top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

የማያለቅስ ልጅ እራት የለውም (ታዬ ተስፋዬ ስሜ)


የማያለቅስ ልጅ እራት የለውም (ታዬ ተስፋዬ ስሜ)

"ስለመቸገርህ መንግስት የሚያዉቀው በካርድህ ስትጠቁመው እንጂ ስትሸልመው አይደለም"

ቅጽ 2

የወልቂጤ ዩንቭርሲቲ ለሁሉም አካባቢ ፍትሃዊ የስራ አድል መፍጠር አለመቻል

የወልቂጤ ዩንቭርሲቲም የስራ አድል ፈጠራ ስንመለከት በትምህርት ሚኒስትር ከሚመደበዉ /መምህራን ቅጥር ዉጪ በዞኑ ከሚገኙ ማህበረሰብ ክፍል በአስተዳደሪያዊ ዘርፎች ላይ የተቀጠረዉን ከ2500 በላይ የስራ አድል ፈጠራ ሲታይ በየጊዜዉ የሚመደቡት የዩንቭርሲቲዉ ፕሬዝዳንቶች ከመጡበት ወረዳ የራሳችን የሚሉትን ሰዎችን የሚሰበስቡ እንደሆነ አይተናል፡፤ አንዳንዴ ከዘቢዳር በታችም ያሉ የጉራጌ ዞን ህዝቦች ቢሳተፉ የሚለዉን ማሰብ ለምን ይሳነናል፡፡ አሁንስ ስንት ተሳትፈዋል ብንል በማስተማር ዉስጥ ካሉ ጥቂት ልጆች በቀር ምንም አልተሳተፉም ማለት ይቻላል ፡፡

ሌላዉ ዩንቭርሲቲዉ በየአመቱ ከመንግስት ከሚመደብለትና ኢንቭስት ከሚያደርገዉ ከ1 ቢሊየን ብር በላይ በጀት ዉስጥ በኮንስትራክሽን ዘርፍ በማቴሪያል አቅርቦት በግብርና ምርቶች በምግብ እህልና የእርድ እንሰሳት አትክልትና ፍራፍሬና በመሳሰሉት እና በተለያዩ ዘርፎች የተደራጁ ማህበራትና ተቋራጮች እና ግለሰብ ኮንትራክተሮች ላለፉት ዓመታት በሞኖፖሊ የተያዘና አብሮነትን የሚክድ ተግባር ነዉ፡፡

ለዘመናት የተጠየቀዉና ምላሽ ያጣዉ የቡታጅራ ካንፓስ ጉዳይ

በመጀመሪያ ካምፓስ ቢከፈት ምን ጥቅም ይኖረዋል ብለን ከጠየቅን ህብረተሰቡ ከትንሹ በጥበቃ በጽዳት በአገልገሎት በምግብ ማብሰል በሹፍርና እና በመሳሰሉት በመቀጠር የስራ አድል ይፈጠራል፡፤ የተሻለ ትምህርት በዝግጅት ያላቸዉ ደግሞ ከማስተማር ዉጪ ባሉ በተለያዩ ክፍሎች ዉስጥ በስፋት ተቀጥረዉ እንዲሰሩ እድል ይፈጥራል፡፤ በግንባታና በመሳሉት ዘርፎች የተደራጁ ማህበራት ደግሞ ኮንስትራክሽን ስራ ላይ እንዲሳተፉ አድል ይፈጥራል፡፤ ለነጋዴዉ የአላቂ እቃ አቅርቦትና በአገልግሎት ዘርፉ በስፋት ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ፡፤ አርሶ አደሩ ደግሞ በግብርና ምርቶች በእህል በአትክልት በየእርድ እንሰሰሳትን በማቅረብ መጠቀም ይቻላል፤፤ በከተማዉ ያሉ ከትንሽ አስከ ትልቅ ምግብ ቤቶች ሬስቶራንቶች ለተማሪዎችና መምህራን አገልግሎት በመስጠት ገቢ እንዲያገኙ ያደርጋል፤፤ በቂ ስራ ያላገኙ ባንኮች ተጨማሪ ተገልጋይ ማግኘት ይችላሉ፤ ዋናዉና ትልቁ ጉዳይ ደግሞ ትህርታቸዉን ማሻሻል እየፈለጉ የቀሩ በርካታ ወጣቶችና ስራ ያላቸዉ የመንግስትና የግል ተቀጣሪዎች በአጠገባቸዉ ካምፓስ መኖሩ በቀላሉ እንዲማሩ እድል ይፈጥራል፡፤ በአጠቃላይ ከላይ ያልጠቀስኳቸዉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅሞችን ማግኘት ያስችላል፡፤ታዲያ ለምን አድሉ ተከለከልን የሚለዉን ፍርዱን ለናንተ መተዉና ካምፓሱን ማን እንደከለከለን እንደሚከተለዉ አቀርበዋለሁ።

በ2002 ዓ/ም ሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር የጉራጌ ማህበረሰብን ወልቂጤ ላይ መጥተዉ ካወያዩ በዋላ የወልቂጤ ዩንቭርሲቲን መሰረት ድንጋይ አስቀምጠዉ የዝዋይ ቡታጅራ ጉብሬ አስፓልት መንገድ ቃል ገብተዉ ሄደዋል።

በዚህ ዉይይት ላይ ከተነሱ በርካታ ሀሳቦች አንዱ የቡታጅራዋ ወ/ሮ ዘይቱና አህመድ አድል በመውሰድ የወልቂጤ ዩንቭርሲቲ ሲፈቀድ የእህት ከተማ ቡታጅራም ካምፓስ እንዲከፈትልን ስትል ጥያቄዋን አንስታ ጠ/ሚ/ሩ መለስ ዜናዊ ጥሩ ምላሽ ሰጧት፡፤ በዚህም ዓመት ይህንን ተስፋ ተይዞ ምርጫ 2002 ተደረገ 99 ፕርሰንት ደኢህዴን አሸነፈ። ከዛ በመቀጠል ይህ የካምፓስ ጥያቄ በ2004 በተደጋጋሚ በማህበረሰቡም በአመራሩም ሲነሳ በወቅቱ የዩንቭረስቲዉ የቦርድ ሰብሳቢ ለነበሩት መኩሪያ ሃይሌ ጥያቄዉ ተነስቶላቸዉ ሲመልሱ አሁን ወልቂጤ ያለዉ ዩንቭርሲቲዉ በደንብ አልተደራጀም ሌላ ካምፓስ መክፈት አይቻልም አሉ፡፡

በድጋሚ 2007 ምርጫ ከመድረሱ በፊት የዝዋይ ቡታጅራ ጉብሬ መንገድ ምረቃ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ በመስቃን ወረዳ አዳራሽ ላይ በአቶ ፍቀዱ አሴሮና አንዲት እናታችን አማካኝነት የቡታጅራ ካምፓስ የቡታጅራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅና የቡታጅራ ሆስፒታል አድገት በተመለከተ ጥያቄዉ ተነስቶላቸዉ ምላሽ ሲሰጡ ቡታጅራ ካምፓስ ሳይሆን እራሱን የቻለ ዩንቭሲቲ የሚገባዉ ከተማ ነዉ ካምፓስማ በጣም ቀላል ጥያቄ ነዉ አጠገቤ ያለዉ ደሴ ዳልኬ/ የቀድሞው ደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ማለት ነው/እና ከፊት ወንበር ተቀምጦ የነበረዉን የዩንቭርሲቲዉን ቦርድ ሰብሳቢ መኩሪያ ሃይሌን እየጠቆሙ የነሱ ዉሳኔ ብቻ ይበቃዋል ከጥቂት ቀን በኋላ ምላሽ ይሰጣሉ አ። በመቀጠልም ይህንን ዉሳኔ ለማስፈጸም በወቅቱ የዞኑ አስተዳዳሪና የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አማካኝነት ሸብ ረብ ተባለና ቦታ መረጣ ይደረግ ተብሎ ቦታ ተመረጠ፤፤ መሰረተ ድንጋይም ይጣላል ተብሎ ሲጠበቅ ቦርድ ሰብሳቢዉ ካምፓሱ እንዳይከፈት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተወስኗል አይቻልም ብለዉ አረፉ፡፤ ይሁን እንጂ እሳቸዉ እንደዛ ባሉ በጥቂት ወራት ዉስጥ የሃዋሳ ዩንቭርሲቲ አራተኛ ካምፓስ ትንሿ የሲዳማ ከተማ ዳዬ ከተማ ላይ ደሴ ዳልኬና ሽፈራዉ ሽጉጤ የመሰረተ ድገንጋይ አስቀመጡ፡፤ ጅማ ዩንቭርሲቲ አጋሮ ካምፓስ፤ ባህርዳር ዩንቭርሲቲ ፍኖተሰላም ካምፓስ፤ ወላይታ ሶዶ ዩንቭርሲቲ 2 ካምፓስ ቦዲቲና ተርጫ ካምፓስ ከፍቷል፤፤ በእድሜ ትንሹና በ2005 የተመሰረተዉ ዋቸሞ ዩንቭርሲቲ ዱራሜ ካምፓስ ሲከፍት በአጠቃላይ በመኩሪያ ሃይሌ ታግዷል ከተባለ በኋላ በሃገሪቱ ዉስጥ እኔ እንኳን ማዉቃቸዉ ከ25 በላይ ካምፓሶች ተገንበተዉ ተማሪዎችን በመቀበል በማስመረቅ ደረጃ ላይ ደርሰዉ ስታይ የጭቆናዉ ክፋትና ኢ-ሞራላዊነት ያንገበግብሃል፡፡ በቅርቡ ደግሞ የወራቤ ዩንቭርሲቲ በትንሷ ገርቢበር ከተማ ላይ መክፈቱን ስንሰማ እኛ መንግስትን ምን ብንበድል ነዉ ያስብላል፡፤ ታዲያ እንዴት ሁሉ ነገር አንደተሟላለት ህዝብ የምርጫ ወንበር ብቻ ለመንግስት እንስጠዉ ይባላል፡፡


የቡታጅራ ኢንድስሪያል ፓርክ ጉዳይ እና ቀጣይ የሚኖረን የመብት ትግል

የቡታጅራ እንድስትርያል ፓርክ ግንባታ በ2007 ዓ/ም መጨረሻ አካባቢ ከፌድራልና ከክልል የመጡ አካላት ጋር በመሆን እኔና የቡታጅራ የቀድሞ ከንቲባ ከዞኑ አስተዳዳሪና ድርጅት ሃላፊ ጋር የተጠየቅናቸው የመብራት substation ያለው፤ በቂ ሆስፒታል በአቅራቢያው ያለው፤ በቂ የሰው ሃይል ማግኘት የሚቻልበት፤ ከሞጆ ደረቅ ወደብ 150km ራዲየስ የሚገኝ ቦታና፤ 150_300 ሄ/ር መሬት ማቅረብ የሚችል የሚሉ የተጠየቅነውን 5 መስፈርት አሟልተን ነበ። ቦታዉም ድራማ ዊጣና ኢሌ አካባቢ ያሉ ቁጥቋጦና ተራራማ ቦታዎችን መርጠን አሳይተናል መስፈርቱንም አሟልተን ተመርጧል ተብለን ከተነገረንና በሚድያም ከተገለፀ በዋላ ማን ነው የቀለበሰው? ቆይቶስ ዞናችን ላይ የሆነ ቦታ ላይ ተቀየረ ተባለ ያም ተተወና ተሰወረ ። ከ5 አመት በዋላ በቅርቡ ይርጋለም ላይ ግን ተመርቆ አይተነዋል ይሄ ህዝብ ልማቱን የሚነጥቁና የሚያስነጥቁ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የሚሉ ጥቂት ደካማ የጉራጌ ካድሬዎችን አምኖ መቀመጡ ዋጋ አስከፍሎናል ስለዚህ መብታችንን በራሳችን መታግልና ማስፈጸም ይኖርብናልና ከዚህ ምርጫ ጀምረን ጭቆናዉን ማስቆም ይኖርብናል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቡታጅራ ድስትሪክት ወደ ሌላ ቦታ መዛወር ጉዳይና ቀጣይ መታገያችን አጀንዳችን

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሰራዉ አዲስ አደረጃጀት መሰረት የቡታጅራዉ ንግድ ባንክ ወደ ዲስትሪክት እንዲያድግና በስሩ በርካታ ቅርንጫፎችንና በርካታ ከተሞችንና ወረዳዎች አካሎ እንዲሰራ በማሰብ ግዙፍ ህንጻ በከተማዉ እንዲገነባ ተደርጓል፡፤ ብቻም አይደል በባንኪንግ ሲስተም ቡታጅራ የራሱ መለያ ኮድና የሚስተዳድራቸዉ ቅርንጫፎች ተገልጸዉ ይገኛሉ፡፤ ይሁን እንጂ ምክንቱ ባልታወቀ ምክንያት ድንገት አንዲታጠፍና ወደ ሆሳዕና እንዲዛወር ተደርጓል፡፡ ይህንን የመልካም አስተዳድርና እና ኢፍትሃዊነት ማስተካከል የነበረበት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና የጉራጌ ዞን አስተዳድር ቢሆንም እነሱም ጉዳዩን ለከተማዉ አመራርና ነዋሪ በመግፋት ችላ ተብሎዋል፡፤ አድሉ የተነጠቀዉ በዞናችን ሌላ ከተማ ቢሆን እንደተለመደዉ ዞኑ በጩኸትና ሁከት ይታመስ ነበር፡፤ የቡታጅራ አካበቢ ህዝብ ግን እዉነተኛ የሚሟገትለት የጉራጌ ካድሬ በማጣቱ መብቱን አሳልፎ በመስጠት ላይ ይገኛል። ይሁን እንጂ ጉዳዩ በትግል ሊስተካከል እንደሚችል ታሳቢ በማድረግ መንግስት ሲረጋጋ ትግሉን ማቀጣጠል ያስፈልጋል።

በዞኑ የሚድያ ተደራሽነት ላይ ያለዉ ችግር ማን ይፈታዋል

በደቡብ ሬድዮና ቴሌቪዥን ስር ከተደራጁ 21 የአካባቢ ማሰራጫ ጣቢያዎች ዉስጥ ቡታጅራ ከተማ ላይ አለመኖሩ የመዋቅራዊ ጭቆና አንዱ ማሳያ ነዉ ለስሙ የወልቂጤ ኤፍ ኤም ለጉራጌና ለስልጤ አካባቢዎች ያደርሳል ተብሎ ዘቢዳር ተራራ ላይ እንዲገነባ ቢታቀድም አቅዱ በተለያዩ ምክንያቶች አልተሳካም በዚህ ምክንት በአንድ ዞን ዉስጥ የምዕራቡ ጉራጌ የጋራ መረጃ ሰርጭት ሲያገኝ የምሰራቁ ጉራጌ ተደራሽ ባለመሆኑ ምክንያት ወደ ኦሮምያ ክልል ርቆ በመሄድ የአሰላ ኤፍ ኤም በተወሰኑ ሰኣት ያገኛል፡፤ታዲያ 650 ሺ ህዝብ የሚኖርበት አካባቢ እንዴት የማህበረሰብ ራዲዮ ያጣል፡፤ ስለሆነም ቡታጅራ ከተማ ላይ እራሱን የቻለ ኤፍ ኤም መገንባት ይኖርበታል እና በጋራ ምንታገልበት አጀንዳ ይሆናል ማለት ነዉ።

ቅጽ 3 ይቀጥላል ተከታትለዉ ያንብቡት

እባክዎ ሌሎች እንዲያነቡት የቻሉትን ያህል share በማድረግ ለልላው ያድርሱ

ታዬ ተስፋዬ ስሜ


64 views0 comments
bottom of page