top of page
  • Writer's pictureየመስቃን ብዙሃን መገናኛ አውታረ መረብ

ግምትና መላ-ምትግምትና መላ-ምት

“የፈለገውን ያህል በእውቀት የመጠቀና በሃብቱ የናጠጠ፣ የትኛውንም ያህል ዝናና ክብር፣ እንዲሁም ጀግናና ጉልበታም ቢሆንም ለብቻው መኖር የሚችል የሰው ዘር የለም። “ለሰው ሰው ያስፈልገዋል”።

አሁን አሁን ዘመነኛው ሰው መሰሉን ዘረ አዳም-ሄዋንን ከአውሬ በበለጠ የሚፈራበት እረከንና ወቅት ላይ ደርሷል። በአራቱም ማእዘን የሚገኘው የሰው ልጅ ከአውሬዎች በላቀ ሁኔታ ሲተላለቅ ይስተውሏል። ምንአልባት ለመኖር የሚያድኑትን የዱር አራዊቶች ሁኔታ ብንቃኝ ወይም በአንድ ቀን ውስጥ ምን ያህል የዱር እንሰሳዎችን ለፍጆታቸው አውለው ሊሆን ይችላል የሚለው ቢጠና ከሰው ልጁ መተላለቅ በእጅጉ ያነሰ ነው የሚሆነው።

ከአስራ ሁለት አመት በፊት ይሆናል አንድ አብሮ አደጌ እና የማከብረው ጓደኛዬ ነበር። እንኖርበት የነበረ ከተማ ውስጥ የሚገኝ ሃይፐር ማርኬት የእሳት አደጋ ደርሶበት የነበረ ሲሆን የሃይፐር ማርኬቱ በእሳት መጋየትን በተመለከተ ደረሰኝ ብሎ የነገረኝ መረጃ ወይም ወሬ “የድርጅቱ ባለቤቶች ከኢንሹራስ ካንፓኒ ጋር በሚስጥር ተወያይተው ነው ያቃጠሉት” የሚል ነበር። በጣም ከመገረሜ የተነሳ የሚስጥር ውይይታቸው ወይም ሚስጥር ብለው በዝግ የዶለቱት እንዲሁም የመረጃ መለዋወጫው ዘዴ እንደዛሬው ባልተስፋፋበት ወቅት ወሬው እንዴት ጓደኛዬ ዘንድ ሊደርስ እንደቻለ ስጠይቀው እርሱም በመገረም ጉዳዩን አስተውሎት ነበር። በተጨማሪም መቼቱን እና ማስረጃውን ያቀረበ እንዲሁም የሚያቀርብም አካል አልነበርም። ሚስጥር አፈትልኮ ሊወጣ ይችላል ነገር ግን ሁሉም ሚስጢር ገሃድ አይሆንም። ገሃድ የሚሆን ከሆነማ ሚስጢር የሚለው ቃል ባላስፈለገ ነበር።

ሌላው ዛሬ ላይ ሆኜ በደቦ ስራ ሰበብ የማገኛቸው አንቱ የተባሉ ግን ስነ ምግባራቸው የተዛነፈ ግለሰብ አሉ። ያው…እንደ ሰው እኔና እኛ ሰው ነንና ከማህበረሰባችን ጋር መልካምን ሰብከውና ቆንጥጠው ያሳደጉንን ቤተሰቦች እንዲሁም የቀደምት ማህበረሰብ ፈለግን በመከተል በብላሽ ማገልገል ከጀመርን ሰንበትበት ብሏል። ታዲያ እኒሁ ግለሰብ ከአይናችሁ ጉድፍ አለ ከጉያችሁና ከልባችሁ ደግሞ የተሸሸገ አለ የሚለው ዲስኩራቸው በዛና እኔም እልክ ቢጤ ያዘኝና እርሳቸውን መድፈሩ ቢከብደኝም በሃሳቤ አልኳቸው “አንቱዬ ምናልባት ከአይኔ ያለውን ጉድፍ እንዲያወጡ እፈቅድሎት ይሆናል… ነገር ግን ከውስጤ ውስጥ የተሸሸገ ቢኖር እንኳን ከፈጣሪዬ በቀር ሊያውቅና ፈልጎ ሊያገኝ የሚችል ስለሌለ ጊዜዎንና አቅሞን ባያባክኑ። ምናልባት የእርሶን የማያልቀውን ጉዳጉድ ዘንግተውት ቢሆን እንጂ… የሃገሬ ሰው ምን ብሎ እንደተረተ ያውቃሉን ?

ከብቶቹ በሌሉበት ሄዳ ኩበት ለቀማ

ተመልሳ መጣች የራሷን ጉድ ተሸክማ

ደግሞም የእርሶው ግምትና መላ ምት ካልሆነ በቃ! ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን እንደፃፈው አይነት ነው። “ስራዬን የሰው ልጅ ስለ ወሰደብኝ የስራ ለውጥ ይደረግልኝ” ብሎ ያመለከተውን የዲያቢሎስን ስራ የነጠቁት እርሶ ነዎት ብዮ በሃሳቤ በድፍረት ተናገርኳቸው።

ግምትና መላ ምት በወዳጃሞች፣ በተጓዳኞችን፣ በቤተ ዘመድ፣ መሃል ቅራኔና ጥላቻን አንግሶ እሰከ መለያየት የተደረሰባቸው ክስተቶች በርካቶች ናቸው። በተጨማሪም ቅራኔና ጥላቻው ሰማይ ነክቶ የተጎዳዱና የተላለቁም እንደዚሁ በርካቶች ናቸው።

ይቀጥላል


41 views0 comments
bottom of page