top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የመለወጥ ጉዳይ (ቡርሐን አዲስ)


የድሃና፣የሀብታም፣ የአዋቂና ወግ አጥባቂ፣ የመሪና ተመሪ፣ የአማኝና ከሃዲ ልዩነት ያለው ከእያንዳንዱ ሰው ነጻ ፈቃድ ውስጥ መሆኑ አይጠፋንም። ከሀብታም ቤተሰብ የተወለደ ሀብታም ሆኖ ሁሌ ይቀጥላል ማለት አይደለም። ቢቀጥል እንኳ የሀብትን ፍሬ-ነገር ለማስተዋል ከሌጣው አዉድማ መጀመሩ ነው ወሳኝ የሚሆነው።


እያንዳንዱ ሰው ምንም ሳይኖረው ከባዶ ሜዳ እንዲጀምር ቢደረግ እያንዳንዱ ሰው በሚፈጥረው ብርቱ ጥረት ልዩነት ያመታል። እንደ አትሌቲክስ ሩጫ ማየት ነው። ተመሳሳይ አቋም እንዳላቸው የታመኑ ሯጮች ከእኩል መነሻ እኩል ጊዜ ላይ ዉድድር እንዲጀምሩ ይሆናል። ከዚያ አሸናፊው የሚወሰነው በሚኖረው የግል በርታትና ኪሂሎቱ ላይ ነው። የተለየ መተት ወይም ተዓምር ስላለው ነው ብለን አናስብም።


እንደ ሀገርም ካሰብን ተመሳሳይ ነው። ሀገራት እንዴት እንዳደጉ ለታሪክ ቀና ስሜት ያለው የምሳሌ ተማሪ ይረደዋል። ብዙ ትጋት፣ ብዙ ጥረትና ተግባር ላይ የጸኑ የትውልድ አካሎች እስካሉ ሰፊ ሀገር ይለወጣል።


የሶቪየት ህብረትን አነሳስ ጨረፍ አድርገን ብናነሳ ማለፊያ ይሆናል። ስታሊን በጨካኝ አረመኔ አምባገነንነት ይነሳል። ብዙ ሚሊዮኖች እንዲያልፉ ምክኒያት መሆኑን በማንሳት አሉታውን አብዝተው የሚተርኩት ብዙዎቻችን ላይ አሳማኝ ተጽዕኖ ፈጥረዋል። እስከዛሬም ይኼው አሉታ ጎልቶ እናያለን።


ይሁን እንጂ አንድ የማይነገር እውነት መኖሩን መታዘብ ተገቢ ነው። ራሺያ በዛሩ ስርኣት ስር ሳለች ክፉኛ የድህነት ወጨፎ ያበረዳት ግዛተ-አጼ ነበረች። በ1902 ታላቁ ደራሲ አንቷን ቸኮቭ ዛሩን ማየት ችሎ ነበርና በጣም ባጭር ጊዜ ውስጥ ሀገሩ ወደ ከፋ አመፅና ትርምስ ልትገባ እንደምትችል የተሰማውን ፍርሃት ገልጾለት ነበር። የደራሲው ትንቢት እንዲፈጸም 15 አመታት ብቻ ነበር የጠበቀው። ከባድ ነውጥና ለውጥ ታየ… የቦልሸቪኮች አብዮት የዛሩን መንግስት ገርስሶ አዲስ ማህበረሰብ መስራት ጀመረ።


የሌኒንን ህልፈት ተከትሎ ጆሴፍ ስታሊን ወደ ስልጣን መጣ። እናም በስልጣን ዘመኑ ከአለም ድሆች ሰፈር ገብታ የነበረችን ግዛተ-አጼ ወደ አለም አቀፍ ኃያል የኢንደስትሪ ስልጣኔ ማሳደግ መቻሉን ልብ ይሏል። ስታሊን የወሰዳቸው እርምጃዎች ለበርካቶች ህልፈት ምክኒያት መሆኑ ሁሌም ጉዳቱን የሚያሳብቅበት መራር ጎኑ ቢሆንም ዛሬም ድረስ በአለም የተፈራች ሀገር መፍጠር መቻሉ ግን አይካድም።


አምባገነን ምሳሌ እንዴት ይሆናል? ብሎ የሚያስብ አይጠፋም። አንዳንዴ ነጻነቱም ኖሮ ከሚያማርጥ ስርዓት ቆንጠጥ በሚያደርግ ገዢ መነቃነቁ አይከፋም። ጭቆና በራሱ የሚያነቃ ነገር አለው። እንደሀገር ስርዓትና መልክ ያለው የመንግስት ኪነት ሳይኖረን ቁርጠኝነት ያለው የሀገር መንፈስ የማንዘራባቸው ሁኔታዎች አሉ።


የጎዝላቪያን መለስ ብሎ እንደምሳሌ መውሰድ በቂ ነው። ጠንካራና ቁንጥጫው ፍቱን መላ የቸረላት መሪ ነበራት። ቲቶ። በስልጣን ሳለ ከተራ ቀጠናነት ወደ አለም አቀፍ ታዋቂና ባለሚና ሀገር አድርጓት እንደነበር ይታወቃል። የእርሱን ህልፈት ተከትሎ ግን… አደገኛ የጎሰኝነት ቃር አጠቃት… ስትፈጥንም… እርስ በርስ ተባልታ ወደ ስድስት ሀገርነት አነሰች።


ለኢትዮጵያ የሚያስተምርምሳሌ አለ…ው።

የዲሞክራሲ ተከታይ ነኝ። ግን በብይን ፍልስፍናዉ ላይ ግዙፍ ጥያቄ አለኝ። የፕሌቶ ሪፐብሊክ በዚህ ዘመን እውን ነው ወይ? ስል ለሚሰማኝ ጥያቄ የሚገባኝ መልስ አሉታ ነው። በትክክል ኢትዮጵያን የሚሰራ የዲሞክራሲ ፍልስፍና አይደለም ያለን።


የተራቀቁ የለውጥሀሳብ መርዞች ከዚህም ከዚያም በሚወነጫጨፍበት የቴክኖሎጂ ወፈፌ ዘመን የዲሞክራሲን ፍልስፍና ከልሶ መገምግም ሳንችል ቃሉን ብናስተጋባው… የጥልቀት ክፍተት እንዳለብን እየመሰከርን እንደሆነ ነው የማምነው።


ለውጥ… ጠልቆ መረዳትን ይፈልጋል። በትክክል ያልገባንን ጉዳይ ብንከተለው… ካሰብነው የለውጥ ደጅ አንደርስም። መንገዱ ላይ እንቆማለን። ወይም እንወድቃለን። ወደምን ዳርቻ ለመድረስ እንዳሰብን በቅጡ ሳይገባን የምንጀምረው የለውጥ ጉዞ… ግምታዊ አልያም ግብታዊ ይሆናል። እናም አንዱ ማስተዋል የለውጥን ሁለንተናዊ ምንነት እስክናዉቀው ንድፈ-ሀሳቡን መረዳት ነው። ሳይገባን የምንጀምረው ጉዞ ብዙ አያራምደንም።


እንደሀገር ትልቅ ለውጥ መፍጠር እንደሚቻል እርግጠኛ የሚያደርግ ጉዳይ ካለ ማናችንም ብናልፍ ከጠንካራ እሳቤ ነው። ሞትና ጉዳትን ሳያስከትሉ፣ ወይም ፍጹም አኮስሶ… የላቀ ለውጥ መፍጠር የሚያስችሉ የጥበብ ብርሃኖችን ማሰብ ደግሞ ታሪካዊ ምሳሌነትን ወደ ብኩርና የሚያሳድግም ይሆናል።


የማንዴላና የጋንዲ የለውጥ ፈጣሪነት ቅኝት ዜማ በደልን በይቅርታ፣ ጦርነትን ደግሞ በሰላም ድል የማድረግ ዝማሬ እንደነበረው እናያለን። ውስጥን አብዝቶ ከማበልጸግ የሞራል ሂማሊያ የሚወለድ አቅም ነው። እልፍ ምሳሌዎች አሉን። ልንማር ፈቃዱ ካለን። አስደናቂና የተለየ ተዓምራዊ ለውጥ መፍጠር የሚያስችል አቅም እንፍጠር ካልን በትክክል እንችላለን።


አሁንላይ ምን አይነት ለውጥ እናስብ? ካልን ምላሹ ይኼው ነው። ከመማር፣ ከማስተዋልና ከማሰላሰል በሚወለድ ብይን ሰው ትልቅ ሰው የሚሆነው በሌሎች ልብ ውስጥ መቆየት እስከቻለ ብቻ መሆኑን እስክናምን በሀሳቦች መብሰልሰል ግድ ነው። ለራስ ብቻ ወይም ወደ ራስ ብቻ በሚመለከት አስተሳሰብ እንኳን ሀገር ራስንም መለወጥ አያስኬድም።


የጆንኤፍ ኬኔዲ ወንድም የነበረውን ቦብ ኬኔዲ እምብዛም አናዉቀው ይሆናል። አሜሪካ ያጣችው ሁነኛ መሪ ነበር። ዛሬ ድረስ የሚቆጩበት ሩቅ ቀድሞ የተራመደ አሳቢ ነበር። ለመሪነት እንቅስቃሴ ጀመረ። በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝም ሰው መሆን ችሎ ነበር። ጥቁሮችና ከዘረኛ ነጮች ዉጪ የነበሩ ሁሉ በፍቅር ያመኑትና ያከበሩትም እጩ ተወዳዳሪ ነበር።


አሜሪካነትን ከመስራችአባቶቻቸው እነዋሽንግተን በኋላ በአንድነት ያገናኘ ወጣትም ሆኖ ነበር። ደግ አይበረክትም እንዲሉ ግን በአጭር ተቀጨ..። የሁሉንም ልብ የሰበረ መርዶም ሆኖ አለፈ።


ጥሩ አጋጣሚዎች ይኖራሉ። በጥንቃቄ ተንከባክበን ካልጠበቅናቸው… ድንገት በሚወነጨፍ ሰንጣሪ ሊከስም ይችላል። ዳግም አንመልሰውም። የአለም ልዑል የሆነችው አሜሪካ ከዚያ ተወዳጅ እጩዋ ቦብ ኬኔዲ (1968) እስካሁን ሁሉን ማቀፍና ለሁሉ መሆን የቻለ መሪ አላገኘችም።


በኢትዮጵያም ውስጥ አጋጣሚዎች ፈጥነው ይከሽፋሉ። ባለፉት ሀምሳ አመታት የፈነጠቁ የአብዮት ንጋቶች ነበሩ። የስልሳ ስድስቱ ለውጥ፣ የ83ቱ ለውጥ፣ የ97ቱ ፍካት፣ እና የአዲሱ መንግስት ማለዳ እንደጥሩ አጋጣሚ የታዩ ለትልቅ አብዮት የሚያበቁ ወሳኝ አጋጣሚዎች ነበሩ።


ሆኖም ሁሉንም በትክክል አልተጠቀምንባቸውም። ለምን? በተደጋጋሚ መሳሳት የምን ምልክት እንደሆነ መገምገም ይኖርብናል። አጋጣሚዎችን በትክክል የመጠቀም አዲስ የአተያይ ባህል መውለድ አለብን። ችግራችን አጋጣሚዎችን መፍጠር አይደለም… በትክክል መጠቀም አለመቻል ነው።


ስለዚህ እንደለውጥ ዋና መፍትሄ የማስበው… የምንፈጥራቸውን አጋጣሚዎች በዘላቂነት ፋይዳዊ ስለማድረግ አፅንኦት መስጠት እንዳለብን ነው።


ቡርሐን አዲስ

26 views0 comments
bottom of page