top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ጓደኛ ለማፍራት ማወቅ ያለብን ጠቃሚ ነጥቦች


ህጻናት ሁሌም በውስጣቸው ጓደኛ የመፈለግ ስሜት አለ። በተፈጥሯቸው ብቸኝነትን ማስተናገድ አይችሉም። ታድያ ትልቅ ሰዎች ስንሆን ለምን እንቀየራለን? አዋቂ መሆንስ ምን ማለት ነው? ጓደኛ ማፍራትን ቀላል የሚያደርግ አንድ አረፍተ ነገር አለ። "ጓደኛዬ ትሆኛለሽ ወይም ትሆናለህ?" ማለት ነው።

አዋቂ ሰዎች ብዙ ጊዜ ስለ ብቸኝነት ሲያወሩ ይሰማሉ። በእንግሊዝ ብቻ 2.4 ሚሊዮን ሰዎች እጅግ የከፋ ብቸኝነት ያሰቃያቸዋል።

ነገር ግን ይህን ችግር በቀላሉ መፍታት ይቻላል። ጓደኛ ለማፍራት የሚጠቅሙ ነጥቦች አነሆ።


1. አንድ ቡድን ይቀላቀሉ

አንድ የሚወዱት ነገር ያሰባሰባቸው ሰዎችን ፈልገው ይቀላቀሉ። እነዚህን ሰዎች ያገናኛቸው ነገር እርስዎንም ወደ ቡድኑ የማይስብበት ምንም ምክንያት የለም። ብዙ ጊዜ ሰዎች ምን እንደሚያስደስታቸው ስለማያውቁ እንደዚህ አይነት ቡድኖችን ሲቀላቀሉ የሚወዱትንና የሚጠሉትን ነገር ለመለየት ይረዳዎታል።

አዲስ ነገርን ለመሞከር ፈፅሞ አይፍሩ። ቴክዋንዶ ወይንም የስዕል ትምህርት ቢጀምሩስ? ሊወዱት ይችላሉ፤ በዚያውም ጓደኞች ያፈሩበታል። ካልወደዱት ግን ሌላ ነገር ይሞክሩ። በመጨረሻ የሚወዱትን ነገር ከጥሩ ጓደኞች ጋር ያገኙታል።


2. በበጎ ፈቃድ ሥራ ላይ ይሳተፉ

በሚወዱት ጉዳይ ላይ ወይንም ሰዎችን መርዳት በሚፈልጉበት ዘርፍ በበጎ ፈቃድ ማገልገል ከሚያስቡት በላይ እርካታ ከመስጠቱ በላይ ብዙ ሰዎችን ለመተዋወቅ እጅግ አመቺው ቦታ ነው።

ብዙ ጊዜ በጎ ፈቃደኞች አዛኝና ቸር ናቸው። ይሄ ደግሞ ጥሩ የጓደኛ መለኪያ ነው።


3. ስልክ ቁጥር ይለዋወጡ

ጓደኛዬ ቢኖራት ወይም ቢኖረው ብለው የሚያስቡትን ባህሪ በአንድ ሰው ላይ ሲያገኙ ፈጥነው ሌላ ጊዜ መገናኘት የሚችሉበትን መንገድ ያመቻቹ። ይህንን ለማድረግ የመጀመሪያው መንገድ ደግሞ ስልክ ቁጥር መለዋወጥ ነው።

ምናልባት አንድን ሰው ድንገት ስልክ ቁጥር መጠየቅ ሊያስፈራ ይችላል፤ ነገር ግን ጓደኝነቱ ከይሉኝታው ሊበልጥ የሚችልበት አጋጣሚ ከፍተኛ ነው።

"ደግመን መገናኘት እንችላለን? ስላገኘሁሽ ደስ ብሎኛል ወይም ስላገኘሁህ ደስ ብሎኛልና ብንደግመውስ?" የሚሉት ጥያቄዎች ለመጠየቅ አይፍሩ።


4. እሺ ይበሉ

አዲስ የተዋወቁት ጓደኛ እራት እንብላ፣ ፊልም እንመልከት አልያም አንዳንድ ሰዎች ላስተዋውቅዎ ሲልዎት ሁሌም ቢሆን እሺ ይበሉ።

ከማያውቁት ሰው ጋር ረጅም ጊዜ ማሳለፍ ሊከብድ ይችላል፤ ነገር ግን ደፈር ብለው የመጀመሪያውን እርምጃ ካልተራመዱ የሚወዱትና የሚያምኑት ጓደኛ ማግኘት ሊከብድዎ ይችላል።

በመጀሪያው ግብዣ ቢቀሩ እንኳን ለቀጣዩ እንደሚሄዱ ቃል ይግቡ።


5. መገፋትን አይፍሩ

መርሳት የሌለብዎት ነገር ጓደኛዎ እንዲሆኑ የፈለጓቸው ሰዎች ሁሉ ጓደኛዎት ላይሆኑ እንደሚችሉ ነው። ይሄ ግን ብዙ ሊያሳስብዎ አይገባም፤ ምክንያቱም የተዋወቁት ሰው ሁሉ ጓደኛዎ የሚሆን ቢሆን ኖሮ ይህንን ጽሁፍ አያነቡም ነበር።

ደፈር ብለው አዲስ ጓደኛ ለማፍራት የቻሉትን ነገር ሁሉ ያድርጉ። እንገናኝ በተባለው ቦታና ሰዓት ሴትዮዋ ወይም ሰውዬው ባይገኙ ምንም ማለት አይደለም።


6. የሥራ ባልደረባዎችን ጓደኛ ያድርጓቸው

አብዛኛዎቻችን ከቤተሰቦቻችን ጋር ከምናሳልፈው ጊዜ በላይ ከሥራ ባልደረቦቻችን ጋር ብዙ ጊዜ ስለምናሳልፍ፤ የቅርብ ጓደኛ ብናደርጋቸው ከጉዳቱ ጥቅሙ ያመዝናል።

ምናልባት ከባልደረቦች ጋር ከሥራ ያለፈ ነገር ማውራት ላይለመድ ይችላል፤ ነገር ግን ደፍረው ግንኙነቱን ወደ ጓደኝነት ለመቀየር ከሞከሩ ጥሩ ጓደኞች ሊያገኙ ይችላሉ።

ከሥራ ባልደረባዎ ጋር ወጣ ብለው ከሥራ ጋር ጋር ያልተገናኙ ነገሮችን ያድርጉ።


7. ስለሰው ለማወቅ ይሞክሩ

ስለራስዎ ለማውራት የሚፈሩ ከሆነ አልያም የሚያወሩት ነገር የሚጠፋብዎ ከሆነ ሰዎች ስለራሳቸው እንዲነግርዎ ይጠይቁ።

ብዙ ሰዎች ስለራሳቸው ማውራት ላይከብዳቸው ይችላል። በዚያው ደግሞ ሌሎች ጥያቄዎችም አብረው ስለሚመጡ ይህኛው መንገድ ይበልጥ ውጤታማ ነው።


8. የሚያስደስታቸውን ነገር ያድርጉ

ትንሽ ሊመስሉ የሚችሉ እንደ ልደት ያሉ አጋጣሚዎችን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል። ሰዎች ልደታቸውን አስታውሰን ስጦታ ስንሰጣቸውና መልካም ምኞታችንን ስንገልጽላቸው በጣም ደስተኛ ይሆናሉ።

አንድ ሰው ጥሩ በማይባል ሁኔታ ውስጥ ካለም ለመርዳት መሞከርና ቅርበትን ማሳየት ጠቃሚ ነው።


9. ለብዙ ነገሮች ክፍት ይሁኑ

እርስዎ ለጓደኛ ብለው የሚያስቧቸው ሰዎች የሚፈልጉትን ሁሉ መመዘኛዎች ላያሟሉ ይችላሉ። ስለዚህ ካሉት የተሻለውን ጓደኛ መርጦ ግንኙነት መመስረት የተሻለ ይሆናል።

እርስዎ ውሻ ቢወዱ ምናልባት ጓደኛዎች ድመት ልትወድ ወይም ሊወድ ይችላል። ይህ ቀላል ምሳሌ ነው። ልዩነቱ በብዙ ነገሮች ሊገለጽ ይችላል።


10. አይቸኩሉ

በአጭር ጊዜ ውስጥ ውድ ጓደኛ ማግኘት የማይታሰብ ነው። በአንድ ጊዜ አንድ ጓደኛ ብቻ ሊኖርዎት አይገባም። ዋናው ነጥብ መሆን ያለበት በተቻለ መጠን ብዙ ጓደኞች እንዲኖርዎት እድርገው ከጊዜ ብዛት የቅርብ የሚሉት ጓደኛ መምረጡ ላይ ነው።

ምንጭ - BBC Amharic

34 views0 comments
bottom of page