷል።ከዚህ ውስጥ 11% (6 ሚሊዮን) የሚሆነው ሙስሊም ነው።ፈረንሳይ በነበራት የቅኝ ገዢነት መስፋፋት ሳቢያ ሙስሊሞች በሚበዙባቸው የሰሜን አፍሪካ አገራት ማለትም ሞሮኮ፣አልጄሪያና ቱንዝያን ገዝታለች።በተጨማሪም በምእራብ፣በኢኳቶሪያልና በምስራቅ አፍሪካ በቅኝ ገዥነት የቆየች ሲሆን ኤስያ ውስጥም ሊባኖስ፣ሶሪያና ኢንዶኔዥያን ያማከለ አገዛዝ ነበራት። የፈረንሳይ ልጥጥ የቅኝ አገዛዝ ግስጋሴ የተለያዩ መስሊሞች በግድም ሆነ በውድ በአገሪቱ ውስጥ እንዲሰፍሩ ምክንያት ሆኗል።


ዛሬም ሰለጠንኩ ከሚለው ማህበረሰብ ውስጥ የቅኝ አገዛዝ ዘመን እሳቤ አልጠፋም። በነጭ ዘረኞች ጭቆና ይደርስብናል የሚሉትን አፍሪካውያንና አረብ ፈረንሳዊያንን እሮሮ መንግስት ከመስማት ይልቅ ለከት ያጣ የግራ ዘመምን ፍልስፍና አራማጅ የሆኑ ግለሰቦችና ቡድኖች የነብዩ መሐመድን ካርቱን የመሳል መብትን ከአገር የምጣኔ ሐብት፣ የዲፕሎማሲ ግንኙነቶችና ብሔራዊ ደህንነት ጋር እኩል ሆነው ባህላዊ መገለጫ መሆናቸው ፓሪስን ጥርስ ያስገባ ክስተት እየሆነ ነው።


ኢማኑኤል ማክሮን እናት የምትሆናቸውን ቀዳማዊት እመቤት ይዘው መንግስቱን ሲረከቡ ወጣት መሪ በመምጣቱ ተሐድሶአዊ ለውጥ ይኖራል የሚል ተስፋ ለምልሞ ነበር።ማክሮን ግን የፈረንሳይን የዛገ የዘረኝነት ተሞክሮ ከማስወገድ ዝገቱን የሚወለውሉ ይመስላል።የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽምና ማክሮን በመላው አለም ላይ ባሉ 1.8 ቢሊዮን ሙስሊሞች ጋር አገራቸውን የሚያጋጭ ንግግር ማድረጋቸው ፖለቲካዊ ትርፍ የሚያስገኝ ቢመስልም የተዛባ ስሌትን እያራመዱ ነው የሚሉ ፊርማቸውን በሰነድ ላይ ያኖሩ 100 ምሁራን በሐሳብ ልእልና እየሞገቷቸው ነው።


«ስልታዊ ዘረኛነትን ከመታገል ይልቅ ፈረንሳይ ኢስላማዊ ተሐድሶን ማድረግ ትሻለች» በማለት ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል። ፈረንሳይ አክራሪነትን ለመከላከል ለሙስሊም ተቋማት ከውጭ የሚመጣን እርዳታ ትቆጣጠራለች፤በፈረንሳይ መስጊዶች ውስጥ የሚያሰግዱ ኢማሞች የመንግስት ስልጠናን በመውሰድ ፈቃድ ይሰጣቸዋል፤እስከ ሐምሳ የሚደርሱ የሙስሊም ተቋማት የመንግስትን መመሪያ በተገቢው መልኩ የማይፈጽሙ ከሆነ በአገር ውስጥ ጉዳይ ሚ/ር ፈቃዳቸው ይነጠቃል ሲል የፈረንሳይ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚ/ር ማስጠንቀቁን ዋሽንግተን ፖስት አስነብቧል።ይህ ፈረንሳይ ከሙስሊም ዜጎቿና ከሙስሊም አገራት ጋር ያላትን ፍጥጫ የሚያረግብ አይደለም። ሙስሊም ወጣቶቿን አዳኝ በሆኑ የአክራሪዎች ፍልስፍና የበለጠ ሰለባ ያደርጋቸዋል የሚል የምሁራን እሮሮ ቢሰማም ፈረንሳይ ጆሮ ዳባ ልበስ ብላለች።


ሳሙኤል ፓቲ የተባሉት መምህር ለተማሪዎቻቸው የነብዩ መሐመድ ካርቱን ስእል በማሳየት «ማየት የማይፈልግ ፊቱን ማዞር ይችላል» ማለታቸው በሙስሊም ተማሪዎቻቸው ዘንድ ቁጣን በመቀስቀሱ ከቸችኒያ በመጣ የ18 አመት ወጣት ተገደሉ የሚል ዘገባ አለም አዳርሷል።ጉዳዩ በፈረንሳይ ሴኩላሮች ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል።የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ነገሩን ከማበራረድና አገራዊ መፍትሔን ከመሻት ይልቅ «በመላው አለም ላይ ቀውስ የገጠመው ሐይማኖት» ሲሉ ኢስላምን ተዛልፈዋል።የእምነቱ ተከታዮችን ግድፈት ሳይሆን ሐይማኖቱን በደምሳሳው ፕሬዝዳንቱ መዛለፋቸው በመላው አለም ላይ ባሉ ሙስሊሞች ዘንድ የማይረሳ መዳፈር ተደርጎ ተመዝግቧል።የቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤድሮጋን የማክሮንን ንግግርን ከማውገዝ አልፈው የፈረንሳይና ቁሳቁስና ሸቀጣ ሸቀጥ ላይ የግብይይት ተአቅቦ እንዲኖር ተጣሩ።የፓኪስታን ፓርላማ የፕሬዝዳንቱን ንግግር በመቃወም ድምጹን ሰጠ።የተለያዩ የአረብና የሙስሊም አገራት በፈረንሳይ ቁሳቁሶችና ሸቀጥ ላይ ተአቅቦ ከማድረግም አልፈው የተቃውሞ ሰልፎችን አካሒደዋል።


የቱርክን መንግስት የሚደግፈው ዴይሊ ሳባህ የተባለው ጋዜጣ የቱርኩን የዜና ወኪል አናዶሉን ዋቢ አድርጎ ባወጣው መረጃ መሰረት ወደ ሙስሊም አገራት ሸቀጦችን የምትልከዋና የምታስመጣዋ ፈረንሳይ 100 ቢሊየን ዶላር ንግድን አሲዛ ነው ቁማር ውስጥ የገባቸው በማለት ያትታል።በዘገባው መሰረት ፈረንሳይ ባለፈው አመት ብቻ 45.8 ቢሊየን ዶላር ሸቀጣ ሸቀጦችንና ቁሳቁሶችን ሙስሊሞች ወደ ሚበዙባቸው አገራት ስትልክ ከነዚሁ አገራት የ58 ቢሊየን ዶላር ግዢን በማከናወን እቃዎችን አስገብታለች።በፈረንሳይ ላየ የተጀመረው የተአቅቦ ምን ያህል ይዘልቃል የሚለው በሒደት የሚታይ ክስተት ነው።


«ማክሮን እስላማዊ አብዮት ማከናወን ይፈልጋሉ» በማለት የጻፈው ፎረን ፖሊሲ በ2017 የተመረጡት ፕሬዝዳንት ማክሮን በ2022 ለሚጠብቃቸው ምርጫ የግራ ክንፉን ድምጽ ሰጪ ሳይሆን የቀኙን ለመሸመት እያደቡ መሆኑን አስነብቧል። ወደ ግራና ወደ ቀኝ ሳይዘነብሉ መሐል ላይ በመሆን ለስልጣን የበቁት ማክሮን በስደተኛና «ሙስሊም-ጠልነት» የሚታወቁ ፖለቲከኞችን በካቢኔአቸው ውስጥ በማካተት የምርጫ ዘመቻ የጀመሩ መሆናቸውን ጠቋሚ ዘገባዎች እየወጡ ነው።


የፈረንሳይ የስራ አጥ ቁጥር 10% ለመድረስ በመቃረቡ ፓሪስ ላይ ያጠለለ ቀውስ አለ።ጥቁርና አረብ የፈረንሳይ ዜጎች ስልታዊና መዋቅራዊ በሆነ ዘረኝንት ሲታመሱ፣ሒጃብን በማስቀረት፣ የነብዩን ካርቱን በመሳል የመተናኮስ ተሞክሮው ቀጥሏል።ፈረንሳይ በመናገር ነጻነነት ስም የጥላቻን አብዮት እያቀጣጠለች ነው የሚል ክስ ይቀርብባታል።ፈረንሳይ ውስጥ በሴኩላር ስም ሐይማኖትን የሚያራክስ ጽንፈኝነት ለከት አጥቷል የሚል እሮሮ እየተሰማ ነው።ፓሪስ ሙስሊምና ጥቁር ወጣቶችን ለግጭቶች ማመካኛ አርጋ ትቀጥላለችን? ወይስ የከሸፈውን ፖሊሲዋን ታሻሽላለሽ? ጊዜ መስታወት ነውና በጊዜ ሒደት ውስጥ የሚታይ እውነታ ይሆናል።


ልብ ያለው ልብ ይበል!

50 views0 comments
bottom of page