top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የመስቃን ወረዳ ፖሊስ እና ፍርድ ቤት ምን እየሰሩ ነው?


የመስቃን ወረዳ ፖሊስ እና ፍርድ ቤት ምን እየሰሩ ነው ? በሚል የተለያዩ በደል የደረሰባቸው የጉዳይ ባለቤቶችን አነጋግረናል ። የመስቃን ወረዳ ፖሊስ ፅ/ቤት ይባል እንጂ የለም የሚባልበት ደረጃ ላይ ደርሷል ቢባል ማጋነን አይሆንም ይላሉ ነዋሪዎቹ። ለምሳሌ በትንሹ አንድ ታሳሪ ማቆያ ውስጥ መቆየት ያለበት 24 ሰአት ቢሆንም ነገር ግን በፖሊስ ጣቢያው ከአንድ ወር እስከ 6 ወር ታሳሪው እንዲቆይ ይገደዳል። በመሰረቱ የመስቃን ወረዳ ለሁለት ከተከፈለ ጀምሮ ስራ እየተሰራ አይደለም የሚለው የአብዛኛው ነዋሪ አመለካከት እንደሆነ ባሰባሰብነው መረጃ ለማወቅ ችለናል።

መስቃን ወረዳ ፖሊስ ፅ/ቤት የመጡትን ባለጉዳዮች ሁኔታቸውን በማየት ሀብት ካላቸው ፍትህን አዛብቶ በማቅረብ ዝግጁ መሆኑን ማሳያዎች አሉ ይላሉ ነዋሪዎቹ። ፍትህ በራሱ አቅጣጫ የመሳትም የመያዝም አቅሙ በሰዎች እጅ ነው ። የመስቃን ማህበረሰብ ከህግ ይልቅ በሀገር ሽማግሌ ቢዳኝ የተሻለ ነው ብሎ ማሰብ ጀምሯል። በሽማግሌ መዳኘቱ እንግልት ከመቀነስ አልፎ ላልተገባ ወጪ አይዳረግም ። ህግም ቢሆን የራሱ ጥሩ ጎን አለው ። ግን የመስቃን ወረዳ ፖሊስ በራሳቸው ጊዜ ህግ ያወጡ ይመስል ሀብታም የማይታሰርበት ሆኖ ቀጥሏል። ፖሊስ የወጣው ከማህበረሰቡ ቢሆንም የተሻለ ኑሮ ለመኖር በማሰብ ፍትህን በገንዘብ የማዛባቱ ስውር ተግባር መቅረት እንዳለበት በሁሉም ዘንድ ይታመናል።


ውድ አንባቢያን በመቀጠል የተለያዩ ባለ ጉዳዮች ጉዳያቸው ከፍርድ ቤት ጋር ተያያዥ የሆነውን ያነጋገርን ሲሆን ባለጉዳዮቹ ለቃለ መጠይቁ ከስማቸው ውጪ ጉዳያቸው ብቻ እንዲገለፅ ፍቃደኛ ሆነዋል ።


1ኛ ባለጉዳይ

በመስቃን ወረዳ በየተቦን ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። የሁለት ወንድ ልጅና የሶስት (3) ሴት ልጆች እናት ሆነው የኖሩበት የተቦን ቀበሌ የነበራቸውን የገጠር የእርሻ መሬት ባላወቁበት ሁኔታ የመጀመሪያ ወንድ ልጃቸው በ1997 ዓ.ም የመሬቱን ልኬት አስለክቶ በስሙ አስመዝግቦ ሲያበቃ ሁለተኛው ልጅ ሌላ ቦታ ሄዶ ስራ ይሰራ ስለነበር የእናቱን ቤት ለማሳደስ በመጣ ጊዜ መሬቱ የኔ ነው አንተም እናትህም ምን አላቹ በማለት እስከ መካሰስ ድረስ በመድረሱ የመስቃን ወረዳ ፍ/ቤት በይገባኛል ክስ በመመስረት እናት መከራከር ይጀምራሉ። ክርክሩ ከመሬት አስተዳደር ከቀበሌ ከመሬት ለኪ ኮሚቴዎች የመስቃን ወረዳ ፍ/ቤት ደብዳቤ ውጪ በማድረግ ልኮላቸዋል። የተላከው የደብዳቤ ምላሽ በመሰብሰብ ምላሽ በመጠበቅ ለረጅም ጊዜ ተመላልሰዋል። በፍርድ ቤቱ ሲጠበቅ የነበረው የሰነድ መረጃ ከመጣ በኋላ የሰው መረጃ በማስፈለጉ ተመሰክሮ ያስመሰከረው የሰው ምስክር የሴትዮዋ ልጅ ነው ። በማለት ቃላቸውን አስቀመጡ። ፍ/ቤቱ የግራ እና የቀኝ በመስማት ሴትዮዋን ይዞታ አልባ በማድረግ በስተርጅና እና በመጦሪያ ጊዜያቸው የሰው እጅ እንዲያዩ ውሳኔ ተላለፈባቸው።


2ኛ ባለጉዳይ

በመስቃን ወረዳ በጆሌ ቀበሌ ቆጬ ገበያ ነዋሪ ናቸው ። ከዛ በፊት በገጠማቸው ጊዜያዊ ህመም ለመታከም ገንዘብ ስላልነበራቸው ከነበራቸው የመሬት ይዞታ በመቀነስ መሬቱን ኮንትራት ያሲዙና ወደተሻለ የህክምና ቦታ ይሄዳሉ። እንደነገሩን በሄዱበት የህክምና ቦታ ጤናቸው በመመለሱ ዘወትር የሚሰሩትን የግብርና ስራ ለመስራት በማሰብ ከአመታት ቆይታ በኋላ ያስያዙትን መሬት ገንዘብ ለመመለስ ይሄዳሉ ። መሬቱን በኮንትራት ይዞት የነበረው ግለሰብ መሬቱን በግዢ እንጂ በኪራይ እንደላልወሰደ ምላሽ ይሰጣል። በመሰረቱ በህጉ መሰረት መሬት መሸጥም ሆነ መግዛት በህግ የተከለከለ ነው ተብሎ ቢነገረውም በእጅ አዙር ይሸጣል ምላሽ የሰጠ ሲሆን ጉዳይ የህግ እገዛ ያስፈልገው ስለነበር ተበዳይ የክስ ሂደቶቹን ካከናወኑ በዃላ እንደማንኛውም ባለጉዳይ ጉዳያቸውን ይዘው መስቃን ወረዳ ፍ/ቤት ይገኛሉ ። የክሱን ጭብጥ ይዘው መጥሪያ በመቀበል መሬቱን በኮንትራት የያዘው ሰው ዘንድ ያደርሳሉ። ተከሳሽ በደረሰው መጥሪያ መሰረት በቀጠሮ ቀን ከፍርድ ቤት የተገኘ ቢሆንም ጉዳዩ እልባት ሳይበጅለት ለሁለት አመት ያህል በመስቃን ወረዳ ፍርድ ቤት ሲንከባለል ቆይቶ መሬቱን በኮንትራት ለያዘው ሰው ይወሰናል ። ተበዳይ ይግባኝ በመጠየቅ ደረጃ በደረጃ ወደሚገኙ ፍ/ቤቶች ይሄዳሉ ። በመስቃን ወረዳ የተወሰነው ውሳኔ የትም ሳይሻር በፌደራል ሰበር ሰሚ ፍ/ቤት ለመጀመሪያ ባለ መሬት የተወሰነላቸው ቢሆንም የመስቃን ወረዳ ፍ/ቤት አፈፃፀሙን እንዲፈፅም ቢፃፍለትም እንደተበዳይ ከሆነ ከዛ በፊት ለተከሳሽ በመወገን የወሰነውን ውሳኔን ዛሬ ምን ብሎ አፈፃፀም ይፈፅማል የሚል ነበር ። በተጨማሪም ሌላ አንድ አመት የፈጀ መንከራተቱ ቀጥሏል ። እንደ ተበዳይ አቤቱታ ከሆነ መስቃን ወረዳ ፍርድ በግለሰባዊ ጥቅም፣ ዝምድና ወይም ሃብታም እና ደህና ለበሰው የማድላቱን ተግባር ማቆም አለበት። በህግ ፊት ሁሉም ዜጎች እኩል ናቸው።


3ተኛ ባለጉዳይ

በመስቃን ወረዳ በገተማ ቀበሌ ባላቸው የይዞታ ይገባኛል ክርክርን የተመለከተ ነው ። እንደሚሉት ተወልጄ ያደኩት እዚሁ ቀበሌ ነው ። አባቴ ብዙ ልጆችን ወልደዋል ። ልጆቹም እናታቸው የተለያዩ ናቸው ። በዚህ ቀበሌ የወላጅ እናቴ ይዞታ አለ ። እኔ በትዳር ምክንያት ከዚህ አካባቢ ርቄ ነው የምኖረው ። በእናቴ ስም የግብር ካርኒ በቡታጅራ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በመሄድ ወራሽነቴን አረጋግጬ በእጄ ይዣለሁኝ ። የእናቴ ይዞታ ለማስለካት ስሄድ የኔ አለመሆኑ በአባቴ ልጆች ይነግረኛል ። እኔ ደግሞ የእናቴ መሆኑ በእጄ ያለው የመሬት የግብር ካርኒ በመያዝ ህግ ወዳለበት ፍ/ቤት በመሄድ ሁከት ይወገድልኝ በማለት ለፍ/ቤት አቀረብኩኝ ።ፍ/ቤት መርምሮ ከወረቀት መረጃ በተጨማሪ የሰው ምስክር ያስፈልጋል ስለተባልኩ ምስክሮቹን ይዤ ቀርቤአለሁ። ምስክሮች ለ20 ጊዜ ያህል ከፍርድ ቤት ይዤ የቀረብኩ ቢሆንም ለጉዳዩ እልባት ሊበጅለት አልተቻለም። ጠበቃ ለመግዝት የአቅም ውስንነት ስላለብኝ እኔው እራሴ ፍርድ ቤት ቆሜ ለማስረዳት እሞክራለሁ ግን ተሰላችቼ ክሱን እንድተው በሚያስመሰል መልኩ ፍርድ ቤት መበቴን ነፍጎኝ ያለምንም ውሳኔ በቀጠሮ እያመላለሰኝ ይገኛል። እውነት ነው ፍርድ ቤት ውስጥ ዘመድ የለኝም። ገንዘብም እንደዛው ። መስቃን ወረዳ ውስጥ ፍትህ አለ ማለት እሳት ላይ ውሃ ጥዶ ወተት እንደመጠበቅ ሆኖብኝ የገጠመኝ የቀን ጨለማ ነው በማለት አቤቱታቸውን አሰምተዋል።


የዛሬው ዳሰሳ ይህን ይመስል ነበር ። በቀጣይ በሌላ አጀንዳዎች እስክንገናኝ ቸር እንሰንብት።


ሻኪር አህመድ

መስቃን ሚድያ ኔትዎርክ

ቡታጅራ

48 views0 comments
bottom of page